አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ውህደት አድርጎ አንድ ከሆነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ አርበኛ ታጋዮችን ማስመረቁ ተሰማ::
አርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮቹን በኤርትራ ያስመረቀው ያለፈው እሁድ ግንቦት 2 ነው:: ከኤርትራ ለዘ-ሐበሻ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ኤርትራ በመግባት አርበኞች ግንቦት 7ን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ:: የምርቃቱን ፎቶዎች ይመልከቱ::
የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከውህደቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አርበኛ ታጋዮች ከትናንት በፊት እሁድ ግንቦት 2 2007 ዓ.ም ደማቅና ታሪካዊ በሆነ ስነ-ስርዓት አስመረቀ፡፡
እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመጀመሪያ ዙር ተመራቂ አርበኛ ታጋዮች ለሦስት ተከታታይ ወራት የተሰጣቸውን የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና እንዲሁም የመረጃና ደህንነት ስፋትና ጥልቀት ያላቸውን ትምህርቶች በመውሰድ በብቃት የተወጡና በተግባር የተፈተኑ መሆናቸውን የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አርበኛ ታጋይ ተስፋሁን ተገኘ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡
አርበኛ ታጋዮች በተመረቁበት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የሌሎች ደርጅቶች አመራሮችና ልዩ ልዩ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አርበኛ ታጋይ ማዕዛው ጌጡ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ታጋዮች ከውህደቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ እንደሆኑና ነባሩን ሰራዊት ሲቀላቀሉ ተረክበው በረሃ የወረዱበትን ታላቅ የህዝብ አደራ በማናቸውም የነፃነት ትግል ሜዳ ላይ ሙሉ በሙሉ መወጣት ስለመቻላቸው ታላቅ ዕምነት እንዳላቸውና እንዲሁም የህወሓት አገዛዝ ግብአተ መሬት መቃረቡንም ጭምር ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ወታደራዊ መምሪያ ዋና ኃላፊ አርበኛ ታጋይ ኮማንደር አሰፋ ማሩም በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ የህወሓት አገዛዝ ህዝባዊነትና ወታደራዊ አቅም እየተሸመደመደ በእጅጉ እየተዳከመ ባለበት ሁኔታ በተቃራኒው አርበኞች ግንቦት 7 ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ ወታደራዊ ጡንቻውም እየፈረጠመ የመጣ መሆኑን፤ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ አንገቱን የደፋው ህዝብ አለንላችሁ ተብሎ ቀና እንዲል የሚደረግበት ጊዜ መድረሱን እና ከእንግዲህ ወዲህ ማናቸውም ምድራዊ ኃይል አርበኞች ግንቦት ሰባትን ፋጽሞ ሊያቆመው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment