አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራና ሪፖርቱን እንዲያቀርብ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ባለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ አድርጎ አቶ በላይ ፈቃዱን በድጋሚ የፓርቲው ፕሬዘዳንት አድርጎ መርጧል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ የሁለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱን ተከትሎ አንድነት በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያደርግ ፓርቲው ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የመላው ኢትዮጵ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ም እንዲሁ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ምርቻ ቦርድ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አድርጎ አቶ ማሙሸት አማረን ፕሬዘዳንት አድርጎ መምረጡ ቢታወቅም፤ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ድርጅቱ ድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሉለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ መኢአድ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሰጠውን ትዕዛዝና ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለውና በድጋሚም ጠቅላላ ጉባኤ እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡
መኢአድና አንድነት ለሁለተኛ ጊዜ ጥር 3 ቀን 2007 ኣ.ም. ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲታዘብ ህጉ በመደንገጉና ፓርቲዎቹ በደብዳቤ ጥሪ ቢያደርጉለትም ምርጫ ቦርድ በሁለቱም ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተወካዩን አለመላኩ ታውቋል፡፡
በተለይ አንድነት ፓርቲ ድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠራ ይፋ ከማድረጉ በተጨማሪ “ይህ በማን አለብኝ ሰሜት የተሰጠ ውሳኔ ሳይታረም ቢቀርና ገዢው ፓርቲ ያለምንም ጠንካራ ተቀናቃኝ ብቻውን ሮጦ ብቻውን እንዲያሻንፍ የሚያደረግ ተቋማዊ ሴራ ቦርዱን በታሪክ ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ዘላቂ ሰላም ላይ ለሚፈጠረው አደጋ ቦርዱ ከተጠያቂነት እንደማይድን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡” ብሏል፡፡
የፓርቲውን ሙሉ መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡-
የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳይፈጠር የምርጫ ቦርድ ታሪካዊ ወንጀል እየፈፀመ ነው፡፡
———-
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
————————-
የአንድነት ፓርቲ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲፈጠር በምንም መለኪያ በገለልተኝነት የማንጠብቃቸውን የዲሞክራሲ ተቋማት በተግባር ለመፈተን እንዲቻል የሁለት ሺ ሰባት ምርጫን በሁሉም ሂደቶች ህዝቡን በማሳተፍ እንደሚወዳደር እና ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ እና የኢህአዴግ አገዛዝ የመጨረሻ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ስንወስን እነዚህ ተቋማት ገለልተኝነታቸውን አረጋግጠው ታሪክ የሚሰሩበት እድልም ያገኛሉ የሚል ተሰፋ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ይህን እድል ከመጠቀም እና በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ከመወጣት ይልቅ ለገዢው ፓርቲ ያለውን ወገንተኝነት በምርጫው ሂደት ዋዜማ በይፋ እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ አሁንም ቦርዱ ወሰነ ተብሎ በሚዲያ የተገለፀው እንዲሁም ለፓርቲያችን በፅሁፍ የተሰጠው “በአስራ አምስት ቀን ውስጥ በጋራ ጉባዔ አድርጉ” የሚል ትዕዛዝ፤ ቦርዱ በተደጋጋሚ ፓርቲያችንን ደንብ እንዲያከብር እየጠየኩ ነው በማለት ከደንብ ውጭ እንድንሰራ የአዛኝ ቂብ አንጓች ሆኖዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ የመጥራት ኃላፊትን ያለበት የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ወይም ደግሞ በአባላት ጥያቄ የጠቀላላ ጉባዔ አባላትን አንድ ሶስተኛ ፊርማ አስባስበው በኦዲትና ኢንስፔክሽን ትዕዛዝ መሆኑ በግልፅ እየታወቀ ከፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ ውጭ በ15 ቀን ውስጥ ጉባዔ ጥሩ የሚል ትዕዛዝ፤ ቦርዱ ከገዢው ፓርቲ ጎን ተሰልፉ እየተጫወተ አንድነትን ከጫወታ ለማስወጣት ካለሆነ ሌላ ምንም ትርጉም ልንሰጠው አንችልም፡፡ ይህ ደግሞ ቦርዱ እየሰራ ያለውን ታሪካዊ ወንጀል ይፋ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ በማን አለብኝ ሰሜት የተሰጠ ውሳኔ ሳይታረም ቢቀርና ገዢው ፓርቲ ያለምንም ጠንካራ ተቀናቃኝ ብቻውን ሮጦ ብቻውን እንዲያሻንፍ የሚያደረግ ተቋማዊ ሴራ ቦርዱን በታሪክ ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ዘላቂ ሰላም ላይ ለሚፈጠረው አደጋ ቦርዱ ከተጠያቂነት እንደማይድን ለማስታወስ እንወዳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ የሰላማዊ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ህዝቡን የስልጣን ባለቤት የማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ ሳምንታትም በመንግሰትና በቦርዱ ላይ ጫና ማሳደሩን እንደሚቀጥልበት እያረጋገጥን አንድነት ፓርቲ ወደ ህገወጥነት የሚወሰደውን “የጋራ ጉባዔ” አካሂዱ የሚለው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የማንቀበለው መሆኑን ለመላው አባላትና ደጋፊዎች ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
ጥር 8 ቀን 2007
ድል የህዝብ ነው!!!
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)