ኢሳት ዜና :- መንግስት በጋምቤላ ክልል በጎደሬ ወረዳ ከመጋቢት እስከ ጳጉሜ በነበሩት ግጭቶች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ12 አይበልጥም በማለት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቢቆይም፣ አቃቢ ህግ የክልሉን ባለስልጣናት ለመክሰስ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ 79 ሰዎች መገደላቸውን ፣ 273 ቤቶች መቃጠላቸውን ከ13 ሺ በላይ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውን ገልጿል።
አንዳንድ ወገኖች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠሩ ሲገልጹ፣ ኢሳት 60 ሰዎች መገደላቸውን የሞአቾችን ስም ዝርዝር ይፋ በማድረግ ዘገባ አቅርቦ ነበር።
አቃቢ ህግ መንግስት አምኖ የሾማቸው የክልሉ ባለስልጣናት ግድያውን እንዳስፈጸሙና ግጭት እንዲነሳ እንዳደረጉ በክስ ቻርጁ ላይ አምልክቷል። የክልሉ ልዩ ሃይል አዛዥ አቶ ያእቆብ ሸራተንና የመዠንገር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤ ራጃን ጨምሮ 35 የክልሉ ባለስልጣናት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የክልሉ ባለስልጣኖች በሚጤ ህዝቡን ሰብስበው ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የመጡ ሰዎች የእርሻ ቦታቸውንና የቡና ተክላቸውን ለክልሉ ተወላጆች እንዲያካፍሉ፣ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን ከክልሉ እንዲወጡ ቅስቀሳ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተመልክቷል።
የግጭቱ መነሻ በአካባቢው የሚታየው መሬት ወረራ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ በዚህ በኩል ተጠያቂ የሆኑ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ለፍርድ አለመቅረባቸው የፍርድ ሂደቱ ተአማኒነት እንዲያጣ አድርጎታል። የቀድሞ የህወሃት አዛዦች የአካባቢው መሬት በስፋት እየቀሙና ነዋሪውን እያፈናቀሉ መሆናቸው በተጨባጭ ማስረጃ ቢረጋገጥም እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ ሳይሰወድባቸው መቅረቱ በዜጎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ መሆኑን አዲስ አበባው ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በመጪው ጥር አጋማሽ የክሱን ዝርዝር ለማዳመጥ ቀጠሮ ሰጥቷል።
No comments:
Post a Comment