Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, May 7, 2015

ሰመጉ ጥቃት እየደረሰበት መሆኑን አስታወቀ



ሰመጉ ጥቃት እየደረሰበት መሆኑን አስታወቀ




ኢሳት ዜና :-የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ( ኢሰመጉ) የአሁኑ ሰመጉ ሚያዚያ 26 ቀን 2007 ዓም ባወጣው መግለጫ በአዋሳና አዲስ አበባ በሚገኙ የድርጅቱ ፅህፈት ቤቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰበት አስታውቋል።

መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ላይ በድርጅቱ ላይ አፍራሽ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሰው ሰመጉ፣ ሚያዚያ 24 ቀን 2004ዓም የሰመጉ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቢሮ በስራ ቀን ከጠዋቱ 4 ሰአት ላይ ተደፍሯል። ሰመጉ የጽ/ቤቱን የጠረጴዛ መሳቢያዎች ገንጥሎ

ሰነዶችን ሲበረብር እጅ ከፍንጅ የተያዘ ግለሰብ ለፖሊስ ተላልፎ ቢሰጥም፣ የክስ ሂደቱ በመታየት ላይ እያለ ግለሰቡ በዋስ ተለቋል በሚል ከአካባቢው እንዲሰወር ተደርጓል ብሎአል።

መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓም የሃዋሳ ሰመጉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቢሮ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በሩ ተከፍቶ ተገኝቷል የሚለው መግለጫው፣ በውስጡ የሚገኙት የመዛግብትና የልዩ ልዩ እቃዎች መስቀመጫ ቁምሳጥኖችና የቢሮው ጠረጴዛ መሳቢያዎች ተሰብረዋል።

ብዛት ያላቸው የድርጅቱ መዝገቦችና የሂሳብ ሰነዶችም በስርአት ተቀምጠው ከነበሩበት ስፍራ ተነስተው በጠረጴዛውና በወለሉ ላይ ተበታትነው ተገኝተዋል። የድርጅቱ ማህተም ከተቀመጠበት ቦታ ተንስቶ ሌላ ስፍራ በመገኘቱ፣ ማህተሙ ለህገወጥ ተግባር ውሎ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት ማሳደሩን የሰብአዊ መብት ተማጓቹ ድርጅት ጠቅሷል። ጉዳዩን የያዘው ፖሊስ ውጤቱን እስካሁን ለሰመጉ አላመለከተም።

መጋቢት 24 ደግሞ ከቀኑ 11 ሰአት አካባቢ አዲስ አበባ በሚገኘው የሰመጉ ዋና ጽ/ቤት የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ በነበረ የሰመጉ መኪና ላይ ከፎቅ ላይ ወደቀ የተባለ እቃ ጉዳት እንዳደረሰበት ገልጿል። ጉዳዩን ለፖሊስ ቢያመለክትም ምንም መልስ ሊያገኝ
አለመቻሉንም ገልጿል።

መንግስት በሃገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ሰብአዊ መብቶችን የማስከበር እንቅስቃሴዎችን በአሉታዊ መንገድ መመልከቱ፣ እንቅስቃሴዎችንም በተለያዩ መንገድ ማዳከሙ እና ጭራሹ አፋኝ ህጎችን በማውታት የማጥፋት ሙከራ ማድረጉ ህጋዊና ጠቃሚ አሰራር አለመሆኑን በተለያዬ ጊዜያት መግለጹን ድርጅቱ ጠቅሷል።

መንግስት የሰብአዊ መብት ተሟጋች አባሎቻቸውንና ሰራተኞቻቸውን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ ሰመጉ ጠይቋል።

ብቸኛው የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት፣ በመላው አገሪቱ የነበረውን ጥንካሬ በገዥው ፓርቲ ተጽእኖዎች እንዲያጣ ተደርጓል። ድርጅቱ ላለፉት 24 አመታት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲያጋለጥ መቆየቱ ከገዢው ፓርቲ ጋር እንዲላተም አድርጎታል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹን የክልል ጽ/ቤቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንዲዘጋ በመደረጉ ፣ በፊት እንደሚያከናውነው ተከታታይ መግለጫውን ሲያወጣ አይታይም። ይሁን እንጅ በተወሰኑ ወራት የሚያወጣቸው መግለጫዎች አሁንም ገዢውን ፓርቲ እያስቆጡት መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment

wanted officials