ደቡብ ኦሞ ውስጥ በአርብቶ አደሮችና በፖሊስ መካከል ግችት ተቀስቅሶ የነዋሪዎችና የፖሊሶች ህይወት ጠፋ፤ ግጭቱና ውጥረቱ ሊቆም አልቻለም።
ጥር ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ኦሞ ዞን አመር ወረዳ- ላላ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ አርብቶ አደሮችና- በፖሊስ መካከል ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ነፍስ መጥፋቱን ነገረ ኢትዮጰያ ዘገበ፡፡
ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ትናንት ጥር 7/2007 ዓ.ም <<አርብቶ አደሮች ማጎ ፓርክ ገብተው አውሬ ገድለዋል>> በማለት ፖሊስ- አርብቶ አደሮቹ ገዳዩን አሳልፈው እንዲሰጡት በጠየቀበት ወቅት ነው ግጭቱ የተነሳው።
በአርብቶ አደሮችና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ከሁለቱም ወገን የሰው ህይዎት መጥፋቱንና የቆሰሉም እንደሚገኝበት የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ከዞኑ ፖሊስ ሻለቃ ለማ አሸናፊ የተባሉ የፖሊስ ባልደረባ በአርብቶ አደሮች ሲገደሉ፤ የዞኑ የፀጥታና የፍትሕ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጩመሬ የረር፣ እና የዞኑ የፖሊስ አባል የሆነው ወታደር ተሰማ መሰረት ቆስለው ደቡብ ኦሞ ዞን ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም በግጭቱ ምክንያትም ከዲመካ ከተማ ቀይ አፈር ወደ ተባለው ከተማ የሚወስደው እንዲሁም ከቱሚ ወደ ዲመካ ከተማ የሚወስደው መንገድ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተዘግቷል። በአሁኑ ወቅት የዞኑ ዋና ከተማ በሆነው የጅንካ ከተማ እና ዲመካ፣ ቱኒ፣ ቀይ አፈር እና ኦሞራቴ ከተሞች ውጥረት መንገሱን አቶ ግርማ በቀለ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲልም በአካባቢው ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚፈጠሩ ያወሱት ሊቀመንበሩ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ግጭቶች ሲፈጠሩ በባህላዊ መንገድ የሚፈቱ ሆነው ሳለ ፤ መንግስት ባህላቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገባና የአገር ሽማግሌዎችን ሳያናግር በአርብቶ አደሮቹ ላይ እርምጃ በመውሰዱ፤ ታጣቂዎች የሆኑት የአካባቢው አርብቶአደሮች ምላሻቸውን በኃይል እንደገለጹ አስረድተዋል፡፡
‹‹በአብዛኛው ግጭት የሚከሰተው የአካባቢውን የግጭት አፈታት ወደጎን በመተው ችግሩን በኃይል ለመፍታት በሚጥረው መንግስት ነው›› ያሉት አቶ ግርማ የአሁኑ ግጭትም የተነሳው በመንግስት ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ግርማ በቀለ አክለውም ‹‹ችግሩን በኃይል ለመፍታት የሚጥረው መንግስት ተጨማሪ የሰው ነፍስ እንዳይጠፋና ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ አሁንም ከኃይል እርምጃው ተቆጥቦ ችግሩ በአካባቢው የግጭት አፈታት እንዲፈታ ማድረግ አለበት›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ትናንት ጠዋት ላይ የተጀመረው የአርብቶ አደሮችና- የፖሊስ ግጭት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልቆመም።
No comments:
Post a Comment