ውጤቱ የታወቀው ምርጫ ሊካሄድ የመጨረሻው ሳምንት ላይ እንገኛለን። የኢትዬጲያ ህዝብ የምርጫውን ውጤት አስቀድሞ የገመተው በመሆኑ ለሂደቱ ትኩረት ሳይሰጠው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በዚህ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ተቀምጠን ሂደቱ እንዴት አለፈ ብሎ ለመመርመር ጊዜው ገና ይመስላል። ከዛ ይልቅ በምርጫው እለት ምን ሊሰራ ይችላል የሚለው ላይ አተኩሮ መንቀሳቀሱ የተሻለ ይሆናል። ለጊዜው ሁለት አማራጮች ይታዩኛል።
አማራጭ አንድ: ድምጵ ያለመስጠት፣
ከሚቀርቡት አማራጮች በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችለው በምርጫው እለት ወደ ጣቢያ ባለመሄድ ድምጵ አለመስጠት ነው። ምንም እንኳን ዋጋው ከባድ ቢሆንም የሚያስተላልፈው መልእክት ከየትኛውም አማራጭ የላቀ ነው። መሰረታዊ የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት በተገፈፈበት፣… የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት በተሽመደመዱበት፣… የገዥው መደብን ፕሮፐጋንዳ ብቻ የሚያስተጋቡ ፕሬሶች የፓለቲካ ምህዳሩን በሞሉበት፣ …የብእር አርበኞችና የሀይማኖት ነጳነት ታጋዬች በአሸባሪው የፀረ ሽብር አዋጅ በተከሰሱበት፣ …ገዥውን መደብ በተወሰነ መልኩ ሊገዳደሩ የሚችሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች በፓለቲካ ውሳኔ ተላልፈው በተሰጡበት… ወዘተ ሁኔታ የምርጫ ካርድ ተሸክሞ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የሞራል ጥያቄ ማስነሳቱ የማይቀር ሀቅ ነው።
ስለዚህ ድምጵ የምሰጠው ምን ፈልጌ ነው? ምን ለማትረፍ ነው? ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ችግሮች በእኔ ድምጵ ሊሻሻሉ ይችላሉ ወይ? የሚሉ ቁምነገሮችን በማንሳት ምላሽ መስጠት የዚህ ሳምንት ቁልፍ ጥያቄ ይሆናል።
በመጀመሪያ ምርጫ ተመዝግቦ ድምጵ ያለመስጠት ልምድ ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች ተከስቶ እንደሆነ መመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል። ሩቅ ሳንሄድ የዛሬ አምስት አመት (2002 አም) በተካሄደው ምርጫ መቼም ልቡን ለኢህአዴግ ሰጥቶ የማያውቀው የአዲሳአባ ህዝብ ተግብሮታል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆን አንጋፋው ፓለቲከኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በ2003 አም " ሥልጣን ፣ባህልና አገዛዝ ፣ ፓለቲካና ምርጫ" በሚለው መጵሀፋቸው በግልጵ አመላክተዋል። ፕሮፌሰሩ የምርጫ 2002 ዋና ተዋንያኖች በሚተርኩበት ክፍል በገጵ 156 ላይ የክልሎቹን ህዝብ ብዛት፣ ለምርጫው የተመዘገቡና የመረጡትን በሰንጠረዥ አሳይተዋል። በዚህም መሰረት በአዲሳአባ እመርጣለው ብለው ከተመዘገቡት ውስጥ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ የመረጡት 43•8% ብቻ ናቸው። በሌላ አነጋገር ለምርጫ ከተመዘገቡት 100 ሰዎች ውስጥ 56 ያህሉ አውራ ጣታቸው ላይ ቀለም አላረፈም። ወይም ምርጫ ካርዳቸውን ቀዳደው ጥለዋል።
በማስከተል ድምጵ ያለመስጠት ውጤታማ የሚሆነው በየትኛው አካባቢ ነው? የሚለውን ጥያቄ እንመልከት። ከልምድ በመነሳት የተቃዋሚ ፓርቲ እውነተኛ ታዛቢ በሌለባቸው፣ ገጠራማ አካባቢዎችና እንደ አፋር፣ ሱማሊያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኔሻንጉል፣ ትግራይ የመሳሰሉ ክልሎች ድምጵ ያለመስጠት ብዙም ትርጉም የለውም። በእነዚህ "ተው ባይ" በሌለባቸው አካባቢዎች ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ተለዋጭ ኮሮጆ የመዘጋጀት እድሉ ሰፊ ነው። የማቅለሙም ስራ አስቀድሞ ይጠናቀቃል። የገዥው ፓርቲ ተወዳዳሪዎች የአካባቢው ህዝብ ባጠቃላይ በአስር እጥፍ ተባዝቶ የሚያክለውን ያህል ድምጵ ያገኛሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አሁንም የፕሮፌሰር መስፍን መጵሀፍ ይሆናል። ሁሉም