Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, August 13, 2015

የመድረክ ልዩ ጉባዔ አባል ድርጅቶቹ ውህደት ላይ እንዲያተኩሩ ወሰነ

–ተጠናክሬ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ አደርጋለሁ ብሏል
f25dc42ddc16911315f45dba350f4f07_L
ነሐሴ 2 እና 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ልዩና አስቸኳይ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ አባል ድርጅቶቹ የውህደት ጥያቄን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች ወቅታዊ የፖለቲካና የአወቃቀር አሠራሮች ላይ በመወያየትና በመወሰን ጉባዔውን እንዳጠናቀቀ ታውቋል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት የፓርቲዎቹ የውህደት ወቅት መቼ መሆን አለበት የሚለው ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር የገለጹት የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ ‹‹እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ፓርቲዎች ውህደት ይፈጽሙ የሚል ሐሳብ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ፓርቲዎቹ መጀመርያ ከአባሎቻቸው ጋር በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩና ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተወስኗል፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
አቶ ጥላሁን፣ ‹‹በጥሩ ሁኔታ ከተንቀሳቀስን በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባዔ ውህደቱ ይከናወናል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ የግድ ከዚህ ማለፍ የለበትም ብለን ያስቀመጥነው የጊዜ ገደብ የለም፤›› በማለት ቁርጥ ያለ ጊዜ እንዳልተወሰነለት ተናግረዋል፡፡
መድረክ በዚህ ልዩና አስቸኳይ ጉባዔው ከገመገማቸው በርካታ ነጥቦች መካከል የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓትና ሒደት ይገኙበታል፡፡ ‹‹እስካሁን በአገራችን በአምስቱም ዙሮች የተደረጉት ጠቅላላ ምርጫዎች ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ አልነበሩም፡፡ ለወደፊቱም በዚህ ሁኔታ መቀጠል ተገቢነት የለውም፤›› በማለት እስካሁን የተካሄዱትን ምርጫዎች በአጠቃላይ ችግር እንደነበረባቸው ገልጿል፡፡
የአገሪቱን የምርጫ ሒደትና ውጤት በተደጋጋሚ በመተቸት፣ ነገር ግን በምርጫዎች በመሳተፍ ላይ የሚገኘው መድረክ ቀጣይ የሚኖረው የትግል አማራጭ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ጥላሁን፣ ‹‹እስካሁን ድረስ በምርጫ ተወዳድረን ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የራሳችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን የሚል ሐሳብ ነበረን፡፡ አሁን ግን ምርጫ መወዳደር ብቻ ሳይሆን ምርጫ የማይኖርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ሲፈልግ አታሎና አስፈራርቶ ሳይፈልግ ደግሞ በጉልበት ቀምቶና ነጥቆ የሚመረጥ ፓርቲ ባለበት አገር ምርጫ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቀጣዩ ትግል የሚሆነው ምርጫና ትክክለኛ የምርጫ ምኅዳር እንዲኖረ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የመድረክ ቀጣይ አቅጣጫ ተብሎ የተለየው ደግሞ ‹‹ሕዝቡ በምርጫ ላይ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ ገለልተኛ የምርጫ አስተዳደር እንዲቋቋም ግፊት ማድረግና የካድሬዎችን ጣልቃ ገብነትና የአፈና መዋቅርን ማስወገድ›› የሚሉት ተጠቃሽ እንደሆኑም እንዲሁ አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ቅዳሜና እሑድ የተካሄደው የፓርቲው ልዩና አስቸኳይ ጉባዔ ሌላው የመረመረው ጉዳይ የፓርቲውን ጠንካራና ደካማ ጐን መገምገም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የተለያዩ ነጥቦችን አንስቶ ተወያይቷል፡፡
መድረክ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስተካከል የታገለበት መንገድና ሕዝቡን በዚህ ላይ ማደራጀት አለመቻሉ ክፍተት እንደነበረው ገምግሟል፡፡ ‹‹በተለያዩ መንገዶች የተጠረነፈውን ሕዝብ ነፃ ማውጣት ላይ ትኩረት ሰጥተን በቂ ሥራ አልሠራንም፤›› በማለት አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ የፈጠረው ወጥመድ ውስጥ እየገቡ ዝም ብሎ ጊዜ ማቃጠል ነበር የነበረው፤›› ሲሉ የእስካሁኑ ሒደት እንደተገመገመ ጠቁመዋል፡፡
‹‹በቀጣይም ሕዝቡን ለማንቃትና ለዚያ የሚመጥን አደረጃጀት ማዋቀር አለብን፡፡ ስለሆነም ከሥነ ልቦናም ሆነ ከትግል አንፃር ያንን አድርገን ሕዝቡ በነፃ ምርጫ የሥልጣን ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥ የሚችልበት ደረጃ እንዳለ ማስገንዘብና በዚያ ደረጃ መሥራት እንዳለብን አይተናል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
መድረክ ባለፈው ዓርብ በሰጠው መግለጫ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱ ላይ ተባብሶ በቀጠለው እንግልት፣ እስር፣ የንብረት መውደምና ሞት የተነሳ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ስላልቻልኩ በህልውናዬ ላይ ልመክር ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡ ጫናው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ በመበርታቱ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እሠራለሁ ያለው መድረክ፣ በአባላቱ ላይ መንግሥት እያደረሰ ያለውን ችግር በአስቸኳይ እንዲያቆም ጥሪ አድርጓል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials