የጥምቀት በዓል መድረሱን ተከትሎ ውጥረት አለ፤ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ከሥላሴ በዓል ላይ ተባረሩ
ጥር ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዛሬ ጥር 7/2007 ዓ.ም የዓመቱን የሥላሴ በዓል ለማክበር አራት ኪሎ የሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የተገኙ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርት በመልበሳቸው በፖሊስ መባረራቸውን ነገረ- ኢትዮጰያ ዘግቧል፡፡
ፖሊስ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ የተጻፈበት ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱትን ወጣቶች ቲሸርቱን እንዲያወልቁ ሲጠይቅ ወጣቶቹ አናወልቅም በማለታቸው ከበዓሉ እንዳባረራቸው የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ ከተባረሩት ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡትንና የሚወጡትን ምእመናን በማስተባበር ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን ፤ ወጣቶቹ -ይታሰሩ፤ አይታሰሩ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለጥምቀት በዓል ሰማያዊ ቲሸርት ያዘጋጁትን የጃንሜዳ እና አካባቢው የጥምቀት በዓል አስተባባሪዎችን በመሰብሰብ፣ ወጣቶች ያዘጋጇቸውን ሰማያዊ ቲሸርቶች በዓሉ ላይ እንዳይለበሱ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
በፖሊሶችና በደህንነቶች ተደጋጋሚ ጫና የጃንሜዳ አካባቢ ወጣቶች ያዘጋጁትን ሰማያዊ ቲሸርትና በቲሸርቱ ላይ ያጻፉትን ጥቅስ መቀየራቸውን ሲናገሩ፤ በአንጻሩ የፈረንሳይና ቤላ አካባቢ ወጣቶች፤ << ሰማያዊ ቲሸርታችንን አንቀይርም!>> በሚል አቋማቸው መጽናታቸው ታውቋል፡፡
ትናንት ጥር 6 ቀን የአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶችና ወረዳዎች ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች፤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባደረጉት ስብሰባ፤ የየካ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› ሲሉ ሪፖርት ማቅረባቸውን የስብሰባው ተሳታፊዎች ለጋዜጣው ገልጸዋል፡፡
ትናንት ጥር 6 ቀን የአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶችና ወረዳዎች ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች፤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባደረጉት ስብሰባ፤ የየካ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› ሲሉ ሪፖርት ማቅረባቸውን የስብሰባው ተሳታፊዎች ለጋዜጣው ገልጸዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፦ ‹‹ደህንነት፣ ፖሊሶችና ካድሬዎች እያንዳንዱን የህዝብ እንቅስቃሴ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በማገናኘት ወቀሳ የሚያቀርቡት፤ ህዝብ ውስጥ ብሶት እንዳለ እና ሰማያዊም የህዝብን ብሶት እንደሚያሳማ ስለሚያውቁ፣ ከምንም በላይ ገዥው ፓርቲ የራሱን ጥላ የማያምንበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ ነው›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ባነሱባቸው ጊዜያት ሁሉ ገዥው ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲን ‹‹የሙስሊም ፓርቲ ነው›› የሚል ሀሰተኛ ወሬ ሲያሰራጭ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ <<አሁንም ፓርቲውን ከእያንዳንዱ የህዝብ እንቅስቃሴ ጋር እያገናኘ ቢበረግግ አያስገርምም>> ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment