Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, August 14, 2014

የአዲስ አበባ መስተዳድር በቤቶች ግንባታ ዙሪያ ለምርጫ እንዲደርስ በሚል አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጠ

የአዲስ አበባ መስተዳድር በቤቶች ግንባታ ዙሪያ ለምርጫ እንዲደርስ በሚል አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጠ
በ40 በ60 በሚባለው የቤቶች መርሃግብር የታቀፉ የዲያስፖራ አባላት ከቀጣዩ ዓመት ምርጫ በፊት ቤት እንዲሰጣቸው የአዲስ አበባ መስተዳድር መመሪያ መስጠቱ ታውቋል።
ሆኖም የጠቅላላ ተመዝጋቢውን የቤት ፍላጎት ለመሸፈን በትንሹ ከ16 ዓመታት በላይ ጊዜን እንደሚወስድ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ እስካሁን 13ሺህ 800 ቤቶችን በሰንጋተራ እና ቃሊቲ ክራውን ሆቴል በመሳሰሉ አካባቢዎች ላይ እየገነባ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ፣ እነዚህን ቤቶች እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ ለዕድለኞች ለማስተላለፍ ታቅዷል።
የአስተዳደሩ ምንጮች እንደገለጹት ቤቶቹ ከቀጣይ ዓመት ምርጫ በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው እንዲተላለፉ ከአስተዳደሩ መመሪያ ተሰጥቷል። ሆኖም ለ40 በ60 የቤቶች ፕሮግራም የተመዘገበው ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር 164 ሺህ 779 ያህል ሲሆን አስተዳደሩ ግን በዓመት ከ10 ሺህ ቤቶች በላይ ቤቶችን የመገንባት አቅም ባለመፍጠሩ የተመዘገቡትን ብቻ ለማዳረስ ከ16 ዓመታት በላይ ጊዜን እንደሚፈልግ የአስተዳደሩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ይህ ደግሞ ከዛሬ ነገ የመኖሪያ ቤት ባለቤት እሆናለሁ ብሎ ተስፋ ላደረገው ሕዝብ ተስፋ አስቆራጭ ዜና ነው ብለዋል፡፡
በ20/80 በተለምዶ ኮንዶሚኒየም ፕሮግራም የምርጫ 97 ን መቃረብ ታሳቢ አድርጎ ሲጀመር ከ350ሺ በላይ የአዲስአበባ ነዋሪ መኖሪያ ቤት እፈልጋለሁ ብሎ መመዝገቡን ያስታወሱት ምንጮቹ ፣ ፕሮግራሙ 10 ዓመታት ያህል ቆይቶ መመለስ የቻለው ግን 100 ሺ በታች ቤት ፈላጊዎችን ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት የጠቅላላ ተመዝጋቢውን ፍላጎት ለሟሟላት ተጨማሪ ከ20 ዓመታት በላይ ጊዜን እንደሚወስድ አፈጻጸሙ በራሱ የሚናገር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአስተዳደሩ ምንጭ እንደሚሉት መንግሥት በአዲስ አበባ በዓመት ለቤቶች ግንባታ ብቻ ከ2 እስከ 3 ቢሊየን ብር እያወጣ መሆኑን አስታውሰው ከዚህ በላይ ለማውጣት የፋይናንስ አቅም ችግር መኖሩን፣ ገንዘቡ ቢገኝም በግንባታ አፈጻጸም በኩል የአቅም ችግር በመኖሩ በአጭር ጊዜ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለመመለስ የማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለጹት ደግሞ ዲያስፖራው በፈለገበት አካባቢ ቤት ለመስራት ይችል ዘንድ ክልሎች መመሪያ እንዲያወጡ መታዘዙን ገልጸዋል። ሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የሆነ መመሪያ ባለማውጣታቸው ለዲያስፖራው ቤት ለማደል የታቀደው እቅድ የተፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ኢሳት የአዲስ አበባን አዲሱን ካርታ ዝግጅት አስመልክቶ ከወራት በፊት በሰራው ዘገባ፣ የቤት ግንባታ መርሃግብሩ የተሰናከለው በአዲስ አበባ የቤት መስሪያ ባዶ ቦታ በመጥፋቱ ነው። ቀደም ብሎ የኦሮምያን ልዩ ዞኖች ወደ አዲስ አበባ በመጠቅለል የቤት መስሪያ ቦታዎችን ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የኦሮምያ ክልል አንዳንድ ባለስልጣናትና አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ በመቃወሙ እቅዱን በቀላሉ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። ዲያስፖራው ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ቦታዎችን እንዲጠይቅ ለማግባባት ኢምባሲዎች የስራ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለአባይ ግድብ በቦንድ ስም ገንዘብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለማሰባሰብ የታቀደው እቅድ አለመሳካቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምነዋል። ከፍተኛ ገንዘብ ይገኝበታል የተባለው የአሜሪካ የቦንድ ሽያጭ አምና ጭራሽ አልተካሄደም ብሎ መናገር እንደሚቻል ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በሁሉም አገሮች ያለው የቦንድ ሽያጭ ደካማ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ፣ ለድክምቱ ዝርዝር ምክንያቶችን አላቀረቡም። የዶ/ር ቴዎድሮስ ገለጻ፣ ኢሳት ከዚህ ቀደም የቦንድ ሽያጩ በውጭ አገር አለመሳካቱን ሲዘግብ የቆየውን ያረጋገጠ ሆኗል።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ገንዘብ ለመሰብሰብ በገዢው ፓርቲ በኩል የሚዘጋጁትን ዝግጅቶች አጥብቆ ሲቃወም እንደነበር ይታወቃል። አቶ መለስ የአባይን ግድብ እቅድ ይፋ ሲያደርጉ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ 1 ቢሊዮን ዶላር ያዋጣል የሚል እምነት ነበራቸው፣ ይሁን እንጅ እስካሁን ባለው መረጃ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊያዋጣ አልቻለም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials