ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በጣምራ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!
የሕውሓት/ ኢህአዴግ መንግሥት ምርጫውን ለማራዘም እንደሚፈልግ በካድሬዎቹ እና ለራሱ ቀረቤታ ባላቸው ግለሰቦች በኩል ሲያስወራ የቆየ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የሰላማዊ ትግሉን ጨርሶ ለመዝጋት እያሳየ ባለው እኩይ እቅድ መሠረት ጠንካራ ፓርቲዎችን፣ የነፃ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ለመዝጋት ዳርዳር በማለት ላይ ይገኛል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጠቅላላ ጉባዔውን ሐምሌ 13 እና 14 ቀን 2005 ዓ.ም ባደረገው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ላይ ሁለት የምርጫ ቦርዱ አመራር ተወካዮች በተገኙበት ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
እነዚህ አመራሮችም ኮረም መሙላቱን በቦርዱ አካሄድ መሠረት ካረጋገጡ በኋላ ስብሰባው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ መኢአድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህግና ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ስብሰባውን አካሂዶ እያለና ከ600 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት 390 ታዳሚዎች በተገኙበት ስብሰባውን አካሂዶ እያለ ምልዐተ ጉባዔ አልተሟላም በሚል ሰበብ አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጠን እነሆ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመቱን ሙሉ ለህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ሁሉ መኢአድም ህጋዊነቱ ተጠብቆ ግብዣ እየተደረገለት አመራሮቹ አስፈላጊውን ስልጠና ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡
ዛሬ በህውሓት/ኢህአዴግ አባላት የሚመራው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሰላማዊ ትግሉ ላይ ከፍተኛ መሰናክሎችን በመፍጠር ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎች እንዲቀሙ፣ እንዲዘረፉና ኮሮጆ እየተገለበጠ ለገዢው ፓርቲ እንዲሰጥ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው ሁሉ በየክልሉ፣ በየዞኑ እና ወረዳዎች የተሰማሩ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች አንድም የገዢው ፓርቲ የደህንነት አባላት አሊያም የየሚገኙበት ቦታ የካቢኔ አባላት መሆናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተደበቀ አይደለም፡፡ ይህ ፍትሀዊና ታአማኒነት ያለው ምርጫ የማይካሄድ መሆኑን ከተረዳን የቆየን ቢሆንም ይኼን ሁሉ ተሸክመን እየተጓዝን እያለ ዛሬ በግልጽ ፓርቲዎችን ለመዝጋት መሞከሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈፀመው ያለው ከድፍረቶች ሁሉ ድፍረት ነው፡፡ የህውሓት / ኢህአዴግ መንግሥት የሰላማዊ ትግሉን ቢቻለው ለመዝጋት ከጫፍ ላይ የደረሰ ቢሆንም ቅሉ እኛ ግን በሰላማዊ ትግሉ ላይ እስከመጨረሻ ድረስ በመጓዝ የምንገፋበት መሆኑን ከወዲሁ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ አድራጐቱ ተቆጥቦ ትክክለኛ የሆነ የምርጫ ሜዳ የማያዘጋጅ ከሆነ በሰላማዊ ሰልፍና ማንኛውንም የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ሁሉ በመጠቀም የምንታገል መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ ይህን ስናደርግ ምክንያት በመፈለግ ሊያስሩን፣ ሊያሳድዱንና ሊገድሉን እንደሚሞክሩ ከዚህ ቀደም እየታየ ካለው ልምድ የምናውቀው ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሊያደርጉብን የሚችሉ ቢሆንም በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ካለው መከራና የሰቆቃ ኑሮ ስለማይብስ የሚደርስብንን ሁሉ ለመሸከም ዝግጁዎች ስንሆን ሕዝባችንም ከጐናችን እንደሚቆም በመተማመን ነው፡፡ ለዚህም ወጣቱና አዛውንቱ በሚደረገው ማንኛውም የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሁሉ፣ በተግባር ከጐናችን በመቆም እንዲሳተፍ እየጠየቅን በእድሜ የገፉ አባቶችና እናቶች ደግሞ በፀሎታቸው እንዲያግዙን እንጠይቃለን፡፡ ዛሬ ህውሓት/ኢህአዴግ ሕዝቡን በደህንነትና መሳሪያ በታጠቀ ሰራዊት አፍኖ ይዞ እያደረሰበት ያለውን የጭቆናና የግፍ አገዛዝ፣ ረሀብ፣ የሰቆቃ ኑሮ አቤት ማለት እንዳይችል አድርጐ አፍኖ በመግዛት ላይ ነው፡፡ ሕዝባችን ይህን ሁሉ አውጥቶ የሚናገርበት የግል የብዙሃን መገናኛው እንዲዘጋ እየተደረገ ነው፡፡
ዛሬ ደግሞ በምርጫ ተወዳዳሪ ሃይል ሆነው ለመቅረብ ይችሉ ዘንድ ውህደት ለመፈፀም ያጠናቀቁ ፓርቲዎችን ማለትም መኢአድና አንደነትን የተለያዩ መሰናክሎችን በመፍጠር ውህደቱ እንዳይሳካ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የሚያሳየን ሁላችንንም በየተራ እየበላ የሚያጠፋን መሆኑን ሕዝባችን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህን ሁኔታ በጥሞናና በእርጋታ በመከታተል የዜጎችን መብት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሁሉ ከታጋዩች ጐን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ የደህንነት፣ የፖሊስ አባላት እና የመከላከያ ሠራዊቱ ጥቂቶቹን በሥልጣን ላይ ለማቆየት አንተ መሰቃየትና መሞት የለብህም፡፡ ጥቂቶቹ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማጥፋት በሥልጣን ላይ ለመቆየት በሚደረገው አድማና ሴራ የተነሳ ዜጎች ለመብታቸው መከበር ሲንቀሳቀሱ አንተ ዜጎችን ማሰቃየትና መግደል የለብህም፣ አንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማይጠቅም ነገር መሰዋዕት መሆን የለብህም፡፡
ስለዚህ የመንግሥት ሥልጣን ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሸጋገር ይችል ዘንድ በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ለመግደል ሳይሆን ከጎናችን ለመቆም መዘጋጀት አለብህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!! የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህን ሁሉ በደል እየፈፀመብን ያለው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን ግልጽ ለማድረግ እንወዳለን፡፡ ይኸውም፡-
1. የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐብትና ንብረት መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ቅሉ በህውሓት/ኢህአዴግ የአማራ ፓርቲ ነው በሚል ሲፈረጅ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደሙ ድርጅቶችንና ጠንካራ ግለሰቦችን ለማጥፋት በተያዘው አቅድ መሠረት መኢአድንም ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው በዚሁ መሠረት መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡
2. በአገሪቱ ላይ ገዢውን ፓርቲ የሚቀናቀኑ ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማጥፋት ከተያዘው እቅድ አንፃር በመንግሥት ወኪሎች የሚመራው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህን እየፈፀመብን ይገኛል፡፡
3. መኢአድና አንድነት ተዋህደው አንድ አማራጭ ሀይል ሆነው ቢቀርቡ የገዢውን ፓርቲ በምርጫ በማሸነፍ ሥልጣን እንደሚረከቡ ስለሚያውቁ ያን ጥንካሬ ለማኮላሸት በተያዘው እቅድ መሠረት ጊዜውን በማራዘም ውህደቱን ለማደናቀፍ በተያዘው እቅድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ዛሬ የአገዛዝ ስርዓቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት የዲሞክራሲ እንቅስቃሴህ ታፍኖ፣ ፍትህ በማጣትና እየደረሰብህ ያለውን ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል እና የፖለቲካ አስተዳደር አቤት የምትልበት አካል አጥተህ በጨለማ ጉዞ ውስጥ ወድቀሃል፡፡ በረሀብ፣ በቸነፈርና በሰቀቀን ኑሮ ቀለበት ውስጥ እንድትገባ ተደርገሀል፡፡ አሁን ደግሞ የተጫነብህን ጭቆና መግለጽ እንዳትችል የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲታፈኑ ተደርጓል፡፡ እንደ መኢአድ ያሉ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውኑ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተለያየ ስውር መንገድ ለማዳከም ጥረት ያደርጋል፡፡
መኢአድና አንድነት ተዋህደው አንድ ጠንካራ አማራጭ ሀይል ሆነው እንዳይቀርቡ ተልካሻ ምክንያቶች እየተፈለጉ የእንቅስቃሴ ገደብ የሚጣልባቸው ከሆነ፣ ጋዜጠኞችና ጠንካራ ታጋዮች በሽብርተኝነት ምክንያት እየተያዙ ወደ እስር የሚወረወሩ ከሆነ ማነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሆኖ የሚቀርበው? በአጠቃላይ የህውሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የሰላማዊ ትግል መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት እድሜውን ለማራዘም በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል፡፡ መኢአድን ለማፍረስ እየሞከረ ካለባቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በአጠፉት ጥፋት ምክንያት በፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ በፍ/ቤት ከፓርቲው የተባረሩ ግለሰቦችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና ድጋፍ በመስጠት ፓርቲውን ለመበተን ጥረት ያደርጋል፡፡
የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነቱ አባላት ሆይ!
እኛ የሰላማዊ ትግሉና በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ብዙ ጥረናል፣ ጥረት በማድረግ ላይም እንገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ የህውሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የምርጫ ቦርዱን መሳሪያ በማድረግ ፓርቲያችንን ለማፍረስ ከፍተኛ ሥራ በመስራት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም መሳሪያ በመሆን ፓርቲያችንን ለማፍረስ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ትናንትና የነፃ ኘሬስ ድርጅቶችን ለመዝጋት ወደ ፍ/ቤት ወስዷል፡፡ ዛሬ ደግሞ በአገሪቱ ላይ በጠንካራነቱ የሚታወቀውን ፓርቲ መኢአድን ለማፍረስ አስፈላጊ ያልሆነ ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የፖሊስ የመከላከያና የደህንነት አባላት ይህን ተገንዝባችሁ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ከገዢው ፓርቲ ወገናዊነት እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ዛሬ የህውሓት/ኢህአደግ መንግሥት እየጨቆነህ፣ እያሳደደህ፣ እያሰረህና እየገደለህ ያለው በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ለነፃነትህ በአንድነት እንዳትቆም በማድረግ፣ የኒው ኮሎኒያሊስቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ እንደ እድገት የሚቆጠር ብልጭልጭ የሆነና እድገት መሰል ህንፃዎችን በዋና ዋና መንገዶች ዳር በማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ የአገርህ ባለቤት ሳትሆን የእድገቱም ባለቤት መሆን ስለማትችል በአንድነት በመነሳት ከዚህ አስከፊ የጭቆናና የብዝበዛ ቀንበር ለመውጣት ከጎናችን እንድትቆም ጥሪያችንን እናስተላልፉለን፡፡ በአጠቃላይ የመኢአድና የአንድነት አመራርና አባላት የሆናችሁ ሁሉ በያላችሁበት ለሰላማዊ ትግሉ በተጠንቀቅ በመቆምና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እያደረሰ ባለው ጥፋት ላይ መግለጫዎችን በማውጣት ወቅቱ ለሚጠይቀው ትግል ጠንክራችሁ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም በያለበት ከእነዚህ አመራሮችና አባላት ጋር በመቆም ሰላማዊ ትሉን እንዲያጧጡፍ እንጠይቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከሕዝብ የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና ከያዘው የጥፋት መስመር በመመለስ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሕዝባችንን በትክክለኛው መንገድ እንዲያገለግል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
No comments:
Post a Comment