ኢህአዴግ በደቡብ ክልል እየተከሰቱ በሚገኙ የ‹‹ብሄር›› ግጭቶች በስተጀርባ ሰማያዊ ፓርቲ አለበት እያለ እየቀሰቀሰ እንደሚገኝና በዚህ ሰበብ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትንም እያሰረ እንደሚገኝ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳትኮ ታዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በተለይም በደራሼ ወረዳ የእርስ በእርስ ግጭት እንደነበር የገለጹት አስተባባሪው ከምርጫው ጋር ተያይዞ ግጭቱ ሆን ተብሎ እንዲባባስ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተለይ በጫሞ ወንዝ አከባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የአንዱን መሬት ለሌላኛው በመስጠትና በማፈናቀል በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በተቀየሰ ሴራ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ግጭት በስተጀርባ የሰማያዊ ፓርቲ እጅ አለበት በሚል ቅስቀሳ ከማድረግም ባሻገር ኃይሌ፣ ኦለታና ሆልቴ በተባሉ ቀበሌዎችና ሰገን ከተማ በግጭቱ ሰበብ በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡
አስተባባሪው አክለውም ‹‹ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በተለይ በ1984 ዓ.ም፣ በ1993 ዓ.ም እና በ1995 ዓ.ም ከፍተኛ ግጭቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ኢህአዴግ ባመጣው ከፋፍለህ ግዛ የተከሰቱ ናቸው፡፡ አሁን ምርጫውን ተከትሎ በፈጠረው ሴራ ያስነሳውን ግጭት ሰማያዊ ፓርቲን ለመምታት እየተጠቀመበት ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment