በመጪው የጥምቀት በዓል ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርቶችን መልበስ አትችሉም ተባሉ፤
ጥር ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቲሸርቶቹ ላይ የሚያሳትሟቸውን ሀይማኖታዊ ጥቅሶችም በራሳቸው መምረጥ እንደማይችሉ ተነገሩ። ድርጊቱ የግል የማመን መብታችንን የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ ሀይማኖታችንንም መድፈር ነው ያሉ ወጣቶች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
ፖሊሶች ከትናት ታህሳስ30ቀን ጀምሮ በ አዲስ አበባ የተለያዩ ሰፈሮች በመንቀሳቀስ ወጣቶች ለመጪው የከተራ እና የጥምቀት በዓል ሰማያዊ-ቲሸርት መልበስ እንደማይችሉ፣ እንዲሁም በቲሸርቶቻቸው ላይ የሚያሳትሟቸውን ሀይማኖታዊ ጥቅሶች ፓሊሶች እስከሚነግሯቸው ድረስ በራሳቸው ፍላጎት ማጻፍ እንደማይችሉ በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን የቀበና፣ የምኒልክና የፈረንሳይ ሌጋሲዮን ወጣቶች ለኢሳት ገለጹ። ወጣቶቹ ሰማያዊ ቀለም ያለው ቲ-ሸርት መልበስ አትችሉም የተባሉበት ምክንያት በግልጽ ባይነገራቸውም፤ ጉዳዩ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ተናግረዋል።
መቶ መቶ ብር በማዋጣት ለበዓሉ የምንለብሰውን ቲሸርት እያሰራን በምንገኙበት ወቅት መንግስት የምንለብሰውን ቲ-ሸርትና በቲሸርታችን ላይ የምናጽፈውን ጥቅስ እኔ ነኝ የምመርጥላችሁ ማለቱ ዓይን ያወጣ አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን ለምእመናን ያለውን ንቀትም ጭምር የሚያሳይ ነው ብለዋል-ወጣቶቹ። ፖሊሶች ከትናንት ጀምሮ ቅስቀሳ እያደረጉ ቢሆንም፤ የየሰፈሩ ወጣቶች ሊቀበሏቸው አልቻሉም። ይልቁንም በፖሊሶቹ ቅስቀሳ የተበሳጩ ወጣቶች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ሂጃብ መልበስ በመከልከሉ በርካታ ሙስሊሞች ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደሚገኙ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment