በአሜሪካ ከጠፉት አትሌቶች ሁለቱ ከ“ናይኪ”ና ከ“አዲዳስ” ጋር ተፈራርመዋል
በዓለም የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል ወደ አሜሪካ አቅንተው ከነበሩ አትሌቶች መካከል ባለፈው ቅዳሜ ድንገት ከተሰወሩትና ከቀናት ቆይታ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱ ከታዋቂዎቹ ‹ናይኪ›ና ‹አዲዳስ› ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ኦሪጎን ላይን ድረገጽ ትናንት ዘገበ። አማኑኤል አበበ፣ ዱሬቲ ኢዳኦ፣ መዓዛ ከበደና ዘይቱና ሞሃመድ የተባሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ ባለፈው ቅዳሜ ከልዑካን ቡድኑ ተለይተው መጥፋታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የኦሪጎን ፖሊስ ትናንት በሰጠው መግለጫ ከጠፉት አትሌቶች መካከል ዘይቱና ሞሃመድ ከናይኪ፣ ዱሪቲ ኢዳኦ ደግሞ ከአዲዳስ ጋር የኮንትራት ስምምነት መፈራረማቸውን ከቡድኑ አሰልጣኞች ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ የኦሪጎን ፖሊስ አትሌቶቹ ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት ሊጠፉ አንድ ቀን ሲቀራቸው እንደነበር መግለጹን የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩን በተመለከተ ሁለቱንም ኩባንያዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ጠቅሷል፡፡
ፖሊስ አትሌቶቹ በአሜሪካ የመቅረት ዕቅድ ይዘው እንደጠፉ ከአሰልጣኞቹ መረጃ እንዳገኘና አትሌት ዱሪቲም የፓስፖርቷን ኮፒ ለአዲዳስ ኩባንያ የኮንትራት ስራ አስኪያጅ ለመላክ እንደምትፈልግ ለአሰልጣኞቿ ጥያቄ ማቅረቧንና አሰልጣኞቹም የቡድኑ አባላት ፓስፖርት የሚገኝበትን ክፍል ቁልፍ እንደሰጧት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አሰልጣኞቹ፤ አትሌቶቹ ከጠፉ በኋላ ፓስፖርታቸውን ካስቀመጡበት እንዳጡት ተናግረዋል ያለው ዘገባው፤ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባከናወነው ቀናትን የፈጀ ፍለጋ አትሌት ዘይቱናን በዋሽንግተን፣ ሌሎቹን ሶስት አትሌቶች ደግሞ ቤቨርተን ውስጥ እንዳገኛቸው አስረድቷል፡፡ አትሌቶቹ በአሜሪካ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩም ሆነ ቀጣይ ዕጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ምንም አይነት መረጃ አለመስጠቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
No comments:
Post a Comment