Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, May 31, 2015

በፓትርያርኩ መቀመጫ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቅርሶች እና ንዋያተ ቅድሳት ጉዳይ ምርመራ እንዲካሔድ ተጠየቀ

Ethiopian_Orthodox_Church_Siege_Addis_Abeba_2


በፓትርያርኩ መቀመጫ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቅርሶች እና ንዋያተ ቅድሳት ጉዳይ ምርመራ እንዲካሔድ ተጠየቀ

  • ታሪካዊው የቅዱስ እንጦንስ ጽሌ በአርተፊሻል ተቀይረዋል ከተባሉት አንዱ ነው
  • የስእለት እና የስጦታ ወርቆች እና የብር ጌጣጌጦች በየመሸታ ቤቱ እየተሸጡ ነው
  • የውጭ ኦዲት እንዲካሔድ በፓትርያርኩ የተሰጠው መመሪያ ተግባራዊ አልተደረገም
  • በየመሸታው አስነዋሪ ሥራ የሚያዘወትሩ ካህናት ለምእመናን መራቅ ምክንያት ኾነዋል
  • የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ ተደርገዋል
(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅጽ 03 ቁጥር 107፤ ቅዳሜ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም.)
st-mary church aa
በምሥረታ ታሪኳ እና በሕገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ድንጋጌ የፓትርያርኩ መንበር በሚገኝባት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በቅርስነት የሚታዩ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት፣ አልባሳት፣ መጻሕፍት እና ልዩ ልዩ ንብረቶች እየተለወጡ እና እየተሸጡ በመጥፋት ላይ ናቸው ያሉ የገዳሟ አገልጋዮች እና ምእመናን ምርመራ እንዲካሔድ ጠየቁ፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ የገዳሙ አገልጋዮች እና ምእመናን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ገዳሟ የበርካታ ንዋያተ ቅድሳትና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ስትኾን ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያን ተሰርቀው በእግዚአብሔር ኃይል የተገኙና ወደ ስፍራቸው እስኪመለሱ ድረስ በአደራ የተቀመጡ ብዙ ንዋያተ ቅድሳትም ያሉባት ነች፡፡
ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ የገዳሟ ንዋያተ ቅድሳትና ታሪካዊ ቅርሳ ቅርሶች ተመርጦ በተመደበው ካህን በየዓመቱ እየተቆጠሩ በጥንቃቄ ተመዝግበው መጠበቅ ሲገባቸው፣ ‹‹የመልካም ሥነ ምግባር አብነት መኾን በተሳናቸው›› አንዳንድ የገዳሟ ሠራተኞች በአምሳላቸው እየተለወጡና እየተሸጡ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገልጧል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተባባሰ መምጣቱ በተነገረው በዚኽ ዓይነቱ ዘረፋ፣ ጥንታውያን ጽሌዎች በአርተፊሻል እንደተቀየሩ፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት እና የወርቅ ጽንሐሕ እንደ ወጡ በጥያቄው ተጠቁሟል፡፡ ‹‹እኔ የማውቃቸው ብዙ ንብረቶች ጠፍተዋል›› ሲል ለኢትዮ-ምኅዳር የተናገረ አንድ የገዳሙ አገልጋይ፣ ድርጊቱ የሚፈጸመው ጥንታውያኑን ንዋያተ ቅድሳት እና ቅርሶች በአሳቻ ጊዜ በማውጣት፣ በዕቃ ማጣርያ እና ሽያጭ ሰበብ እንዲኹም ሰነዶችን በመደለዝ እና በማጥፋት እንደኾነ አስረድቷል፡፡ ጥገና እየተደረገላቸው በቅርስነት ተከብረው ለአጠባበቅ ምቹ በኾነ ዕቃ ቤት ተቀምጠው መጎብኘት የሚገባቸው የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ጨምሮ ቀደምት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የለበሷቸው ካባዎች፣ ቀጸላዎች፣ አክሊሎች፣ መጎናጸፊያዎች፣ መጋረጃዎችና ጽዋዎች በግምጃ ቤቱ ስለመኖራቸው በንብረት ዓመታዊ ምዝገባ እና ቁጥጥር ማጣራት እንደሚያስፈልግ አገልጋዩ በሐዘን ጠይቋል፡፡
የድርጊቱ ዋነኛ ፈጻሚዎች እንደኾኑና የማጣራቱ ርምጃ እንዲካሔድባቸው የተጠየቀው÷ በገዳሙ የቁጥጥር ክፍል ሓላፊ፣ በንብረት ክፍል ሓላፊ እና በቄሰ ገበዙ ላይ ነው፡፡ የሦስቱን ሓላፊዎች ድርጊት የሚያውቁ አንዳንድ የገዳሟ መነኰሳትም ‹‹የድርሻችን›› በማለት ሲጠይቁ እንደሚስተዋሉ የጠቀሱት አመልካቾቹ፣ ‹‹የቢሮ ሥራ እንሰጣቸኋለን፤ የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራውን ወደነበረበት እንመልሰዋለን›› በሚል ሕገ ወጥ አካሔድ እና ጥቅም በማማለል ማባበያ እየተደረገላቸው እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በሚልዮኖች የሚቆጠር የገዳሟ ገንዘብ እና ንብረት በአስተዳደር ሓላፊዎች እና ሠራተኞች መመዝበሩን ተከትሎ በኅዳር ወር አጋማሽ የተቋቋመውየሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ኮሚቴ፣ የስድስት ወራት የሥራ ጊዜው ቢጠናቀቅም በእጁ ያለውን ንብረት አስረክቦ ለመቀየር ዝግጁ ካለመኾኑም በላይ በኮሚቴው የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር እና ቄሰ ገበዙ ተካተውበት ቆጠራው በካሽ ካውንተር አጋዥነት በባንክ ባለሞያዎች ድጋፍ እንዳይቆጠር አባላቱ መቃወማቸው ተመልክቷል፡፡
ኮሚቴው ከምእመናን በስእለት የተሰጡ ንብረቶች በአግባቡ እየተመዘገቡ ግምታቸው ታውቆ በሕጋዊ መንገድ ገቢ እንዲኾኑ በማድረግ በኩልከፍተኛ ድክመት ማሳየቱ የአመልካቾቹ ሌላው ትኩረት ነው፡፡ በተለይም ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲኽ እየተባባሰ በመጣው የንብረት ምዝበራ፣ ከበጎ አድራጊዎች ለገዳሙ የተለገሠ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና ጸሎተ ቅዳሴውን ለብዙኃን ለማስተላለፍ ያገለግላል የተባለ ፕሮጀክተር ተመዝግቦ ገቢ ሳይደረግ በግለሰቦች ወጥቶ መሸጡ ተገልጧል፡፡
በደብዳቤው እንደሰፈረው÷ ከመቶ ኻያ ግራም በላይ የአንገት እና የጣት ወርቆች፣ Aba Woldetinsae Adamuመጠናቸው የማይታወቅ የብር ጌጣጌጦች በደንቡ እና በመመሪያው መሠረት በሕጋዊ ሰነድ ለንብረት ክፍሉ ገቢ ሳይደረጉ መልአከ ብሥራት አባ ወልደ ትንሣኤ አዳሙ በተባሉ የቆጠራ ኮሚቴው አባል በተለያዩ መሸታ ቤቶች መሸጣቸው በዓይን እማኞች ተረጋግጧል፡፡
ከሰማኒያ በላይ ካህናት ባሉበት ገዳም የቃለ ዐዋዲ ደንቡን የሥራ ሓላፊዎች ምርጫ እና የአገልግሎት ዘመን ድንጋጌ በመቃረን ተመሳሳይ ያልኾኑ ሓላፊነቶችን ደራርበው ይዘዋል የተባሉት መልአከ ብሥራት አባ ወልደ ትንሣኤ፣ የልማት ኮሚቴው ለሚያሠራው ኹለ ገብ እና የአገልግሎት ሕንፃ ያለፕሮፎርማ በተፈጸመ ጥራቱን ያልተጠበቀ የብረት ግዥ ተገቢ ያልኾነ ጥቅም (ቢያንስ ከብር 200,000 በላይ) ማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡ የገዳሟ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ያዥ፣ የልማት ገንዘብ ተቀባይ፣ ዕቃ ግዥ እና ንብረት ቁጥጥር ሓላፊ የኾኑት የመልአከ ብሥራት አባ ወልደ ትንሣኤ ስም ከቄሰ ገበዙ አባ ሳሙኤል ቀለመ ወርቅ እና ሌላ ካህንን ጨምሮ ለምንኩስና ሥርዐት በማይስማማ ተግባር በአልባሌ ቦታ ከመገኘት ጋርተያይዞም ተነሥቷል፡፡
መነኰሳቱ፥ ‹ልናጠምቃቸው ነው፤ መበለቶችን መከባከብ ይገባል›› በሚል እና በምግብ አብሳይነት ሰበብ በገዳሙ ቅጽር በሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው የሚገቡ ሴቶችን እስከ መንፈቀ ሌሊት እያቆዩ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ነውር በመፈጸም፤ በየግሮሰሪው ዓምባጓሮ እየፈጠሩ ከአስተናጋጆች ጋራ ለድብድብ በመጋበዝ፤ በስካር ወደ ገዳሙ ተመልሰው እየገቡ ከምእመናን ጋራ በክፉ አንደበት በመመላለስ፤ ከልክ በላይ የጠጡትን በማንቃረር፤ በዘር አንዳንዴም በመንደር እየተከፋፈሉ ቅጽሩን የአሉባልታ እና የአድማ መናኸርያ በማድረግ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ነቅፈው አስነቅፈዋል፤ ክብረ ቤተ ክርስቲያንን ደፍረው አስደፍረዋል ተብሏል፡፡ አዲሱ የገዳሟ ሰበካ ጉባኤ ይህን ለመከላከል የጊዜ ወሰንን ጨምሮ ያወጣው ዝርዝር የመተዳደርያ ደንብ ‹‹ሕጉ እኛን ለመገደብ ነው፤ እስከ ከዛሬ እንደኖርነው እንኖራለን እንጂ ሕግ አያስፈልግንም፤›› ባሉት በሦስቱ መነኰሳት ግንባር ቀደምነት ተግባራዊነቱ መስተጓጎሉ ተዘግቧል፡፡
ከሰማኒያ ዓመታት በላይ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችው ገዳሟ አኹን ያለችበት የቤተ መቅደስ የውስጥ አገልግሎት‹‹መንፈሳዊ ሕይወት በማይታይባቸው እና ሞያዊነት በሚያንሳቸው ካህናት የተነሣ ደረጃዋን የማይመጥን ነው፤›› ይላሉ አመልካቾቹ፡፡የውስጥ አገልግሎቱ እና የክህነቱ ተግባር በቂም በቀል፣ በጥላቻ ለደመወዝ ሲባል ብቻ እንጂ መንፈሳዊነቱ ተጠብቆ እና ሥነ ሥርዐቱ ተሟልቶ እየተፈጸመ አይደለም፤ ከጥምቀት እስከ ጸሎተ ፍትሐት አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለምእመናን መስጠት የካህናቱ ኹሉ ሓላፊነት እንደመኾኑ የተመደቡበትን ተልእኮ በሙሉ ኃይላቸው እና ችሎታቸው ለበላይ ሓላፊ በመታዘዝ ከማከናወን ይልቅ ደጀ ጠኚዎችን እየተኩ በውክልና የሚያስፈጽሙ፤ ‹‹ተረኛው የለም፤ ጊዜው አልፏል›› በሚል ግልጋሎት ፈላጊ ምእመናንን ግብረ ገብነት እና ቅንነት በጎደለው ቃል እየተናገሩ የሚያስመርሩ ካህናት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ አመልካቾቹ፣ ‹‹በአገልግሎት ከአረጀንባት ቅድስት ስፍራ የሰበካዋ ምእመናን እንዲርቋትና ወደ ሌሎች አድባራት እንዲሔዱ ምክንያት ኾነዋል፤›› በማለት ካህናቱን ይወቅሳሉ – በደብዳቤአቸው፡፡
ምእመናንን በሃይማኖት የመጠበቅ ግዴታቸውን የዘነጉት ካህናት፣ ከተጠያቂነት ለመዳን የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን ጨምሮ ቅርበት አላቸው የሚባሉ ሓላፊዎችን መከታ እንደሚያደርጉም ተገልጧል፡፡ የገዳሙን ሀብት እና ንብረት ከመጠበቅ ጀምሮ ለገዳሙ አስተዳደር እና አገልግሎት የበላይ ሓላፊና ተጠሪ የኾኑት አስተዳዳሪው በተጠቀሱት ካህናት እና መነኰሳት ዘንድ ሥልጣን አልባ መደረጋቸው ተነግሯል፡፡
St Marry Bulding comp.
የገዳሟ ያለፉት ስድስት ዓመታት የሒሳብ አያያዝና የንብረት አጠባበቅ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር የልማት ኮሚቴው የበላይ ጠባቂ በኾኑት በፓትርያርኩ ባለፈው ኅዳር ወር የተሰጠው መመሪያ እስከ አኹን ተግባራዊ አለመኾኑ የአስተዳዳሪው ሥልጣን ውሱንነት እና የተጠቀሱት ዋልጌ መነኰሳት የበላይነት መገለጫ ተደርጎ ታይቷል፡፡ በታኅሣሥ ወር አጋማሽ በተመረጠው አዲሱ ሰበካ ጉባኤ ገዳሟ፣ የኻያ በመቶ የሀገረ ስብከት ፈሰስ ውዝፏን በመክፈልና ተቀማጯን ወደ 1 ነጥብ 8 ሚልዮን በማሳደግ የተጓተተው የባለስድስት ፎቅ ሕንፃ ግንባታ እየተፋጠነ ቢኾንም ለውጭ ኦዲቱ ‹‹እየተዘጋጀን ነው›› ከማለት ያለፈ በተግባር ለማስፈጸም አለመቻሉ ታውቋል፡፡
የንብረት እና የቁጥጥር ክፍሎች ሓላፊዎች ከቄሰ ገበዙ ጋራ በመኾን ‹‹አዲሱ ሰበካ ጉባኤ ኦዲት አስደርጎ እኛን ሊያባርረን ነው፤ አንገታችንን እንሰጣለን እንጂ ኦዲቱ አይካሔድም›› በሚል የውጭ ኦዲት ምርመራው እንዳይፈጸም በተለያዩ ስልቶች እየተከላከሉ እንዳሉ ነው የተገለጸው፡፡ ፈቃድ እየጠየቁ ዕረፍት በመውጣት በሥራ ገበታ አለመገኘት የኦዲት ምርመራው እንዳይፈጸም የማስታጎል አንዱ ስልት መኾኑ ተጠቁሟል፡፡
መንበረ ፓትርያርክ በኾነችው በገዳሟ በውስጥ አገልግሎቷ ከሚታይባት በቂ ሞያ እና ቁጥር ያላቸው ካህናት ጉድለት ባሻገር በቢሮ ሠራተኞች ዘንድም ከፍተኛ የዕውቀት ማነስ እና የአቅም ውስንነት እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ለአብነት ያኽል፣ ለኦዲቱ ሥራ የሚያስፈልገውን የሒሳብ ሪፖርት በጥራት እንዲያቀርቡ የሚጠበቁት የሒሳብ ሹሙ የትምህርት ደረጃ ከዐሥረኛ ክፍል ያለፈ አይደለም፡፡ ሰበካ ጉባኤው ለቦታው በዕውቀት የሚመጥን ባለሞያ እንዲላክ ከአንድ ወር በፊት በጉባኤ ወስኖ ሀገረ ስብከቱን የጠየቀ ቢኾንም ክፍተቱ እንዳይደፈንና ‹‹ከእኛ በላይ ሰው የለም›› በሚል ከቢሮ ሠራተኞች ጋር በጥቅም በተቆራኙት ሦስት ካህናት ክፋት እንዳይፈጸም መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡
‹‹ሰበካ ጉባኤው አይጠቅመንም፤ ይውረድልን›› በሚሉ አድማዎች ሳቢያ ሰበካ ጉባኤው አርቅቆ ያቀረባቸው የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ፣ የንብረት እና የግዥ ዝርዝር መመሪያዎቹ÷ ‹‹መተዳደርያ ደንብ፣ ማኑዋል የሚባል ነገር አያስፈልገንም፤ እንዲያስቀሩልንም ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነግረናቸዋል›› በሚሉት ሦስቱ ግንባር ቀደም መነኰሳት የተነሣ ሊሠራባቸው እንዳልቻሉና ተጨባጭ ለውጥ ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት ዕንቅፋት እንደገጠመው ተመልክቷል፡፡ ይኸውም የአድኅሮት አቋማቸው ‹‹ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ቃለ ዐዋዲ እና የሠራተኛ መተዳደርያ ደንብ አለን፤ ሌላ ምንም አያስፈልገንም›› የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሳይተባበሩበት እንዳልቀረ ተጠቁሟል፡፡
the pat and his special sec Nebured Elias
የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ተቆጣጥረው ፓትርያርኩን በየዕለቱ በስሕተት ጎዳና መምራታቸውን የቀጠሉት የመዝባሪዎች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

