ለፖሊስ ከፍተኛ አዛዦች በኮልፌ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ከተጠናቀቀ በሁዋላ መደበኛ ፖሊሶች ደግሞ በተለያዩ የማሰልጠኛ ቦታዎች በግዳጅ ገብተው ስለመንግስት ፖሊሲና እቅድ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።
በኮልፌ በአዛዥ ፖሊሶች ሲጠየቁ የነበሩት ጥያቄዎች በመደበኛ ፖሊሶች ተጠናክረው መቅረባቸው ታውቋል። ከትናንት ጀምሮ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ግንቦት 20 እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ውስጥ 500 የሚደርሱ ፖሊሶች ገብተዋል። እያንዳንዱ ፖሊስ ለ12 ቀናት ስልጠና የሚሰጠው ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ፖሊስ ለ12 ቀናት 800 ብር በጀት ተመድቦላቸዋል። ይህ ገንዘብ ለምግብ፣ ለምኝታ እና ለሌሎችም ወጪዎች ሲሆን፣ ፖሊሶቹ ከስልጠና ቦታው መውጣት፣ ምግብ ከውጭ አስመጥቶ መብላት እና ለሻሂ እረፍት በሚል ወደ ውጭ መውጣት አይፈቀድላቸውም። 46 የሚሆኑ ነፍሰ ጡር ሴት ፖሊሶች ቤታቸው እየሄዱ እንዲያድሩ ቢጠይቁም የተፈቀደላቸው ግን 15 ብቻ ናቸው። ፈቃድ ከተከለከሉት መካከል የ3 ወር አራሶችም እንደሚጘኙበት ታውቋል። መሰረት ከስልጠናው በሁዋላ ቤታቸው እንዲያድሩ ሲፈቀድላቸው ሌሎች ፖሎሶች ግን በስልጠናው ቦታ ማደርና መዋል ግድ ይላቸዋል።
የተመደበላቸው በጀት አነስተኛ መሆኑና ለቁርስ፣ ለምሳና ለእራት የሚቀርብላቸው ምግብ ደረጃውን ያልጠበቀ ነው በማለት ቢቃወሙትም፣ አሰልጣኞቹ ግን ይህ ተደረገው ፖሊሱ ለመንግስት ያለውን ታማንነት ለመፈተን ተብሎ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
በንፋስ ስልክ በተካሄደው የመጀመሪያ ቀን ውይይት ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ይህ መንግስት ለህዝቡና ለእናንተ ምን ያላደረገው ነገር አለ? ምን ጉድለት አለበት? የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ፖሊሶች መንግስት እያደረገው ያለው ነገር እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን፣ የአስተዳደሩም ሁኔታ ልክ አለመሆኑን እና ለውጥ እንደሚያሻው በድፍረት ገልጸዋል። የመንግስት ባለስልጣናት ለህዝቡ ተሰሩ ያሏቸውን ስራዎች ዘርዝረው ቢያቀርቡም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፖሊሶች አጣጥለዋቸዋል። መንግስት ለአዲስ አበባ ፖሊሶች የኮንዶሚኒየም ቤት እንዲያገኙ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውና የቤት ችግራቸው እንደሚፈታላቸው ቢናገርም፣ ፖሊሶች ግን ከዚህ ቀደም የተገቡትም ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ አልሆኑም በሚል በባለስልጣኖች በድጋሜ የተገቡትን ቃል ኪዳኖች አልተቀበሉዋቸውም።
ፖሊሶቹ የመንግስትን ስትራቴጂንና ፖሊስን እንዲያውቁ፣ በመጭው ምርጫ ላይ ፖሊሶች መንግስት እንዲያሸንፍ ጥረት እንዲያድርጉ ተነግሯቸዋል። ተቃዋሚዎች የሚናገሩት የማይረባ መሆኑንና መንግስትን መደገፍ አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን ገልጸዋል።
ሰልጣኝ ፖሊሶች የስልክ ጥሪ ቢደርሳቸው ስልክ ማንሳት እንደማይችሉና የተደወለላቸውን ስልክ ለተቆጣጠሪዎች የማስመዘገብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። የስልክ ጥሪ የተቀበለና ጥሪውን ያላስመዘገበ ፖሊስ የዲሲፒሊን እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
በአዲስ አበባ የወጣቶች ስፖርት ማእከልም እንዲሁ 600 የሚሆኑ ፖሊሶች ለስልጠና እንዲገቡ ተደርጓል።