እንደሚያውቀው በምርጫ ህጉ መሰረት አንድ የምርጫ ወረዳ የሚዋቀረው በምርጫ ወረዳው እስከ መቶ ሺህ ህዝብ ( ህጳናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂ በሙሉ) ሲኖር ነው። በማእከላዊ ስታስቲክስ መረጃ መሰረት በኢትዬጲያ ከ15 አመት በታች የሚሆነው ሕዝብ ቁጥር 45•2% ያህል ይሆናል። ይህ ማለት በአንድ ምርጫ ክልል ለመምረጥ እድሜው የደረሰ በሙሉ ተመዝግቧል ቢባል ብዛቱ ከ50 ሺህ በታች ይሆናል። ይህን ታሳቢ አድርገን ጋሽ መስፍን በገጵ 157 ላይ " አስገራሚ የምርጫ ውጤት" በሚል ርእስ የ25 ሰዎች ከመቶ ሺህ በላይ ድምጵ ማግኘታቸውን በሰንጠረዥ አሳይተዋል። ከዚህ ውስጥ ፊልቱ ወረዳ የተወዳደሩት አቶ ኡስማን አለ መላ 368, 211 ፣ ጂጂጋ ምርጫ ክልል አቶ አሊ ኡመር አለሌ 213,288፣ አሁንም ጅጅጋ አቶ አብዱልፈታህ አብድላሂ 246,782 የሚያህል ድምጵ አግኝተዋል። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ድምጵ መስጠትም ሆነ አለመስጠት የሚያመጣው ለውጥ የለም።
( በነገራችን ላይ የእነ ኡስማንን አስገራሚ ውጤት ስመለከት በጭንቅላቴ የሚመጣው አርቲስት ታማኝ በየነ በአንድ ወቅት በአዲሳአባ ስቴዲዬም ያቀረበው ቀልድ ነው። በወቅቱ በጫካ መሽገው ኢህአዴግ ስንት የኢትዬጲያ ወታደሮች እንደገደለ በሬዲዬ የሚናገሩት ፍሬህይወት ( በአሁን ሰአት የአዲሳአባ ፓርላማ እጩ) እና ሴኮቱሬ ጌታቸው ነበሩ። በየቀኑ 50ሺህ፣ 100ሺህ ገደልን የሚለው የእነ ሴኮ ብስራት ያልተዋጠለት ታማኝ " እነዚህ ሰዎች ከነገው ትውልድ ተበድረው ይገላሉ ወይ?" የሚል ቀልድ አንስቶ በታሪክ ተመዝግቦለታል። በንጋታው የሬዲዬ ጣቢያውን የተረከበው ሴኮቱሬ " ታማኝ! ሂሳቡን ስንመጣ እናወራርዳለን" ብሎት ነበር። አወራርደው ይሆን??)
አማራጭ ሁለት: የድምጵ መስጫ ወረቀቱን የተቃውሞ መግለጫ ማድረግ
ይህ አማራጭ ከግለሰብ ደህንነት አንጳር አስተማማኝ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው። ይህን እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉ ሰዎች በአንድ ለአምስት መዋቅር ውስጥ ተጠርንፈው መላወሻ ያጡ ግን ደግሞ ገዥው መደብንም ሆነ ተቃዋሚዎችን ለመምረጥ ፍላጐት የሌላቸው መሆናቸው አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የአንድነት፣ መኢአድና የትጥቅ ትግል አማራጭን የሚደግፋ ግለሰቦች በዚህ ማእቀፍ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ ( በኢህአዴግ ኔትወርክ "C" እና " D" ደረጃ የተሰጣቸው)። በተለይ ባለመምረጣቸው የስራ ዋስትና የማጣት እጣ ፋንታ የሚያጋጥማቸው ነዋሪዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ወረቀቱን የተቃዉሞ መግለጫቸው ቢያደርጉት ይመረጣል።
ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ወረቀቱ ላይ የሚሰፍረው የተቃውሞ መልእክት ምን ይሁን የሚለው ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ በተቻለ መጠን መልእክቱ ወጥ እንዲሆን ማድረግ ነው። በተለይም የቡድን ጥያቄ ያላቸው ማህበረሰቦች የጋራ ፍላጐታቸውን የሚያሳይ የተቃውሞ መልእክት ( ምስልን ጨምሮ) ሊነድፋ ይችላሉ። ለምሳሌ የሙስሊሙን ንቅናቄ የሚመሩ አመራሮች ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት " ፍትህ" ፣ አሊያም " የጨረቃ ምስል" የሚያሳይ እንዲሆን ማድረግ። የኦርቶዶክስ ተከታዬች ሰሞኑን የታረዱ ወንድሞቻችንን ለመዘከርና መንግስት በቤተክርስቲያኗ ላይ የሚያደርሰውን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም " የመስቀል ምልክት" አሊያም ተዛማች ነገሮችን ማድረግ። ለውጥ የሚመጣው በትጥቅ ትግል እንደሆነ የሚደግፋ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ መንገድ ወጥ መልእክት ወይም ምልክት የሰፈረበት ወረቀት ወደ ኮሮጆ እንዲጨምሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ይቻላልም።
No comments:
Post a Comment