ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን እንዳይታዘብ እንደሚፈልግ ገለጸ
•የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ፓርቲዎችን አነጋግሯል
ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ህብረት 5ኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንዳይታዘብ እንደሚፈልግ ለህብረቱ ታዛቢ ቡድን ገለጸ፡፡ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ ሚያዝያ 26/2007 ዓ.ም በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን በተናጠል በምርጫው ዙሪያ ያነጋገረ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ቡድኑን ያነጋገሩት አቶ ወረታው ዋሴ እና አቶ እምዕላሉ ፍስሃ ህብረቱ ምርጫውን እንዳይታዘብ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡
የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ከአሁን ቀደም በተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች መታዘቡን ያወሱት የሰማያዊ ተወካዮች፣ ህብረቱ በሪፖርቱ ለአምባገነኖች እውቅና ከመስጠት ያለፈ አንዳች እውነታውን የሚያሳይ ትዝብቱን አላስቀመጠም ሲሉ ለታዛቢ ቡድኑ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ህብረቱ የአምባገነኖች ስብስብ ነው›› ያሉት የፓርቲው ተወካዮች፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ተስፋ በማጣት በታዛቢነት እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ህብረት ግን ለአምባገነኖች እውቅና ለመስጠት መምጣቱ በሰማያዊ ፓርቲ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቀደምት ፓን አፍሪካኒስቶች አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት ታግለዋል፤ የአሁኖቹ እውነተኛ ፓን አፍሪካኒስቶች ደግሞ አፍሪካን ከአምባገነኖች ነጻ በማውጣት ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል›› በማለት ለህብረቱ ታዛቢዎች የገለጹት የፓርቲው ተወካዮች፣ በዚህ ረገድ ህብረቱ ተገቢውን ስራ እያከናወነ ነው ለማለት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ጋባዥነት 5ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ በቅርቡ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ህብረቱ በዛሬው ዕለት ያነጋገራቸው ፓርቲዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በውል አልታወቀም፡፡
No comments:
Post a Comment