Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, January 5, 2015

ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ እና የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ፤

ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ እና የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ፤
DSC_0984 DSC_1012
ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ከወራሪ ሃይሎች ጋር ተፋልሞ ድል ያስመዘገበው ለነጻነቱ በሚሰጠው ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ነው። የዚህ ታላቅ ህዝብ ተጋድሎ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ህዝብ የነጻነት ፋና ወጊ ሆኗል።
ይህ ለነጻነት የተከፈለ ትግልና ዉጤቱ እንዲሁ በቀላል ነገር የመጣ አልነበረም። ሁሉም የኢትዮጵያዊያን ልጆች ዘር ሃይማኖት ብሄር ቀለም ሳይለዩ ባንዲት ባንዲራና ባንዲት እናት አገር ኢትዮጵያ ስም ተሰባስበው አንድ ልብ አንድ አላማ ይዘው ስለታገሉ እንጅ። በዚህ ምክንያትም የአገራችን መላው ህዝብ በየትኛዉም ቦታ እራሳቸዉን ቀና አድርገው የሚሄዱ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼዉም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የነጻነት እጦት ዉስጥ ተዘፍቆ ይገኛል። ያ ነጻነት የለመደ ህዝብ !ያ ተባብሮ በሰላም መኖር ልማዱና ባህሉ ያደረገ ኩሩ ህዝብ! ዛሬ ግን በነጻነት እጦት ስር ወድቆ ከአኩሪ ታሪኩ ጋር ወደታች እየሰጠመ ይገኛል። ወያኔ ኢህአዴግ በዘራው መርዝ ምክንያት እርስ በርሱ ተለያይቶና ተፈራርቶ እንደጠላት እየተያየ ይገኛል።
ከሃያ ሶስት አመት በላይ ሰላም አጥቶ ነጻነት እንደተጠማ ኑሮዉን እየገፋ ነው የሚታየው። በህወሃት አገዛዝ እየተንገፈገፈ ቢሆንም ተባብሮ ግን ከላዩ ላይ የተሸከመዉን የመከራ ሸክም ሊያራግፈው ያልቻለው በከፋፋይ ወያኔ መራሽ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ገመድ ተጠፍሮ ስለተያዘ እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል። ለዚህ መፍትሄዉ ደግሞ የተባበረ ትግል እንደሆነ በጽኑ እናምናለን።
የነጻነት እጦት የወለዳቸውና የኢትዮጵያን ህዝብ ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ የሚታገሉ በርካታ ድርጅቶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። የትግላቸው ዉጤት ግን ግቡን አልመታም። ሁላችንም ታጋይ ድርጅቶች ለምን ስንል ራሳችንን የምንጠይቅበት ወቅት ላይ እንዳለን የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ ያምናል። የዚህ ጥያቄ መፍትሄ ኣቅጣጫ ደግሞ ወደ አንድነት የሚወስደን ይሆናል። ያለ አንድነት የቱንም ያህል ብንታገል የምንፈልገዉን ዉጤት ልናመጣ እንደማንችል ያሳለፍናቸው የትግል ጊዜያቶች አሳይተዉናል።
ይህን የተገነዘበው የኢትዮጵያ ህዝብ ኣርበኞች ግንባር ዘብ\EPPFG\ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ /EPUM/ ጋር በጋራና በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሷል። ታህሳስ 20 –2014 በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ አምስተኛ አመት የምስረታ በአል ላይ የሁለቱ ድርጅቶች ባንድ አመራር ጥላ ስር መጠቃለላቸው ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ኣርበኞች ግንባር ዘብ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ልኡል ቀስቅስ የዉህደቱን አስፈላጊነት አስመልክተው የሚከተለዉን ብለዋል፦ «ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላም ዴሞክራሲና ልማት ሰፍኖ ማየት የምንሻ ሁላችንም አገር ወዳድ የትግል ድርጅቶች እስካሁን ባካሄድናቸው የትግል እንቅስቃሴዎች የምንፈልገዉን ዉጤት ማምጣት አልቻልንም። ለዚህም ዋናው ምክንያት ተባብረን አለመታገላችን ነው። ይህም ለወያኔ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል። ካሁን በኋላ ግን አካሄዳችንን ቆም ብለን አይተን በመተባበር አምባገነኑ ስርዓት እንዲወገድ ማድረግ መቻል አለብን። ከዚያ በተረፈ ምርጫ በመጣ ቁጥር የምናደርገው እንቅስቃሴና የተናጠል ትግል የትም እንደማያደርሰን ልንገነዘብ ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብና የኢትዮጵያ አንድነት ንቅናቄ ያደርጉት ዉህደት ፈር ቀዳጅ ነው» ብለዋል።
በዉህደቱ ላይ የተገኙት የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ /EPUM/ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ጥላሁን ገላው በበኩላቸው በዛሬው እለትም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ እና የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። ስለዚህ በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ጋራ አብሮ የመስራት አላማ እንዳላቸው ያረጋገጡት የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ንቅናቄ ሊቀ መንበር ሌሎች ድርጅቶች፣ ቡድኖች፣ ግለሰቦችና በብሄር ደረጃ የተደራጁ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ወቅቱ ስለሚያስገድድ በጥምረት ለመስራት ከተስማሙት ድርጅቶች ጋር ለመስራት እንዲመጡ ጥሪ አድርገዋል።
በመላው አለም የምትገኙ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያን የሁለቱን ድርጅቶች ዉህደት ተገንዝባችሁ ከጎናችን እንድትቆሙና አስፈላጊዉን ትብብር እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment

wanted officials