(ነገረ ኢትዮጵያ) በባሌ ዞን ሰልጣ ቀበሌ፣ ሲናና ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ወርቅነህ ጋድይ አያና የእድር ስብሰባ ላይ ጥያቄ ጠይቀሃል ተብለው መታሰራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የዞኑ አስተባባ አቶ ደመላሽ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ በተለይ ከምርጫው በኋላ ካድሬዎች አቶ ወርቅነህ እድርን ጨምሮ ከማህበራዊ ጉዳዮች እንዳይሳተፉ ጫና ሲያደርጉባቸው እንደነበረም ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም የአካባቢው ህዝብ ‹‹በፖለቲካ መሳተፍ ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው፡፡ እድር ደግሞ ማህበራዊ መብቱ በመሆኑ መሳተፍ አለበት›› በማለቱ እስካሁንም የእድር አባል ሆነው ቢቀጥሉም በእድሩ አካሄድ ጥያቄ አለኝ በማለታቸው ‹‹ለምን ጥያቄ ትጠይቃለህ?›› ተብለው እንደታሰሩ አስባባሪው ገልፀዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ጋድይ በአሁኑ ወቅት በሲናና ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የአስተዳደር አካላት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ በሚፈፅሙት በደል ምክንያት ከትግል ውጭ ፍትህ እናገኛለን ብለው እንደማያምኑ አቶ ደመላሽ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment