ከሳምንታት በፊት ልደታ ፍርድ ቤት በአንድ ችሎት በአጋጣሚ ሁለት የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ተከታተልኩ፡፡ ሁለቱም እስረኞች ዝዋይ ሆነው በፕላዝማ ይግባኝ እየጠየቁ ነው፡፡ አንዱ ህፃን ደፍሯል ተብሎ 2 አመት ከምናምን ብቻ ተፈርዶበታል፣ ሌላኛው ደግሞ በህፃን ላይ መድፈር የሚመስል ወንጀል ፈፅመሃል ተብሎ አራት አመት ተፈርዶበታል፡፡ መጀመሪያ ህፃን ደፍረሃል ተብሎ 2 አመት መፈረዱ ገረመኝ፡፡ ህፃን ላይ መድፈር የሚመስል ወንጀል ፈፀመ የሚባለው ደፈረ ከሚባለው በላይ አራት አመት ሲፈረድበትም ገረመኝ፡፡ በመረጃ የተደገፈ ከሆነ የሁለቱም በጣም የሚገርም ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ መድፈር የሚመስል ወንጀል የሚለውን ከመድፈርም በላይ ወንጀል ማድረጉ ምን ያህል በደመነፍስ እንደሚሰራ የሚያሳይ ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ ህፃን መድፈር 4 ወር ብቻ እንደሚያስቀጣ እየተሰማ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ስልክ አስጭሆም ሆነ በሌላ መንገድ ‹‹ችሎት ደፈረ›› የሚባል ሰው በ6 ወር እስር ይቀጣል፣ በጥፊ የተማታ 6 ወር ይቀጣል፣፡፡ ጎትቶ የጣለም እስከ 6 ወር ይቀጣል፡፡ ቀለል ያለ ስድብ የተሳደበ ከ3 ወር ጀምሮ ይቀጣል፡፡ ሰልፍ ላይ ተገኘህ ተብሎ አራት አመት ይቀጣል፡፡ በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ ፓርቲ ፓምፕሌት ሲበትን የተገኘ ሰው ህፃኗን ደፈረ ከተባለው ሰው ከተፈረደበት በላይ ይቀጣል፡፡ የፃፈ 18 አመት ይቀጣል፡፡ እውነቱን የተናገረ 20 አመት ይቀጣል፡፡ እንዲያውም ተደብድቦ፡፡ የደፈረው ይደብደብ እያልኩ አይደለም፡፡ የሚሰጡትን ትኩረት ስለሚያሳይ እንጅ፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ህፃን ቢደፈር ግድ የሚሰጣቸው አይደሉም፡፡ እርጉዝን በስለት ወግተው ፅንስና እናቱን
በጭካኔ ገድለዋል፡፡ ከኦነግ ጋር አርባጉጉ፣ በደኖ… ያደረጉት ይህንን ነው፡፡ ህፃናትን፣ እናቶችን ከቀያቸው
አባርረዋል፣ በእሮፕላን አስደብድበዋል፡፡ ኦጋዴን ላይ ተነግሮ የማያልቅ ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ ከመድፈርም፣
ከማስደፈርም በላይ ገድለዋል፡፡ አስገድለዋል፡፡ ነገሩ እናቶችን፣ ህፃናትን ብቻ ሳይሆን ሀገርም አስደፍረዋል፡፡
ደፍረዋል፡፡ ቤተክርስቲያንና መስጊድን ደፍረዋል፣ ባህልና እምነትንም ደፍረዋል፡፡ አስገድደው እነሱ የሚፈልጉትን
እምነት እንዲያምን እየጣሩ ነው፡፡ አስገድደው ገዳም እያረሱ ነው፡፡ አስገድደው ፖሊስና ካድሬ ጫማውን አጥልቆ
መስጊድ እንዲገባ እያደረጉ ነው፡፡ በአጠቃላይ አስገድዶ መድፈር ፖሊሲያቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ሲደፈሩ
ብቻ ነው ለእነሱ አንገታቸውን ደፍተው የሚገዙት፣ ተሸማቅቀው የሚበዘበዙት! እነዚህ አገር የደፈሩና ያስደፈሩት
ጭራሹን ዘመነኞች ሆነዋል፡፡ ጭራሹን የተደፈሩትን ወንጀል አፈላልገው የማይገባቸውን እየቀጡዋቸው ነው፡፡ እነሱ
የሚዘውሩት ፍርድ ቤት ደግሞ ህፃናትን አስገድደው የሚደፍሩትን በርቱ ተበራቱ! ድፈሩ እያለ ነው!
ጌታቸው ሺፈራው
ጌታቸው ሺፈራው
No comments:
Post a Comment