ሁላችንም ታስረናል፤ ነጻ
እንድንወጣ ሁላችንም እንነሳ
መላዋ ኢትዮጵያ
እስር ቤት ሆናለች ።ከአሳሪዎቹ ከወያኔ ኢህአዴግ በስተቀር ከ 82 በላይ ብሄር በሄረሰቦች በጠቅላላ በጽኑ እስር ላይና አሳራቸውን በመብላት ላይ ይገኛሉ። ለናሙና ያህል ብንመለከትም በቀለ ገርባ ና ጓደኞቹ ከኦሮሞ፤አንዷለም አራጌ፣ የሽዋስ
አሰፋና ጓደኞቹ ከአማራ ፤ አብርሃ ደስታ ና አረናዎች ከትግራይ፤ ኦኬሎ አኳይና ጓደኞቹ፡ ከጋምቤላ ፤ ባሽር ማክታልና ጓደኞቹ፡ ከ ሶማሊ ( ኦጋዴን) ፤ዳንኤል ሽበሺ እና ጓደኞቹ (ከ ደቡብ
ክልል)፤
አንዳርጋቸው ጽጌ ፣ እስክንድር፣ ርእዮት፣
አቡበክር ቅይጥ (ከ አዲስ አበባ)
እና ሌሎች ወዘተ ስብጥር ስናይ በእስር ቤት የብሄር ብሄረሰቦችን ተዋጽኦ ለማረጋገጥ በሚመስል መልኩ ወገኑ ያልታሰረበት የሃገሪቱ ክልል የለም።
ከእስር ቤት በስተቀረ የመከላከያ አዛዥነትን ብንመለከት ግን ከ 60 ከፍተኛ
መኮንንነት ውስጥ 58ቱ ከትግራይ ብቻ የተመደቡ ናቸው። በየሃይማኖት ተቋማቱ፥ ብአዴንም ሆነ በሌሎችም
መሰሎቹ የኢህአዴግ ፖለቲካ ድርጅቶች ፥ በተለያዩ የኢኮኖሚ
ዘርፎች የመሪነቱን ሚና በሞኖፖሊ የሚሾፍረው ወያኔና ወያኔ የሆነ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያን በገጠርና በከተማ ከፍለን ብናይም መላ ገጠሬው መላ ከተሜው ታስሯል። ገበሬውን አንድ ለ አምስት በሚሉት የትብተባ ገመድ በመተብተብ ወሬኛ አድርጎታል።
በሰንበት ሳይቀር የሃይማኖት ተቋማትን እንዲተው በማደረግ የክህደት አብዮታዊ ወያኔነትን በግድ ይግቱታል። ከወያኔ መዋቅር አልታቀፍም ካለ የእህል ማዳበሪያ ይከለከላል ሰለዚህ ይታሰራል። አንዱ ገበሬ
ሌላውን እንዲሰልል በማድረግ ጥንታዊ አብሮነቱን እየሸረሸሩት ነው።
በከተማ ያለው የትራንስፖርት ችግር ሰልፈኛ አድርጎናል። የኑሮ ውድነት የስራ እጥነት ገዝፎ ሰራ ለመቀጠር
የኢ ህ አ ዴ ግ አባል መሆን የግድ ነው።የ ወጣት ሊግ የ አዛውንት ሊግ የሴቶች ሊግ
ፎረም ወዘተ የወያኔ የመዋቅር እስር ቤቶች ናቸው። መደገፍ እንጂ መቃወም አይችሉም። ተጠቅላይ ምኒስትሩ ኃይለማርያም ደሳለኝም አሻንጉሊት ናቸው !
ሌሎቻችን የበይ ተመልካች መባሉ ቀርቶ ሲበሉ እንዳናያቸው ጭለማ እስር ቤት አጉረውናል።
ተፈጥሮኣዊ በሆነው የመናገር የመጻፍ መብታችንን በመጠቀም ፍትሃዊ የሃብት
ክፍፍል ይኑር ፥ዜጎች በእኩልነት ይታዩ፥ መልካም አስተዳደር ይሰፈን፥ የሃገር አንድነት ይጠበቅ ብለን ስንናገር ስንጽፍ እንቀሰፋለን።ይባስ ብሎ ነጻንታችንን ለመለጎም ባወጣው የጸረ
ሽብር ህጉ ሰበብ ሰለ ፍትሕ፥ስለነጻነት ፥ ስለዲሞክራሲ ማቀንቀን ግንቦት ሰባት ወይም ኦነግ አሰኝቶ በ “አሸባሪነት” እድሜ ልክ ያስወነጅላል።
ስድስት ሰላማዊ የዞን ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞችን ያገተው የካድሬነት ስራ የሚሰራው ፖሊስ
የረባ የሃሰት ክስ መጎንጎን አቅቶት ለሁለት ወራት ያህል የፍርድ
ቤት ቀጠሮ ሲያራዝም ነበር። ጦማሪያኑ በየብዕሮቻቸው የሃይል አማራጭ የሚወስዱትን ግንቦት ሰባትንና ኦነግን የሚቃወሙና በሰላማዊ
ምርጫ መንግስት እንዲለወጥ የሚወተውቱ መሆናቸው እየታወቀ ግማሾቹን
ከግንቦት ሰባት ገሚሶቹን ከኦነግ ጋር ግንኙነት የነበራቸው
በማለት የክስ ድራማ ስክሪፕት ከሁለት ወራት መጉላላት በኋላ ጽፎ ሰጥቷቸዋል ።
የግንቦት
ሰባት የፍትሕ የነጻነት የዴሞክራሲ ንቅናቄ መስራችና ዋና
ጸሃፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታፍነው መያዛቸው በተገለጸበት ቅጽበት በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ከሆኑት መካከል አቶ ሐብታሙ አያሌው እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከአንድነት፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ፣ አቶ አብርሃ ደስታ ከአረና ትግራይ ተይዘው ወደ ሰቆቃው ማእከል ማእከላዊ ተወርውረዋል።የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ከግንቦት ሰባት እና ከአንዳርጋቸው ጋር አቆራኝቶ ለመወንጀል
እየሮጠ ያለው ወያኔ ጉልበቱን እና የሃገር አንጡረ ሃብትን በመጠቀም ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል በዜጎች ላይ እየፈጸመ ይገኛል።
እያንዳንዱን ሰው ባሰሩ ቁጥር አሸባሪ የሚል ስም ይለጥፉበታል። የጸረ ሽብር ህጉ በጣም ልቅ የሆነ ሰልጣን አጎናጽፏቸዋል። ሕገ መንግስቱ ሰው በተያዘ በ 48 ሰዓት
ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ቢልም የጸረ ሽብር
ህጉ ፖሊስ ከ 2 ወር እስከ 4 ወር ጊዜ በላይ
ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ማገት እንደሚችል ሰለሚፈቅድ ሀገ መንግስቱ ተጥሷል። በተጨማሪም ፖሊስ በዘፈቀደ
መንገድ ላይ አካሄዱ ያላማረውን ማንኛውም ሰው
መያዝ እንዲሁም ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ግለሰብን መበርበር እንደሚችል መብት ሰጥቶታል። ፖሊስ ይሕን መሰል የካድሬነት ስራ እንዲሰራ ያደረገው ሕገ መንግስቱ ተጥሶ ነው።
በሰላማዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን የሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ወያኔ በሰራው አጥማጅ ህግ ከመከሰስ አላመለጡም። ሃሳባች ሁን በግል ሚዲያዎች ጋዜጦች፥ በኢሳት ቴሌቪዥን
በ ኢንተርኔት ወዘተ ለምን ገለጻችሁ ተብሎ ፓለቲከኞቻችንና የግል ጦማርያንም ታስረዋል። በ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢቴቪ እንዳይጠቀሙ
ማደረጉ ሳያንስ የግል ሚዲያዎችን ኢሳትን ጨምሮ መከልከሉ ምንም አትተንፍሱ ሙቱ ማለት ነው። ሃገር ቤት
ያሉ የ መጽሄት የ ጋዜጣ ኣዘጋጆች የጸረ ሽብር ህጉ ማንኛውም ጽሁፍ አንቀጽ ፮
ሊያሰጠይቃቸው ስለሚችል በጣም እየፈሩ ይገኛሉ፤ ሁላችንም የፖሊስን ዱላ ና እስር ቤት ጸበል ጸዲቅ እየተጋፋ እየቀመስን ነው።
መንግስት በግልጽ
ጣልቃ በሃይማኖት ውስጥ በመግባት ያራሱን ካድሬ ቄስና ካድሬ ሼክ ሾሟል። ይህንን የተቃወሙ ሙስሊሞች በየጁምአው እየታሰሩ ይገኛሉ። ድምጻችን ይሰማ እያልናቸው ያፍኑናል።እስከመቼ አንዱ ሲታሰር አንዱ ቆሞ ያያል። ቆሞ የሚያያውም ሰለማያገባው ሳይሆን የወያኔን ዱላና እስር በመፍራት ነው። እስከመቼ ሁላችንም በ ፍርሃት ተሸብበን እንኖራለን???
የፍርሃት ድባብን በመስበር የታሰርንበትን ፍርሃት ሰንሰለት እንበጥሰው።
ከቃሊቲ፥ ከ ማዕከላዊ ፥ከዝዋይ፥
ከብርሸለቆ ና ሌሎችም ቦታዎች የታሰሩትን
ወገኖቻችንን ማስፈታት የምንችለው በዞን አስር
ታስረን በተወሰነ መልኩ የምንንቀሳቀሰው ሰዎች ነን።
ኑሮ ተወደደ ዘረኝነት ስር ሰደደ ብለን ሰለተቃወምን የሚገድለን ዘረኛ ፋሺስት ቅኝ አገዛዝ ተወግዶ በዲሞክራሲያዊ በህጋዊ መንገድ የተመረጠ የመንግስት ስርዓት እንዲኖረን የምንፈልግ ፍትህ የናፈቀን ለራሳችን
ነጻነት ስንል ለፍልሚያ መዘጋጀት ግድ ይለናል። በእርግጥ የነ ርዕዮት አለሙ፥የውብሸት ታዬ፥ የበቀለ
ገርባ የነ አቡበከር፥ ና ለሎችም መታሰር ብቻ ሳይሆን ታስረውም ህክምና መከልከል ሲቀጥልም በየዕለቱ የሚፈጸምባቸው ግርፋት ድብደባ ቶርቸር ይቅር ብሎ
ሰልፍ መውጣት ጫካ መመሸግ ከሰብዓዊነት የመነጨ ነው። የዲሞክራሲ ተሟጋች
ብርቅዬዎቻችንን ምሳሌ ለመጨመር ያህል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን
አሳስረን ዝም የምንልበት ጊዜ አይደለም የ
አሁኑ ወቅት።
ምክንያቱም
በነሱ መታሰር ነጻነታችን የሚዘገየው የኛ ነው ፤ የወያኔ ዘር ባለመሆናችን
አድልዎ የሚፈጸምብን፤ ፍትህ የተጓደለብን እኛም ታሰረናል ፥ እንፈታ ፥ ያገባናል።
ሁላችንም በነጻነት እንድንኖር ተባብረን እንታገል !
አብርሃም ዘ.
No comments:
Post a Comment