Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, January 3, 2015

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ ኮሚሽኑ ጉዳት እያደረሰብኝ ነው አሉ

f0c5f85042bfe6951cd8168ec96f155e_L
  • 2409
     
    Share
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በምርመራ ወቅት ተፈራርመው የተረካከቡበትን ሰነድ (ቨርቫል) ሊሰጣቸው ባለመቻሉ፣ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት ታኅሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. አመለከቱ፡፡
አቶ ወልደ ሥላሴ ክሱን እየመረመረው ላለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እንደገለጹት፣ ተጠርጥረው በኮሚሽኑ መርማሪዎች ሲያዙ ቤታቸው ሦስት ጊዜያት ተፈትሿል፡፡ የተገኙ ማስረጃዎችንም በምስክሮች ፊት ተፈራርመው ለመርማሪ ቡድኑ አስረክበዋል፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴ የተመሠረተባቸውን ክስ እንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሠረት መከላከያ ምስክሮቻቸውን ለማሰማት ማስረጃውን ከኮሚሽኑ ሲጠይቁ፣ የተሰጣቸው መጻሕፍት የተቆጠረበት መረካከቢያ ሰነድ (ቬርቫል) ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹን ሲጠይቁ የኤግዚቢት ኦፊሰሩ ሥልጠና ስለሆኑ ስልክ እንደሚደውሉላቸው ከመገለጽ ባለፈ ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመሰማታቸው በፊት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ያስታወሱት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ሰነዱ እንዳልተሰጣቸውና እህታቸው ትርሐስ ወልደ ሚካኤል እናቷን ልትጠይቅ መጥታ በመታሰሯ አብራቸው እየተጎዳች መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ከሐምሌ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለዘጠኝ ጊዜያት የፌዴራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) ኤግዚቢት ክፍል በመሄድ ሦስት ጊዜያት ዳይሬክተሩን፣ ስድስት ጊዜያት ደግሞ የተለያዩ ኃላፊዎችን ማነጋገራቸውን የገለጹት የአቶ ወልደ ሥላሴ ጠበቃ፣ በወቅቱ የኮሚሽኑ መርማሪ የነበሩት ግለሰብ እስካሁን እንዳላስተላለፉት እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
መርማሪው አይደለም ለበርካታ ወራት ለጊዜያዊ ምርመራ ሲወጣ እንኳን፣ ለምርመራ መውጣቱን ገልጾ ለሌላ መርማሪ አስተላልፎ መውጣት እንደነበረበት የተናገሩት ጠበቃው፣ እንዴት ወደ ኮሚሽኑ ንብረት ክፍል ሊያስተላልፉት እንዳልቻሉ እንዳልገባቸው ገልጸዋል፡፡
በቂ ልፋት ማድረጋቸውንና ፍርድ ቤቱም ማዘዙን ያስታወሱት ጠበቃው፣ ፍርድ ቤቱ ሁሉም የተሟላ መረካከቢያ ሰነድ እንዲቀርብ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ኃላፊነት ስላለበት የተሟላና ኦርጂናል የሆነ የተረካከቡበትን ሰነድ እንዲያስረክባቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የእኛ መረካከቢያ ሰነድ ከኮሚሽኑ ውጪ ለምን በመርማሪ እጅ ይቀመጣል?›› በማለት የጠየቁት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ ‹‹ሰነዱ እከሌ ጋ ነው፣ እንትና ጋ ነው፤›› የሚለው መመላለስ እየጎዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የድምፅ (ኦዲዮ)፣ የምስል (ቪዲዮ)፣ የፒሲ፣ የአይፓድና የአይፎን ማስረጃዎችን መርማሪዎቹ መውሰዳቸውን ያስረዱት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ ሌላም ተጨማሪ የሚያስፈልጋቸው ሰነድ በቤታቸው ውስጥ እንዳለ ገልጸው፣ ተፈቅዶላቸው በአጃቢ ኼደው እንዲያመጡ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀዋል፡፡
ወንድማቸው አብሯቸው መኖሩንና ተከራይቶ የወጣው ሊያገባ ሁለት ወር ሲቀረው እንደነበር ጠቁመው፣ እሳቸው ጋ የነበረው ሰነድም በመርማሪዎቹ እንደተወሰደ ገልጸዋል፡፡ የእህታቸውም አብሮ መወሰዱን አክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተፈራረሙበትን ሰነድ የኮሚሽኑ መርማሪ ይዘው እንዲቀርቡና ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱ አዟል፡፡ መርማሪው ለምን እስካሁን ሊያስረክቡ እንዳልቻሉና የምርመራ ሒደቱ ምን ይመስል እንደነበር ዛሬ ቀርበው እንዲያስረዱም አዟል፡፡ ለኮሚሽኑ ያስተላለፉት ካለና በእጃቸው ያለውንም እንዲያቀርቡ ታዟል፡፡ ሦስት ጊዜ መፈረማቸው በተጠርጣሪው ስለተገለጸ ቬርቫሉን መርማሪው ይዘው ይቅረቡ በማለት ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials