የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና አዲስ አበባ ውስጥ የወረዳ 17 ዕጩ ተወዳዳሪ የሆነው አቶ ዮናታን ተስፋዬ የታዛቢዎቹን ፎቶ ግራፍና አድራሻ ለምርጫ ጣቢያው እንዲያሳውቅ ተጠየቀ፡፡ እስካሁን ከታዛቢ ሙሉ ስም ውጭ ፎቶግራፍና አድራሻ የሚጠየቅበት አሰራር እንደሌለ የተገለጸ ሲሆን ምርጫ ቦርድም ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ የታዛቢዎችን ስም ዝርዝር እንዲልኩ ማስታወቁ ተመልክቷል፡፡
ይሁንና የወረዳ 17 ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌታቸው ማሞ ‹‹ይህ የወረደ መመሪያ ነው፡፡ የታዛቢዎቹን ፎቶ ግራፍና አድራሻ ካላመጣችሁ አንመዘግብም›› ማለታቸው ታውቋል፡፡ የሌሎች ፓርቲዎችና የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች በትናንትናው ዕለት የታዛቢዎቻቸውን ስም ዝርዝር ያሳወቁ ሲሆን ፎቶ ግራፍና አድራሻ እንዳልተጠየቁ ለማወቅ ችለናል፡፡
እስካሁን የታዛቢን ፎቶ ግራፍና አድራሻ የሚጠይቅ ህግ እንደሌለ የገለጸው አቶ ዮናታን ‹‹ይህ ጥያቄ እየተጠየቀ ያለው በእኔ ላይ ብቻ ነው፡፡ መቼም ህጋዊ መመሪያ በእኔ ላይ ብቻ ሊወርድ አይችልም፡፡ ለእኔ ብቻ ህገ ወጥ መመሪያ ወጥቷል ማለት ነው፡፡ የዚህ መመሪያ የሚሉት ዋናው አላማው ታዛቢዎችን በማዋከብ እንዳይታዘቡ ለማድረግ ነው›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