Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, August 22, 2015

ለወጪ ንግድ ዘርፍ መዳከም የመንግሥት ቢሮክራሲ ተጠያቂ ተደረገ


11903809_443398799195196_3690487593313832144_n
  • 286
     
    Share
-የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማሽቆልቆል አሳሳቢ ሆኗል
በመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ዘርፍ የተመዘገበው ደካማ ውጤት፣ በመንግሥት ቢሮክራሲና በአስፈጻሚዎች ድክመት ጭምር መሆኑ ተገለጸ፡፡ የአፈጻጸሙ ድክመት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት አደጋ ላይ መጣሉ ተጠቆመ፡፡
ይህ የተገለጸው በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ዙሪያ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከንግድ ማኅበረሰቡና ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡
11896119_1042047069148054_1788774137031689069_n
ነሐሴ 11 እና 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በተለያዩ አዳራሾች ከተካሄዱት የውይይት መድረኮች መካከል፣ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሆኑት በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የተመራው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የግሉ ዘርፍ፣ የሠራተኞችና የአሠሪዎች ተወካዮች በተለይ በሁለቱ ዘርፎች ላይ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያልተገኘበትን ምክንያት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለምንድነው የወደቀው? በማለት ጥያቄ ያነሱት ዶ/ር አርከበ፣ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን የዕቅድ ዘመን ከማኑፋክቸሪንግ ሌላ የወጪ ንግዱ ላስመዘገበው ደካማ አፈጻጸም ያሉ ችግሮችን ማወቅ እንደሚሹ ገልጸው፣ ችግሩ የግሉ ዘርፍ አቅም ማነስ ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከምታውለው መድኃኒት ውስጥ 90 በመቶው ከውጭ የሚገባ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር አርከበ፣ በዚህ ዘርፍ ከውጭ የሚገባውን መድኃኒት ሊያመርቱ የሚችሉ ባለሀብቶች ተሳትፎ ማነስን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለው ኢንቨስትመንት አናሳ መሆኑን ለማመላከትም የግብፅን የመድኃኒት ኢንዱስትሪ አስታውሰዋል፡፡ ግብፅ ለአገር ውስጥ የሚሆናትን የመድኃኒት ፍጆታ አሟልታ የተረፋትን ለውጭ ገበያ ታቀርባለች ብለዋል፡፡
ዶ/ር አርከበ እንዲህ ባሉት ዘርፎችና በሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማሳደግ መዋቅራዊ ለውጥ ሊመጣ ይገባል ብለዋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማሳደግ የሚቻለው ደግሞ በመንግሥት ሳይሆን በባለሀብቱ ነው ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ መንግሥት የመሪነቱን ሚና  እንደሚጫወት ግን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው ድርሻ አምስት በመቶ መሆኑን፣ ይህ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ድርሻ ብዙም ለውጥ እንደሌለው፣ ስለዚህ ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ኃላፊነት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ነገር ግን የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከገቡ በኋላ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርት ማምረት ሲገባቸው፣ አራት አምስት ዓመታት ሲፈጅባቸው መታየቱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይደረስበታል የተባለውን ግብ እንዳያሳካ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ችግሩ የመንግሥት ነው? ወይስ የባለሀብቱ? የሚል ጥያቄ ከዶ/ር አርከበ ቀርቧል፡፡ ተሳታፊዎችም ችግሩ የመንግሥት ጭምር መሆኑን በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ፣ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን መደገም የለበትም ያሉዋቸውንም ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡
ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመግባት ትልቅ እንቅፋት ሆነዋል ከተባሉት ጉዳዮች አንዱ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መስተጓጎል መሆኑንም በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ለወጪ ንግድ መዳከም አንድ ምክንያት መሆኑን የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ገልጸዋል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቢኖሩም እንኳ የኃይል አቅርቦቱ መቆራረጥና በበቂ ደረጃ ያለመቅረቡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ፣ ይህ የማይስተካከል ከሆነ ወደፊትም ችግሩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በዚህ የውይይት ፕሮግራም ዶ/ር አርከበም ሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደ ችግር ካነሱዋቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የፋይናንስ አቅርቦትን የሚመለከት ነበር፣ ‹‹አንድ አገር በለፀገ የሚባለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን ኤክስፖርት በሚያደርገው ምርት በበቂ ደረጃ ከመሸፈን አልፎ በቁጠባ መልክ መቀመጥ ሲችል ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፡፡  የዓለም ኢኮኖሚ በሚታመምበት ጊዜ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ እንዳይጎዳ የሚያደርገው ለቀጣይ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያለበት ሁኔታ በጣም በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ በመጀመርያው ዕቅድ ዘመን ክፉኛ የወደቅንበት ዘርፍ ቢኖር የወጪ ንግድ አፈጻጸማችን ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ይህንን የሚያክል አገር እያመነጨ ያለው የውጭ ምንዛሪ አንድ ኮርፖሬሽን ሊያስገኘው የሚችል እንደሆነ አመልከተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለገቢ ንግድ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እያገኘች ያለችው ከውጭ ብድርና ዕርዳታ መሆኑ ለውጭ ፍላጎት ማሟያ እየዳረጋት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ስለሚታወቅ ደግሞ በአንዳንድ ባንኮች አካባቢ ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር እየተፈጸመበት መሆኑን መንግሥት የሚያውቀው መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አርከበ፣ ለውጭ ምንዛሪ ጉድለቱ ግን ዋነኛ ምክንያት በመጀመርያው የዕቅድ ዘመን ከወጪ ንግድ ይገኛል የተባለው ከስምንት እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር ሊገኝ አለመቻሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ መትረፍረፍ አለበት፡፡ የአንድን አገር ዕድገት የሚገታው ዋነኛ ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሌለ ምንም ነገር ማድገር ስለማይቻል በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት መደፈን ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡ በ3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንዴት ይህን ዕድገት ማስቀጠል ይቻላል? በማለት የውጭ ምንዛሪ ግኝት አሳሳቢነትን ጠቁመዋል፡፡
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት? በማለት ዶ/ር አርከበ ላቀረቡት ጥያቄ፣ ከተሰብሳቢዎች መካከል አብዛኞቹ  በመጀመርያው ዕቅድ ዘመን የታዩትን ችግሮች አለመድገምን እንደ መፍትሔ አቅርበው፣ በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ቢሮክራሲዎች አላሠራ ማለታቸውን በዋነኛነት ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል  በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ አራት ዓመት እንደፈጀባቸው፣ ይህ የሆነው ግን በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በገጠሟቸው ቢሮክራሲዎች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከምዕራብ ኦሮሚያ ክልል አሊ አባቦር ዞን የመጡት ሌላው ተሳታፊ ለወጪ ንግድ መዳከም ደግሞ አሁን ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ኮንትሮባንድ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ በቡና ላይ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ ፈጦ እንደሚታይ በመግለጽ፣ የድርጊቱ መስፋፋት ቡና ባለቤት አለው ወይ? የሚያስብል ነው በማለት አለ ያሉትን ችግር በሰፊው አብራርተዋል፡፡
እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ቡና በቀን በመንግሥት ተሽከርካሪዎች ጭምር ታጅቦ በግልጽ እንደሚወጣ፣ አዲስ አበባ ሲገባም በሞተር ብስክሌት ጭምር ሳይቀር እንደሚታጀብ የገለጹት እኚህ ተሳታፊ፣ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ለወጪ ንግዱ ማነቆ እየሆነ መምጣቱን መንግሥት ሊገነዘበው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የቡና ኮንትሮባንድ ንግድ በተደራጀ ሁኔታ የሚፈጸምና በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ባሉ አስፈጻሚ አካላት ጭምር የሚታገዝ ነው በማለት ያለውን ችግር በምሬት ተናግረዋል፡፡ ችግሩ የፓርቲ አባልነትን መሸሸጊያ በማድረግ የተፈጠረ ብልሹ አሠራር የወለደው በመሆኑ፣ ይህንን ብልሹ አሠራር ለመግታት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎችም በተለይ ከመልካም አስተዳደር ጋር ያለው ችግር የፓርቲ አባልነትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸም በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለሥርዓቱም ጭምር አደጋ ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አገሪቱ በዕድገቱ ላይ ብትሆንም ይህንን ዕድገት ማስቀጠል ከባድ እየሆነ ነው ያሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ አስፈጻሚዎች የማስፈጸም አቅም ማነስ በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ የመሬት አስተዳደር ውስጥ ያሉ አስፈጻሚዎች፣ የጉምሩክ ባለሥልጣንና የመሳሰሉት ተቋማት ለወጪ ንግዱ እንቅፋት መሆናቸውንም የራሳቸውን ገጠመኝ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
የአበባ አምራቾችና ላኪዎችም በዘርፉ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ብዙ እንቅፋቶች እንዳጋጠማቸው የገለጹበት መድረክ ነበር፡፡ በአበባ ኢንዱስትሪ ውስጥ በመሳተፍ ቀዳሚ ከሚባሉት ባለሀብቶች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ፀጋዬ አበበ፣ የአበባ እርሻን ለማስፋፋት አንዱ ማነቆ የሆነው የማልሚያ ቦታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡  ለማስፋፊያ የሚሆን ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በተደጋጋሚ ያሳወቁ ቢሆንም፣ እስካሁን መፍትሔ አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ደግሞ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት የሆነው ብርቱ ጉዳይ የመንግሥት ስብሰባዎችና የግምገማ ባህሎች ናቸው ብለዋል፡፡
ግምገማ ቃሉ ራሱ አሉታዊ ትርጉም አለው ያሉት ዶ/ር አረጋ፣ ሠራተኞች ብዙ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት እገመገማለሁ ብለው ተሸማቀው በመሆኑ ለአገልግሎት መጓደል ምክንያት እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
‹‹ፕሮፌሸናል ሠራተኞች መበረታታት አለባቸው፡፡ የፓርቲ አባልነትና የፕሮፌሽናል ሥራ መለየት አለበት፤›› ያሉት ዶ/ር አረጋ፣ ለምሳሌ መሐንዲስ ከሆነ በመሐንዲስነቱ ብቻ መሥራት አለበት ብለው፣ አሁን የሚታየው ግን ከላይ መሐንዲስ ከሥር የፓርቲ አባል ከሆነ መሸማቀቅ ይፈጥራል፡፡ ይህ ቁልጭ ብሎ የሚታይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ደግሞ፣ በአጠቃላይ የግል ዘርፉንና የመንግሥትን ግንኙነት የተመለከተ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹የግል ዘርፍ  የኢኮኖሚው ሞተር ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የግል ዘርፉን ምን ያህል ይፈልገዋል?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
መንግሥት የግል ዘርፉን ይዞ በትክክል ተጠቅሟል ወይ? የሚለውም ጥያቄ ሊመለስ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹የኮሙዩኒስት አስተሳሰብ ያለ ይመስል ያህል የግሉ ዘርፍ በዝባዥ ነው፣ ገንዘብ አለው፣ ጨቋኝ ነው በሚል አመለካከት ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከትም የግል ዘርፉ ሊሠራ የሚያስበውን ነገር እንዳይሠራ ማነቆ እየሆነበት ነው በማለት፣ መንግሥት የግል ዘርፉን በትክክል የዕድገቱ አንቀሳቃሽ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባዋል በማለት ጠይቀዋል፡፡
አቶ ሰለሞን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ፈጻሚ የግል ዘርፉ ነው ከተባለ በዕቅዱ ላይ ተሳታፊ መሆን ነበረበት ይላሉ፡፡ በተለይ በመጀመሪያው ዕቅድ ላይ እንደ ተቋም የግል ዘርፉ ያልተሳተፈ መሆኑን በማስታወስ፣ መንግሥት በትክክል የግሉ ዘርፉን መጥቀም አለበት ብለዋል፡፡
ዶ/ር አረጋም ይህንን ሐሳብ በመደገፍ፣ ‹‹እውነት የግል ዘርፉ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ነው የሚባለው ለማለት ያህል ነው? ወይስ በትክክል?›› የሚል ጥያቄ በማቅረብ በዚህ ረገድ እሳቸውም ብዥታ ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለአባባላቸው ምሳሌ ይሆናል ያሉት ደግሞ መንግሥት ለግል የትምህርት ተቋማት ያለውን አመለካከት ነው፡፡
እንደ ዶ/ር አረጋ ገለጻ የትምህርት ዘርፍ ሲነሳ ሁሌም ስለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነው የሚነሳው፡፡ በርካታ የግል የትምህርት ተቋማት ቢኖሩም ስለነሱ እንደማይነገር አመልክተዋል፡፡ ‹‹የእነሱ አስተዋጽኦ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የለም፤›› ያሉት ዶ/ር አረጋ፣  ይህ የግል ዘርፉን አስተዋጽኦ የሚያደበዝዝ በመሆኑ በቀጣዩ ዕቅድ ውስጥ የእነዚህ ተቋማት ሚና ሊገለጽ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ግልጽ ሊሆን ይገባል ያሉት ሌላው ነጥብ ደግሞ፣ የግል ዘርፉ አንዳንድ ሥራዎች ውስጥ ለመግባት ‹‹ይህንን ሥራ ሜቴክ ይሠራው ይሆን?›› በሚል ሥጋት መፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የሜቴክ ሥራ ምን ድረስ እንደሆነ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ዶ/ር አረጋ አመልክተዋል፡፡
