Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, August 22, 2015

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየዓመቱ ከ1.5 ቢልዮን ብር በላይ ይመዘበራል



አዲሱ ዓመት ቤተ ክርስቲያን በፀረ ሙስና እንቅስቃሴዋ ልዕልናዋን የምታስመልስበት እንደሚኾን ፓትርያርኩ ተናገሩ
የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማስቀረት “የተለያዩ ነፋሳት እየነፈሱ” መኾኑን ጠቁመዋል
የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ሙስና እንቅስቃሴውን በማጠናከር በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል


ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው:

መጪው 2008 ዓ.ም.፣ ቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮቿን አስተካክላ ልዕልናዋን የምታስመልስበት እንደሚኾን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡

ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ የሙስና እና የሥነ ምግባር ብልሹነትን ለማስወገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ “ጭላንጭል እየታየበት ነው” ያሉት ፓትርያርኩ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ ልዕልና እና ሕይወት እስኪመለስ በሰላማዊ መንገድ እና በአቋም መታገላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡

አቡነ ማትያስ በፓትርያርክነት በተመረጡበት በዓለ ሢመት፣ በቆራጥ የለውጥ ርምጃዎች የፀረ ሙስና ሥርዐት ለመደንገግ የገቡትን ቃል መነሻ በማድረግ በተካሔዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ከየሰንበት ት/ቤቶች ሥራ አመራር አባላት ጋር ከትላንት በስቲያ ከቀትር በኋላ በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር ጉባኤ ተወካዮች በተገኙበት ውይይት፤ “ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለማረም እና ለማስወገድ በሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ከጎኔ እንድትቆሙ” በሚል ፓትርያርኩ የሰጡት አባታዊ መመሪያ ምእመኑን ያስደሰተ እና ወጣቱን ያነቃቃ መኾኑ በተወካዮቹ ተገልጧል፡፡
መመሪያውን ለማስፈጸም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንዳሉ የተናገሩት የማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ፣ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዳይገኝለት የሚጥሩ ኃይሎች ፓትርያርኩ ከወጣቶች እንዳይገናኙ የፈጠሩትን ዕንቅፋት አስረድተዋል፤ ዕንቅፋቶቹን በመቋቋም በተሠሩ ሥራዎች ወጣቶቹን እንዲያበረታቱም ጠይቀዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እና ሰፊ የመሬት ይዞታ ቢኖሯትም የሚገባውን ያኽል ተጠቃሚ እንዳልኾነች ሰሞኑን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ የቀረበው የአዲስ አበባ አድባራት የመሬትና ሕንፃዎች ኪራይ ተመን ጥናታዊ ሪፖርት ማረጋገጡን የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ በውይይቱ ላይ ጠቅሰዋል፡፡ የንግድ ተቋማቱ የሚያመነጩት ገቢ የግለሰቦች መጠቀሚያ ከመኾኑ ባሻገር፣ በሀገረ ስብከቱ የቃለ ዐዋዲውን ሕግና መመሪያ ተደግፎ በታማኝነት ባለመሠራቱ በየወሩ ብር 100 ሚሊዮን፣ በዓመት ብር 1ነጥብ5 ቢልዮን ለራስ አገዝ ልማት መሰብሰብ ሲቻል እንደሚመዘበር ልዩ ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡
በሙሰኛ ሓላፊዎች ላይ አስተማሪና ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ ብልሹ አሠራርን በወሳኝ መልኩ ለማረምና ለማስወገድ፤ በመሪ ዕቅድ የሚመራ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ለለውጥ የተዘጋጀ አስተዳደራዊ መዋቅር ለማደራጀት፤ ዘመኑን የዋጀና ወጥነት ያለው የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዐት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት በፓትርያርኩ የተጀመረው ጥረት በቅርቡ በተሳካ መልኩ ከዳር እንደሚደርስ ልዩ ፀሐፊው አብራርተዋል፡፡ “የጠቅላይ ቤተክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ ብዙ ከደከመበት ጥናታዊ ሪፖርት ጋር ተያያዞ በቅርቡ ኹላችንም በጉጉት የምንጠብቀውን ነገር እናያለን፤” ያሉት ልዩ ጸሐፊው፣ “በአዲስ ዘመን፣ በአዲስ መንፈስ ቤተ ክርስቲያናችን የተሳካ አስተዳደራዊ የለውጥ ኹኔታ ይኖራታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ እናንተ ወጣቶች ስለኾናችኹ በሩ ክፍት ነው፤ አግዟቸው፤” ብለዋል፡፡
የተጀመረውን የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ለማዳከምና ተቋማዊ ለውጡን ለማስቀረት “ብዙ ነፋሳት እየነፈሱ” እንዳሉ ያመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች “ሕይወት የሚሰጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ነፋስ (መልእክት)” ብቻ ማድመጥ እና መከተል እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የካህናትም የምእመናንም መኾኗንና ልዩነቱ የሓላፊነት ድርሻ ብቻ እንደኾነ ያስረዱት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹ትውልዱ ዛሬ በሚሠራው ሥራ የታሪክ ተጠያቂም ተመስጋኝም በመኾኑ ወጣቶች አያገባችኹም አይባልም፤ የነገ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ናችኹ፤ በሞያችኹ፣ በዕውቀታችኹ የበለጸጋችኹ ስለኾናችኁ ትልቅ ሚና አላችኹ፤ ይኼን ጸያፍ ነገር አስወግደን የቤተ ክርስቲያንን ሕይወቷን፣ ልዕልናዋን እስክናስመልስ አብረን በጋራ መቀጠል አለብን፤›› በማለት የሰንበት ት/ቤቶቹን አመራሮች አሳስበዋል፡፡
ፓትርያርኩ፣ ጭላንጭል ታይቶበታል ባሉት የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብቶች እና ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠት አላግባብ የበለጸጉ የአድባራት ሓላፊዎች በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ እንዳሳለፈ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials