በምዕራብ ጎጃም የብአዴን አባላት አርበኞች ግንቦት 7 ውስጣችን ሰርጎ ገብቷል በሚል እርስበርስ እየተወነጃጀሉ መሆኑ ተሰማ * ክፍፍሉንም አባብሶታል
በምዕራብ ጎጃም የብአዴን አመራሮች መካከል መከፋፈል ተፈጠረ
የአርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ እንደዘገበው የምዕራብ ጎጃም የብአዴን አመራርና አባላት ከሀምሌ 29 እስከ ነሀሴ 1 2007 ዓ.ም ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ነው መከፋፈሉ ሊከስት የቻለው፡፡ የምዕራብ ጎጃም የብአዴን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሀብታሙ፣ የዞኑ ምክትል ከንቲባ አስፋው ገበየሁና የወረዳው የብአዴን ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አላምር ተሻለ የተባሉ የህወሓት አገልጋይ የመሩት በዱላ ቀረሽ ስድድብ፣ እርስበርስ መወነጃጀልና የተደበቀ ገመናን በመነስነስ ታጅቦ ለሦስት ቀናት የዘለቀው ስብሰባ ከመነሻው በዋናነት ለውይይት ያቀረባቸው አርበኞች ግንቦት 7 ባወጀው ጦርነት ላይ ተመስርቶ በሽበርተኝነት ላይ የሚያጠነጥን አንድ ሃሳብና የብአዴንን 35ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርን የሚመለከት ሌላ ተጨማሪ እርዕስ ያነገበ ሁለት አብይ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡
ነገር ግን ስብሰባው የታቀደለትን አቅጣጫ ስቶ ፈር በመልቀቅ አባላትና የበታች የብአዴን አመራሮች ከአንድ ላይ በማበር በበላይ አመራሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያነሱ የበላይ አመራሮች ደግሞ በፌደራል መንግስቱ በሚገኙ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡
በመሆኑም የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚ የሆነው ብአዴን ከሦስት ጎራ የመሰነጣጠቅ እጣ ገጥሞት ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበት ይገኛል፡፡
የብአዴን አባላትና የበታች አመራሮች የበላይ አመራሮቻቸውን “የህወሓት አሽከሮች በመሆናችሁ ለክልሉ ብሎም ለአገራችን ምንም አይነት አዎንታዊ ሚና አከናውናችሁ ለውጥ ልታመጡ አልቻላችሁም፡፡” በማለት ልክ ልካቸውን ነግረው እርቃናቸውን ሲያስቀሯቸው የበላይ አመራሮች ደግሞ በበኩላቸው “ችግሩ የኛ አይደለም የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ ብልሽቱ ያለው ከላይ ከአለቆቻችን ነው፤ የፌደራሉ የብአዴን አመራር በህወሓት አንገቱን ታንቆ ተይዟል፡፡” በማለት የብአዴንን ቁንጮዎች በአደባባይ አበሻቅጠዋቸዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም የብአዴን ዝቅተኛ አመራሮችና አባላት “በአገሪቱ ብሎም በክልሉ እስካሁን ምንም አይነት እድገት አልተመዘገበም፤ ዘወትር የምታቀርቡት ሪፖርት ነጭ ውሸት ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ የሚገኘው የልማት እንቅስቃሴ አንድ ክልል ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፤ ልክ እንደ ትግራይ ሁሉ ዳያስፖራው ክልሉን እንዲያለማ እድል አልተሰጠውም በሩ ክርችም ብሎ ተዘግቷል…” የሚሉ ሃሳቦችን አጠናክረው አንስተዋል፡፡
አስፋው ገበየሁ፣ አማረ የተባሉና ሌሎች የምዕራብ ጎጃም የብአዴን አመራሮች በስርቆት ከፍተኛ ሀብት ማፍራታቸው በስብሰባው ላይ ተጋልጧል፡፡
በተጨማሪም የምዕራብ ጎጃም የብአዴን አመራሮችና አባላት በውስጣቸው የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት እንደተሰገሰጉ በማመን እርስበርስ ወደ መፈራረጅ በመሄዳቸው ሹጉጣቸውን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው በዓይነ ቁራኛ እየተያዩ ስብሰባውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
በዳንሻ ከተማ ለህዝቡ ሊከፋፈል በመጋዘን የተከማቸ ከ30 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት የደረሰበት በመጥፋቱ በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ እጥረት መከሰቱ ታወቀ፡፡
የምግብ ዘይቱን ለዳንሻና አካባቢው ህዝብ እንዲያከፋፍሉ የተረከቡት ክብሮምና ተክላይ የተባሉት ግለሰቦች ሲሆኑ ከ30 ሺህ ሊትር በላይ የሆነውን የምግብ ዘይት ተዘረፈብን ሲሉ ህብረተሰቡን ለከፋ ችግር ዳርገውት ይገኛሉ፡፡
– See more at:http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45761#sthash.RZM1xiVy.dpuf
No comments:
Post a Comment