ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ከውንጀላ እንዲቆጠብ ጠየቀ
• ይቅርታ ጠይቅ መባሉ ህገ-ወጥ መሆኑን ገልጾአል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታህሣሥ 28/2007 ዓ.ም ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ህገ-ወጥ ተግባራት›› እየፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ ለጻፈው ደብዳቤ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በፃፈው መልስ ምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ውንጀላቸው ህገ-ወጥ በመሆናቸው ቦርዱ ከውንጀላዎች እንዲቆጠብ ጠይቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ ፓርቲ ህጋዊ እውቅና ሳያገኝ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ፣ ቦርዱ ያዘጋጃቸውን ስብሰባዎች ረግጦ ወጥቷል፣ ከቦርዱ እውቅና ውጭ ፓርዎቹን እያስተባበረ ነው በሚል ውንጀላ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡፡ ሆኖም ሰማያዊ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ በተሻሻለው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወር ውስጥ ፓርቲዎች ላቀረቡት የእውቅና ጥያቄ መልስ ካልሰጠ ማመልከቻውን ያቀረበው ፓርቲ እንደተመዘገበ እንደሚቆጠር እና ሰማያዊ ፓርቲም ይህን ህጋዊ መሰረት ተጠቅሞ ህጋዊነቱን እንዳወጀ በደብዳቤው የገለጸው ፓርቲው ‹‹ድርጊታችን ህጋዊ ስለነበር ቦርዱ የህጋዊ እውቅና እና የምስክር ወረቀት ከመስጠት ውጭ በወቅቱ ምንም አይነት ውንጀላ እና ክስ አላቀረበም›› ሲል የአሁኑ ውንጀላ መሰረተ ቢስ መሆኑን ገልጾአል፡፡
ቦርዱ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በተለያዩ አፍራሽ ተግባራት ውስጥ እየተሰማራ ይገኛል›› በሚል በተለያዩ ጊዜያት ቦርዱ ያዘጋጃቸውን ስብሰባዎች ለመበተን ሙከራ አድርጓል፣ ጥሎም ወጥቷል በሚል ለቀረበበት ውንጀላም ፓርቲው ቦርዱ ባዘጋጃቸው ስብሰባዎች አጀንዳዎችን አቅርቦ በቦርዱ በተደጋጋሚ ውድቅ እንደተደረገበት ገልጾ ቦርዱ ‹‹የእኔን አጀንዳ ስሙኝ›› በሚልባቸው ስብሰባዎች ሙሉ ጊዜ መሳተፍ ግዴታም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበረበት ገልጾአል፡፡ ‹‹ባላመንባቸው አጀንዳዎች ላይ ያለመሳተፍ ህጋዊ መብታችን ነው›› ያለው ፓርቲው ወደፊትም ቢሆን ቦርዱ በተመሳሳይ አቀራረብና ይዘት የሚቀጥል ከሆነ ስብሰባዎችን እየጣለ እንደሚወጣ ገልጾአል፡፡
ቦርዱ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ከቦርዱ እውቅና ሳያገኝ ትብብር የሚባል አደረጃጀት መስርቶ ህገ-ውጥ እንቅስቃሴ አድርጓል›› በሚል ላቀረበው ክስም በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝባ አዋጅ 573/2000 32፣ 34ና 35 ውህደት፣ ቅንጅትና ግንባር ካልሆነ በስተቀር ፓርቲዎች በሚያግባቧቸው ጉዳዮች ተባብረው ሲሰሩ የምርጫ ቦርድ እውቅናን መጠየቅ እንደማይጠበቅባቸው ገልጾ፣ ቦርዱ በፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ህጋዊ መብትን እየተጋፋ መሆኑን አውቆ ከእንደዚህ አይነት ውንጀላዎች እንዲቆጠብ ጠይቋል፡፡
በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ ይጠይቅ›› ብሎ ያቀረባቸው ክሶች መሰረተ ቢሶችና ህጋዊ መሰረት የሌላቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም ብሏል፡፡ ‹‹ይህ አይነት የይቅርታ ጠያቂና ይቅርታ አድራጊ ግንኙነት ለምርጫ ቦርድ በህግ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት ውጭ በመሆኑ የቦርዱና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ ግንኙነትን ያልተከተለና ተቀባይት የሌለው መሆኑን እንገልጻለን›› ሲል ይቅርታ ጠይቅ መባሉ ህገ-ወጥ መሆኑን ገልጾአል፡፡
No comments:
Post a Comment