Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, May 9, 2015

አደራጅተው ገደሉን። ተደራጅተን ብንገድልስ? (ከ አብርሃም ዘታዬ)





                               አደራጅተው ገደሉን። ተደራጅተን ብንገድልስ? (ከ አብርሃም ዘታዬ)

በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ከደረሰብን ሃዘን ሳናገግም በሜዲትራንያን ባህር የሰጠሙ ወገኖቻችንን መርዶ ተረዳን። በሃገር ቤት ከድሮም ጀምሮ በተናጥልም በጅምላም መጨፍጨፋችንም አላቆመም። ባለቅኔው “ሞትና የላሊበላ ህንጻ ሁልጊዜ አዲስ ነው” ብሎ እንደተቀኘው ስለ አዲሱ ኣሟሟታችን እንጉርጉሮ እናውጣለት ከተባለ በሰፈር ተደራጅተን እየሞትን ነው። በሊቢያ ሰማዕትነት ከተሰዉት ውስጥ አምስቱ አብሮ አደጎች በመደዳ ቤታቸው የሚገኘው ቂርቆስ ሰፈር አዲስ አበባ ነው። ይሄው ሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ ሰጥመው ከሞቱት ደግሞ አስሩ የአንድ ሰፈር በተለምዶ መርካቶ አባኮራን ሰፈር ከሚባለው የተሰደዱ ናቸው፡፡ ልጆቻቸው ተደራጅተው እንደሞቱ ወላጆቻቸውም ተደራጅተው ለቅሶ ተቀምጠዋል።

በስደት ሃገር በጅምላ መሞታችን አዲስ ነገር ቢመስልም ገዳዮቻችን በሃይማኖት ወይ በሰፈር ታርጌት አድርገው የገደሉን ቢመስልም ከጥንት ጀምሮ ያለን የዕድር ባህል አሰባስቦናል።ኢትዮጵያዊ የሃዘን ስሜት አንድ አድርጎናል። ለተረኞቹ አባኮራን ሃዘንተኞች ቂርቆሶች እዝን ይዘው መጥተዋል። ከወለጋ ሄዶ ወይ ከትግራይ ሄዶ የሞተውን ቤት ሆነ የሌሎቹንም ቤታቸውን እየፈለጉ ከምስራቅም ከደቡብም የሃገሪቱ ክፍሎች እየተጓዙ ሳይቀር መላ ኢትዮጵያውያን ለቅሶ ደርሰዋል።ያልቻሉ ሻማ አብርተዋል።ቁጭታቸውን ገልጸዋል።በእርግጥ ሁላችንም ሀዘን ላይ ነን። የነሱ ለቅሶ ብለን ጣታችንን የምንቀስር ወይም ከንፈራችንን መጥጠን የምናልፍ አይደለንም። አንገታችን የተቀላ ሜዲትራንያን ባህር የሰመጥን እኛም ነን። አሳዳጆቻችን የኑሮ ድህነትና የወያኔ ደህንነት እስካልተወገዱ ድረስ ለቅሶ ሊደርሱን የሚገባ ሁላችንም ቤት ነው።

ግን ራሳችን ለመጽናናት ካልተነሳን የትኛው ሃገር መጥቶ ያበረታታናል? ቱባ የ ዕድር ባህላችን ለለቅሶ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ነጻነት ትግል እናውለው እንጂ። ለማልቀስ እንደተሰባሰብን ወያኔን ለማስለቀስ እንሰባሰብ። በዘር መደራጀትን ሽሽተን ወደሚያሰምጠው ባህር፥ ወደ እሚባላው በረሃ፥ወደ ተሳለብን የአይሲስ ሰይፍ ለመታረድ ከምንነዳ ነጻነት ያሳጣንን አረመኔ ዘረኛ ስርዓት እዛው በአገራችን ሜዳ ተናንቀን ብንጥለው የስደት እና የውርደት ምንጭ የሆነውን ከምንጩ እናደርቀዋለን። 


በዘር በሰፈር በሃይማኖት የከፋፈለን ወያኔማ ሃዘንንም እየነጠለ ይገኛል። በስንት ዘገምተኛነት የቂርቆስን አንድ ቤት የዜና ሽፋን ሰጥቶ ከአስር በላይ ሜዲትራንያን ባህር ሰጥመው ሬሳቸው አበኮራን ሰፈር አዲስ አበባ የገባውን ዝም ብሎታል።  የሊቢያ ሰማዕታትን ስም እንዳወቃችሁት እንዳጮሃችሁት   ሁሉ በሜዲትራንያን ከሰመጡት የተለዩት ሰባቱ የአባኮራን ሙስሊም ወንድሞቻችን ስም እንድሪስ አደም ከሁሉም ቲኒሹ ሲሆን የ 18 አመት ታዳጊ አብዱል ከሪም ዘይኔ 20 አመት ሰኢድ ይመር 22 ነጃ ሳቢር 25 ኑሩ መሀመድ 25 አብዱልጀሊል ወጉ 25 አና አሊ መሀመድ 26 ናቸው። የሊቢያ ሰማዕታትን  ሰፈረተኞች እንዳጽናናን ሁሉ ሜድትራንያን ባህር የሰጠሙትንም ሙስሊም ወንድሞቻችን ሰፈርተኞች መንግስትም እኛም ሳናዳላ እናጽናና። በሊቢያ የሞቱት ዜግነታቸው ይጣራ ያለው ዘረኛ ወያኔ፥የኛን ያህል ያልተቃጠሉት የዚምባቡዌ፥ የማላዊ፥ የአንጎላ፥ የናይጄሪያ ዜጎች መንግስታት በደቡብ አፍሪካ ለደረሰባቸው ጥፋት ካሳ እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ የቀለደብን መሰሪው ወያኔ፤በአረብ ሃገራት ዜጎች ሲበደሉ ሲገደሉ እንደመንግስት ያልታደገው አምባገነን ወያኔ ዛሬ ምርጫ ሲደርስ በአዞ እምባው ሊያባብለን ያምረዋል።በሳውዲ አረቢያ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሃዘን ለመግለጽ ሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ስንሰለፍ እሷን አትንኩብኝ ብሎ ሁሌ ከበዳይ ጎን የሚቆመው ወያኔ ዛሬ የግንቦት ምርጫ ስለደረሰ ሀዘን መግለጫ አደባባይ መውጣት ትችላላችሁ ለቅሶ ማሰማት ግን አትችሉም ይለናል።ለጨፍጫፊው መለስ ዜናዊ እሬሳ የአስራ አምስት ቀን ክብር ሰጥቶ ከሰላሳ በላይ ላለቁት ነፍሳት የአንዲት ቀን ብቻ ለዛውም የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ዲስኩር አደረገው። በዚህችም ቀን የመንግስት ካድሬዎች ባንድ ተደራጅተው ተሰለፉ ሰለሞቱት ሳይሆን “ስለልማት” ለፈለፉ። መፈክር ያሰሙትን አሳፈሱ።


አብዛኛው ሀዘንተኞች ተደራጅተን ሃዘናችንን ወያኔ ላይ መግለጽ አቅቶን አብዮቱን ቀበርነው። ለትምህርት ይሆነን ዘንድ ግን አንድ ፌደራል ፖሊስን አስር ወጣቶች ከበውት ሲመክቱ አይተናል።እንዲህ አይነት አንድ ፖሊስን ለአስር የማገት ኣደረጃጀት በመላው ኢትዮጵያ መለመድ አለበት። ሲቀጥል አስር ሆነን ተቀናጅተን ትናንሽ ፖሊስ ጣቢያዎችንም መማረክ እንችላለን። የዋሁ ገበሬ ሳይቀር በወያኔ አንድ ለአምስት ተጠርንፎ አንዱ ሌላውን የሚሰልልበትን መዋቅር እኛ ለበጎ ብናውለውስ። በዕድር ፥ በዕቁብ፥ በማህበር ላይ ያለንን የመደራጀት ልምድ ለነጻነት ትግል በምስጢር ማዋል አያቅተንም።


የሰሜን አፍሪካ ሀገራት አምባገነን ገዢዎች በህዝባዊ አብዮት የተወገዱት በቱኒዚያ የኑሮ ውድነትን ተቃውሞ ራሱን ባቃጣለ አንድ ሰው ሞት ምክንያትን ተከትሎ ነው። ያሳደደ እና በአይሲስ ወያኔ ያስገደላቸው፤በሃገርቤት በየቀኑ የሚገደሉ ወገኖቻችን ብዛት ቁጭት ከነሱ አብዮት መብለጥ አለበት።ባለፈው አመት የምዕራብ አፍሪካዋን ቡርኪናፋሶ አምባገነን ገዥ ብሌስ ኮምፓወሬን ከስልጣን ያስወገደው የሁለት ቀን ተቃውሞንም አይተናል። በዚህ በያዝነው አመት ደግሞ ሕዝባዊ ማዕበሉ ወደ ምስራቅ አፍሪካዋ ቡሩንዲ አምርቷል።በቀጣይነት ከቡርኪናፋሶ የበለጠ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚል ማንቂያ አባባልና ችሎታ ያለን እኛ ነን።እንኳን ሶሻል ሚዲያዎች ለመገናኛ በዚህ ዘመን ተፈብርከውልን ጥንት አባቶቻችን የውስጥና የውጭ አርበኛ ሆነው በመደራጀት ወራሪ ጣልያንን አባረው ነጻነት አጎናጽፈውናል።ተጠራርተን የሊቢያን በረሃ ለማቋረጥ እንደተነሳን፥ለጉዞው ያሟጠጥነውን ጥሪት በረሃና ባህር ከሚበላብን ያሳደደንን ያሳረደንን ወያኔ ማስወገጃ ማህበር ብናቋቁምበት ወይም ነጻ ኣውጪ ድርጅትን ብንረዳበት ዘላቂ መፍትሄ ነበር አሁንም ይሆናል።

እነሱ ተደራጅተው እንደሚደበድቡን ፥እንደሚያሰድዱን እኛም ተደራጅተን እናሰድዳቸው።


በሀገር ውስጥም በውጭ ሃገርም እኛው የአንድ ቀዬ ልጆች እየሞትን ነው ስለዚህ እኛው ተደራጅተን ገዳዮቻችንን እንከላከል።

ከ አብርሃም ዘታዬ zeabraham@gmail.com







- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/6855#sthash.qi7VvjBT.dpuf

No comments:

Post a Comment

wanted officials