Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, May 7, 2015

“የጀግኖች እናቶቻችንን እና አባቶቻችንን ፈለግ እንከተል!” – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት


“የጀግኖች እናቶቻችንን እና አባቶቻችንን ፈለግ እንከተል!” – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማክሰኞ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፭

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርገዋት የኖሩት ደረታቸውን ለጦር፣ እግራቸውን ለጠጠር፣ ሕይዎታቸውን ለሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር እንዲሁም ለወገኖቻቸው ነፃነት ሲሉ ሲገብሩ የኖሩ ጀግኖች እናቶች እና አባቶች ስለነበሩን ነው። ከ፸፬(ሰባ አራት) ዓመታት በፊት ፋሽስት ጣሊያንን ያንበረከኩት የዛሬው ትውልድ ወላጆች እና አያቶች፣ ከሁሉም የሚበልጠው የጽናታቸው ምንጭ፣ ለአገራቸው ነፃነት የነበራቸው ቀናዒነት ነበር። ነገር ግን «የእሣት ልጅ ዐመድ» ሆኖ፣ በእኛ ትውልድ ዘመን እነርሱ በብዙ ልፋት እና ትግል የገነቧት ኢትዮጵያ በመፈራረስ ሂደት ላይ ናት።

በአምሥቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን «ዱሩ ቤቴ» ብለው የፋሽስት ጣሊያኖችን እና የእነርሱ ባንዳዎች የነበሩትን ከሃዲዎች ጥምር ጦር ተፋልመዋል። በኅዳር ወር ፲፱፻፳፯ ዓ.ም. ኦጋዴን ውስጥ ወልወል ወደተባለው የኢትዮጵያ ግዛት የፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች ዘልቀው በፈጠሩት ትንኮሣ የተጀመረው ጦርነት፣ ከአምሥት ዓመታት በላይ ወስዶ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ ወረራው ተቀልብሷል። በእኒያ አምሥት የአርበኝነት ዓመታት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይ ዐማሮች፣ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በአሁኑ የገንዘብ ስሌት ሲተመን በቢሊዮን ብሮች የሚገመት ንብረት ወድሟል። ውድ እና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶች ተዘርፈዋል፣ ወይም እንዲወድሙ ተደርጓል። ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው ክቡር የሆነውን የአገርን ነፃነት ለማስመለስ ነበር፣ ጀግኖቹ የዚያን ዘመን ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነቱን ከፍለው አድርገውታል!

ከተለያዩ የታሪክ ድርሣናት እና መጻሕፍት ለማመሣከር እንደሚቻለው (ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. «የታሪክ ማስታወሻ»፣ ዶ/ር ተወልደ ትኩዕ በ፲፱፻፺ ዓ.ም. «የኢትዮጵያ አንድነት እና ኢጣሊያ»፣ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. «የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983»፣ ገብረወልድ እንግዳወርቅ በ፪ሺህ ዓ.ም. «ማይጨው፣ የማይጨው ዘመቻና የጉዞ ታሪክ»፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በ፪ሺህ፬ ዓ.ም. «የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት»፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም በ፪ሺህ፭ ዓ.ም. «መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ») ለማመሣከር እንደሚቻለው፣ በአምሥቱ ዓመት የፋሽስት ጣሊያን የወረራ ዘመን ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት አርበኞች በስፋት ይንቀሳቀሱ የነበሩት በተለይ፦ በሸዋ፣ በጎጃም፣ በጎንደር እና በወሎ ክፍለሀገሮች ነበር። ከእነዚያ ስመጥር የአርበኞች መሪዎች መካከል ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይገኙበታል።

· በሸዋ፦ አቡነ ጴጥሮስ፣ መላከፀሐይ ኢያሱ (የልጅ ኢያሱ ልጅ እና የሸዋ አርበኞች መሪ፣ አበበ አረጋይን ራስ ብለው የሾሙ)፣ ራስ ደስታ ዳምጠው (በሲዳሞ ግንባር ያዋጉ እና በጉራጌ አውራጃ በፋሽስቶች ተማርከው የተገደሉ)፣ ራስ አበበ አረጋይ (መንዝ፣ ተጉለትና ቡልጋ፣ ምንጃር)፣ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ደጃዝማች አበራ ካሣ (ሰላሌ)፣ ደጃዝማች አስፋው ወሰን ካሣ (ሰላሌ)፣ ደጃዝማች ወንደወሰን ካሣ (ሰላሌ)፣ ደጃዝማች ባልቻ ሣፎ (በጉራጌ)፤ ደጃዝማች ፍቅረማርያም አባተጫን፣ ደጃዝማች አውራሪስ (መሐል ሸዋ)፣ ደጃዝማች መንገሻ ወሰኔ (መሐል ሸዋ)፣ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቆሥላሤ (መርሃቤቴ እና ሰላሌ)፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ (ጅባትና ሜጫ)፣ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ (ጅባትና ሜጫ)፤ ደጃዝማች በቀለ ወያ (በጉራጌ)፤ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ልጅ ኃይለማርያም ማሞ፣ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣

· በጎጃም፦ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ (የጎጃምን እና የጎንደርን ጦር መርተው በሽሬ ግንባር ያዋጉ)፣ ራስ ኃይሉ በለው (ሞጣ)፣ ቢትወደድ አያሌው መኮንን (ባህርዳር-አቸፈር)፣ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ (አቸፈር እና አገው ምድር)፣ ደጃዝማች አበረ ይማም (ባህርዳር፣ አቸፈር እና ሜጫ)፣ ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህ (ቡሬ ዳሞት)፣ ደጃዝማች ደስታ እሸቴ (ደጋ ዳሞት)፣ ደጃዝማች ኃይለኢየሱስ ፍላቴ (ደጋ ዳሞት)፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (ብቸና)፣ ደጃዝማች መንገሻ አቦዬ (ሞጣ፣ ትውልዳቸው አልቡኮ (ወሎ))፣ ቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ፣ አአቶ ጌታሁን ተሰማ (በኋላ ሚኒስትር እና አምባሣደር)፤

· በጎንደር፦ ደጃዝማች ዮሐንስ እያሱ (የልጅ እያሱ ልጅ፣ እና የቤገምድር አርበኞች አስተባባሪ)፣ ቢትወደድ አዳነ መኮንን፣ ቢትወደድ ገሠሠ ረታ፣ ራስ ውብነህ (አሞራው) ተሰማ፣ ደጃዝማች ዳኘው ተሰማ (ጎንደር፣ ቤገምድር)፣ ደጃዝማች ብሬ ዘገዬ፣ ደጃዝማች ታደሰ ይማም፣ ደጃዝማች ጀምበሩ፣ ደጃዝማች ገብሬ ካሣ፣ ፊታውራሪ ሥዩም ነጋሽ፣ ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን(አባ ከንትር)፣ ፊታውራሪ አለማየሁ ቢተዋ (ጭልጋ)፤

· በወሎ፦ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ (በላስታ)፣

· በባሌ፦ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፤

· በሐረርጌ (ኦጋዴን)፦ ግራዝማች (በኋላ ደጃዝማች) አፈወርቅ ወልደሰማዕት፤

· በኢሉባቦር፦ አቡነ ሚካኤል፤

በዚህ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ያልተካተቱ አያሌ አርበኞች አሉ። ለወደፊት እያጣራን በስፋት እንዘግብበታለን።

ከፋሽስት ጣሊያን ጦር ጋር ሲፋለሙ የነበሩት አብዛኞቹ ጀግኖች እናቶች እና አባቶች ዛሬ በሕይዎት የሉም። ከመቃብር በላይ የሚውል ሥራቸው ግን ለዘለዓለም በትውልድ ሲዘከር የሚኖር ነው። ለመሆኑ እኒያ ጀግኖች ዛሬ ከመቃብር ተነስተው የትግሬ-ወያኔ የሚያመሰቃቅላት አገራቸው ኢትዮጵያ ያለችበትን እጅግ አሣፋሪ የታሪክ ምዕራፍ ቢመለከቱ ምን ይሰማቸው ይሆን? መቼም በምንም ተዓምር የባንዶች ልጆች እና የልጅ-ልጆች የሆኑት እነ መለስ ዜናዊ፣ ስብሐት ነጋ፣ ወዘተርፈ የሚያፈራርሷት የኢትዮጵያ ሁኔታ ሐሴትን ሊያቀዳጃቸው በፍጹም እንደማትችል ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የሚገነዘበው ነው። ስለዚህ በእኛ ስንፍና እና ቸልተኝነት አገራችንን ለዚህ የታሪክ ውርደት ያበቃነው የአሁኑ ትውልድ፣ ለተተኪው ትውልድ የባሰ ችግር ከምናወርሰው፣ ቆም ብለን ያለፍንበትን የስህተት ጎዳና እንመርምር፣ ጊዜው ሣይጨልምብንም እናርመው!

ኢትዮጵያ በታማኝ እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!

No comments:

Post a Comment

wanted officials