በገዳሟ ‹‹ሃይማኖት ጎድሏል፤ ግብረ ገብነት ጠፍቷል፤ ምዝበራ ተንሰራፍቷል›› የሚሉት አመልካቾቹ፣ በመጋቢት ወር ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄአቸውን ለማቅረብ ሞክረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይኹንና የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ‹‹ጾም ሲፈታ እንጂ አኹን አይቻልም›› ብለው በማለታቸው ችግሩ እየተባባሰ እንዲሔድ ምክንያት መኾናቸውን በመጥቀስ ጉዳዩ ፖሊስን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት እንዲጣራ ያደርጉላቸው ዘንድ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በበኩሉ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ወደ ፓትርያርኩ ቀርቦ ከተመረጠበት ታኅሣሥ ወር ወዲኽ በአስተዳደር እና በልማት ያከናወናቸውን ተግባራት በሪፖርት ማቅረቡ ዘግይቶ ተሰምቷል፡፡ በተለይም በአሠራር መመሪያዎቹ ዝግጅት ‹‹ከጠበቅኹት በላይ ነው የሠራችኹት›› የሚል ማበረታቻ ከፓትርያርኩ ማግኘቱ ተገልጧል፤ ለተግባራዊነቱ ስለገጠመው ዕንቅፋትም ‹‹በቃለ ዐዋዲው መሠረት ሕግ እና ሥርዐት ተከትላችኹ ርምጃ ከመውሰድ የሚያግዳችኹ ነገር የለም›› የሚል መመሪያ መቀበሉ ተነግሯል፡፡


St Marry Church
የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ስያሜዋን ያገኘችው በ፲፱፻፳፪ ዓ.ም. ስትመሠረት የብፁዓን አባቶች መንበር ስለሚገኝባትና በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ስለምትገኝ መኾኑን ታሪኳ ይገልጻል፡፡ ስፍራው ቀደም ሲል የሥርዐተ ምንኵስና መሥራቾቹ የቅዱስ አባ እንጦንስ እና አባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበት የግብጻውያኑ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ እና ዕጨጌው እንዲኹም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት የሚያደርሱበት በመኾኑ አቡን ቤት እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ በግብጻዊው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ከኢየሩሳሌም መጥቶ በመናገሻ ማርቆስ ተቀምጦ የቆየው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ጽላት እስከገባበት ድረስም ምእመናን አምልኮታቸውን ይገልጹበት ነበር፡፡
ጥር ፳፩ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ትእዛዝ መሠረቱ የተጣለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራው የተጠናቀቀው መስከረም ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ በፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ምክንያት ሌሎች በርካታ ታቦታትም በቤተ መቅደሱ ተቀምጠው እንደነበር ይነገራል፡፡ ገዳሟ የግብጽ ኦርቶዶክስ ካህናት እና የሕንድ ኦርቶዶክስ ካህናት በየራሳቸው ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽሙባት ብቸኛዋ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን ዛሬም በገዳሙ ደቡባዊ አንቀጽ ከክርስትናው ቤት ፎቅ ላይ በመገኘት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡
በሚያዝያ ወር መጨረሻ ለፓትርያርኩ በተጻፈው የገዳሟ ካህናት ደብዳቤ ‹‹በአርተፊሻል ተቀይረዋል›› ከተባሉትና ምርመራ እንዲካሔድ ከተጠየቀባቸው ጥንታውያን ጽላት አንዱ ታዲያ የአበ መነኰሳት ቅዱስ እንጦንስ መኾኑ ነው እየተነገረ የሚገኘው፡፡
HaraTewahdo

No comments:

Post a Comment

wanted officials