‹‹አሁን ማተኮር ያለብን በሚቀጥለው አሥር ዓመት ሁላችንም ተረባርበን የበለፀገች አገር ማየት ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ‹‹ጉድለቶችና ማነቆዎች በሚታዩበት ጊዜ የመንግሥትን ጉድለቶች ከታየን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ቢሆንም በባለሀብቱ በኩል ያሉትም ችግሮች ሊፈቱ ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ችግር በተመለከተም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰጡት አስተያየቶች ከአስፈጻሚዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በፀጥታ ችግርም ትልቅ እንቅፋት ነው ተብሏል፡፡ ለትላልቅ እርሻዎች የሚሆኑ ባዶ መሬቶች እንዳሉ በመጠቆም፣ በእነዚህ መሬቶች ላይ ለማልማት በርካታ ባለሀብቶች ሙከራ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፣ ነገር ግን በፀጥታ ችግር፣ እምነት በማጣትና በመሳሰሉት ችግሮች የዘርፉ ተዋናዮች ያሰቡትን ለማሳካት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡
በተለያዩ ደረጃዎች የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት የግሉም ሆነ የመንግሥት ችግሮች መሆኑን የጠቆሙት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ፣ በተለይ በመንግሥት በኩል ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች መላላት ለችግሩ መስፋፋት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ የውጭ ባለሀብት በሚገባ እየተስተናገደ አይደለም የሚሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ የውጭ ባለሀብትን እናበረታታለን እየተባለ በተግባር የሚታየው ግን በተቃራኒ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የውጭ ባለሀብቱ ጊዜውን በአግባቡ ለመጠቀም አስልቶ የሚመጣና እያንዳንዱን ደቂቃ ሊጠቀም የሚፈልግ ቢሆንም፣ ወደ እኛ አስፈጻሚዎች ሲሄድ ግን ነገና ከነገ ወዲያ ይባላል፡፡ ይህ የውጭ ባለሀብቱን አያበረታታም፡፡ አስፈጻሚዎች ነገ ከነገ ወዲያ ማለታቸውን እንደ ቀላል ነገር የሚቆጥሩት መሆኑ ለዕቅዱ ተፈጻሚነት እንቅፋት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ችግር አለባቸው የሚባሉ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ መንግሥትም ለሕዝብ ተጠያቂ የሆነ ባለሥልጣን መፍጠር አልቻለም፤›› ያሉት አቶ ፋሲል፣ የግሉ ዘርፍ የአቅምና ሌሎችም ችግሮች ቢኖሩበትም በመንግሥት በኩል ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ዝግጅት ካልተደረገ ነገም ሌላ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ፋሲል እየታዩ ናቸው ያሉዋቸውን ችግሮች ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሁን እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍና በተሻለ ለመጓዝ ከታሰበ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ችግር የሚታይባቸው ዋና ዋና የመንግሥት ተቋማት ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ፋሲል ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ተሰጥቶባቸው ፈር መያዝና አገልግሎት አሰጣጣቸውንም ማስተካከል ይገባቸዋል ያሉዋቸውን ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ የመንግሥት ተቋማትን ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አንዱ ነው፡፡ ወደ ኋላ የተመለሱ ያሉዋቸው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም አስቸጋሪ የተባሉ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባንኮች እየተሻሻሉ የመጡ ቢሆኑም፣ አሠራራቸውን ሊያስተካክሉ፣ መንግሥት ትኩረት ሊያደርግባቸውና ሊያስተካክላቸው ይገባዋል ከተባሉት ውስጥ ተካትትዋል፡፡
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተመሳሳይ ትኩረት የሚሹ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ፋሲል ገለጻ፣ እነዚህ ተቋማት ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሠራ ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡ ዘወትር ችግሩን ብቻ ከመግለጽ ለችግሩም መፍትሔ ያስፈልጋል በማለትም አሳስበዋል፡፡
በሁለቱ ቀናት ውይይት የተሰበሰበው አስተያየት ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ በዛሬው ዕለትም [ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም.] ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የማጠቃለያ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ስድስት ሺሕ ያህል ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials