Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, August 24, 2014

በአሶሳ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ተከስቷል

አንድ ሰው በበሽታው ሞቷል
የክልሉ ጤና ቢሮ በሽታው ኢቦላ አይደለም ብሏል 
በሽተኞች ላይ ደም ማስመለስና ማስቀመጥ ተስተውሏል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምግብ መበከል ሊሆን ይችላል ተብሎ የተጠረጠረ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ በሁለት ሰዎች ላይ መከሰቱንና አንደኛው መሞቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ታዬ ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን የኢቦላ በሽታ በክልሉ በየትኛውም አካባቢ አልተከሰተም ብለዋል፡፡ 
የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በክልሉ በሚገኘው ባምባሲ የስደተኞች ጣቢያ በሽታው ተከስቷል ሲሉ ያሰራጩት መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፤ ለጊዜው በትክክል ምንነቱ ያልታወቀው በሽታ የተከሰተው ከስደተኞች ጋር ምንም አይነት ንክኪ በሌለው የአሶሳ ከተማ መንደር 47 በሚባል አካባቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 
በህክምና ባለሙያዎች የምግብ መበከል ሊሆን ይችላል በተባለው በዚህ በሽታ የተያዙት ሁለት ግለሰቦች ላይ የታየው ምልክት ደም ማስመለስና ማስቀመጥ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሃብታሙ፤ በሽተኞቹ ለብቻ ተገልለው በጥንቃቄ እንዲታከሙ ተደርጓል፣ የአንደኛውን ህይወት ማትረፍ ባይቻልም ሌላኛው ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ህክምናቸውን እየተከታተሉ ነው ብለዋል፡፡ 
የኢቦላ በሽታ ምልክቶች ከሌሎች በሽታዎች ጋርም ሊመሳሰል ይችላል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ነገር ግን በህክምና ባለሙያዎች በሽታው ኢቦላ አለመሆኑ ተረጋግጧል፤ በሽታው የምግብ መበከል ሳይሆን እንዳልቀረ ተጠርጥሯል ብሏል፡፡ 
በድንበር አካባቢ በሽታው ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ የጠየቅናቸው ኃላፊው፤ ሱዳን ውስጥ በሽታው ስለሌለ ስጋት የለብንም ብለዋል፡፡ 
ህብረተሰቡ በሽታው ኢቦላ ነው በሚል እንዳይደናገጥ በክልሉ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ትናንት ጠዋት ቀርበው በሽታው ኢቦላ አለመሆኑን ማስረዳታቸውን አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡ ተጨማሪም ግብረ ሃይል በማቋቋም ምንነቱ በትክክል ያልታወቀውን በሽታ ለማጣራት ባለሙያዎች የተከሰተበት ቦታ ድረስ በመሄድ የማጣራት ስራ መስራታቸውንና ኢቦላ በክልሉ የትኛውም አካባቢ እንዳልተከሰተ ማረጋገጣቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አህመድ አማኖ፤ በሃገሪቱ በየትኛውም አካባቢ ኢቦላ አለመከሰቱን ከየክልሎች በሚሰበሰቡ መረጃዎች መረዳት መቻሉን ለአዲስ አድማስ ገልፀው፤ ምናልባትም ከሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ትኩሳት፣ የአፍንጫ መንሰር ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል፡፡ አሶሳ ተከሰተ ተብሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲዎች የተሰራጨውም ትክክለኛ መረጃ አይደለም ብለዋል ኃላፊው፡፡ 

http://addisadmassnews.com/

No comments:

Post a Comment

wanted officials