‹‹የሕግ አማካሪ የማግኘት፣ የማማከር እና የመከላከል መብታቸው ተጣቧል፡፡››/የወረዳው ምእመናን/
‹‹መታሰር በክርስትና ያለ ነው፤ ክልሉ ጣልቃ እንዲገባ ጥሩ አቅጣጫ ተይዟል፡፡››/የሐዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ/
በኦርቶዶክሳዊ ክርስትናቸው ለሚደርስባቸው በደል መፍትሔ በመሻት የድረሱልን ጥሪ ያሰሙት
በምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የስልጤ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት፣ የሐሰት ወሬዎችን በማሰራጨት ሕዝብን አሸብራችኋል፤ በወረዳው የአስተዳደር አካላት ላይ ጥርጣሬን በማስፋፋት እና የሕዝብን አስተሳሰብ በማወክ በሕዝብ ዘንድ ጥላቻን አነሣስታችኋዋል በሚል እስከ ዘጠኝ ዓመት የእስር ቅጣት ተፈረደባቸው፡፡
በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን የምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በሦስት የወንጀል ክሦች ከ6 – 9 ዓመት የእስር ቅጣት ውሳኔ ያሳለፈባቸው ተከሣሾቹ፣ በሐዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት በምትገኘው የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመራሮች የኾኑ ስድስት ምእመናን ናቸው፡፡
የወረዳው ዐቃቤ ሕግ እንዳስረዳው፣ ‹‹ተከሣሽ ምእመናኑ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 60(ለ)፣ 485(2)፣ 486(ሀ) እና (ለ)፣ 364(1)ለ ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ እና የቤተ ክርስቲያኗን ማኅተም በመጠቀም ለተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልኾኑ ተቋማት ባደረሱት እና ሐራ ዘተዋሕዶ በተባለው ድረ ገጽ ላይ ባሰራጩት የዐመፅ ቅስቀሳ ጽሑፍ ወንጀል ፈጽመዋል፤›› ብሏል፡፡
‹‹የድረሱልኝ ጥሪ›› በሚል ርእስ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተሰራጨውና የስድስቱም ተከሣሾች ፊርማ ያረፈበት ሰነዱ፣ የምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳን 30 ኢትዮጵያውያን በግፍ ከተገደሉበት ሊቢያ ጋር በማመሳሰል ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በመኾናችን ምክንያት ግፍና በደል እየደረሰብን ነው፤ የእምነቱ ተከታይ የኾኑ የመንግሥት ሠራተኞች ያለበቂ ምክንያት ከሥራ መባረር፣ የግድያ ዛቻ እና የተለያዩ በደሎች እየደረሰባቸው ነው፤ በጭንቀት እና በስጋት ላይ ነን፤ መቼ ምን እንደምንኾን አናውቅም፤ ድረሱልን›› በማለት በወረዳው የአስተዳደር አካላት ላይ ጥርጣሬን ያስፋፋና በሕዝብ ዘንድ ጥላቻን ያነሣሣ እንደኾነ በወንጀሉ ዝርዝር ተገልጧል፡፡
ወረዳዋ፣ ፍጹም ሰላም እና የአስተዳደር አካላቱ እና ሕዝቡ፤ የአምልኮ ቦታ አመቻችቶ ከመስጠት አልፎ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ሲጣል ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እንግዶችን በመቀበል እና ለቤተ ክርስቲያኗ ግንባታ ያልተቆጠቡ ድጋፋቸውን እየሰጡ ያሉበት ነው ያለው ዐቃቤ ሕግ፤ ስለ ወረዳው የማያውቁና በኢንተርኔት የተለቀቀውን ጽሑፍ የተመለከቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በወረዳዋ የሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው አደጋ ደርሶባቸዋል በሚል በድንጋጤ እና በስጋት በመውደቃቸው በወሬ ሕዝብን የማሸበር ወንጀል መፈጸሙን ገልጧል፡፡
በወረዳው የተለያዩ ተቋማት የመንግሥት ሠራተኞች የኾኑት አምስቱ ተከሣሾች÷ ማስረሻ ሰይፈ ቤተ ሥላሴ፣ ሙሉጌታ አራጋው ጥሩነህ፣ ሀብታሙ ተካ ዳግሰው፣ ማሩ ለማ አጋ እና ንጋት ለማ ጁታ እያንዳንዳቸው የአምስት ዓመት ከስድስት ወራት የእስር ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፤ በዋና አነሣሽነት የተከሠሡት እና በሌላ ክሥ የተላለፈባቸውን የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት እስር በመፈጸም ላይ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ እና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር መ/ር የማርያምወርቅ ተሻገር፣ በስምንት ዓመት ከስምንት ወራት እስር እንዲቀጡ ነው የተወሰነባቸው፡፡
ቀደም ብሎ በእስር ላይ የነበሩትን መ/ር የማርያምወርቅ ተሻገርን ጨምሮ ስድስቱም ተከሣሾች ካለፈው ዓርብ ከቀትር በኋላ ጀምሮ በወራቤ ዞን ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ ምእመናንና አመራሮች ‹‹የድረሱልን ጥሪ››፣ በእምነታቸው ምክንያት በአንዳንድ ባለሥልጣናት የደረሰባቸውን አድልዎ እና በደል ለቤተ ክህነት እና ለመንግሥት አካላት ለማሳወቅና መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ መዘጋጀቱን በማስታወስ፣ በኢንተርኔት መሰራጨቱ ከሰበካ ጉባኤው እና ከሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው አባላት ዓላማና ፍላጎት ውጭ እንደኾነ የሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት በቂ/ጉ/ቅ/ማ104/07 በቀን 04/11/07 ‹‹ማስተካከያ›› በሚል ርእስ በጻፈው ደብዳቤ መግለጫ ሰጥቶበት እንደነበር ተገልጧል፡፡
ይኹንና የሐዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ የወረዳ እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገናኙበት መድረክ የተፈጠረውን ችግር በመግባባት ለመፍታት እና ከሥሩ ለማድረቅ በተስፋ እየተጠበቀ ባለበት ኹኔታ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ምእመናንና አመራሮች ከሥራ መፈናቀላቸው ሳያንስ ለእስር መዳረጋቸው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ኢትዮ-ምኅዳር ያነጋገራቸው የወረዳዋ ምእመናን ገልጸዋል፡፡ የፍትሕ ሒደቱም ተከሣሾቹ በዘፈቀዳዊ እስር፣ በሽምግልና ሰበብ እና በአጫጭር ቀጠሮ የሕግ አማካሪ የማግኘት፣ የማማከር እና የመከላከል መብታቸው የተጣበበበት እና ከፍተኛ ተጽዕኖ የተደረገበት እንደነበርአስረድተዋል፡፡
ከውሳኔው በኋላም በየምሽቱ በወረዳው አስተዳደር ቢሮ ድረስ እየተጠሩ፣ ‹‹ከዚኽ በኋላ በማንኛውም ነገር አንዳች ስታደርጉ ብናያችኹ አስፈላጊውን ርምጃ እንወስድባችኋለን የሚል ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየተፈጸመብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሥራ ልምድ እና የድጋፍ ደብዳቤ በሚጠይቁበት ወቅትም ሰብአዊ እና የዜግነት መብታቸውን የሚጥስ በደል እየደረሰባቸው እንደኾነና በአገልግሎታቸው ጉልሕ አስተዋፅኦ ያላቸው ጠንካራ ምእመናን በየምክንያቱ ከአካባቢው መራቅን እንደመረጡ አስረድተዋል – ‹‹በሥራ ልምዳችን ላይ አስነዋሪ ቃላት እየጻፉ፣ ይኼም ሲበዛባችኹ ነው፤ ይህንንም እኛ ስለኾን ነው የሰጠናችኹ ይሉናል፡፡››
ቅዳሴ ቤቱን/ምረቃውን/ የሚጠብቀው የቤተ ክርስቲያኑ የዕንጨት እና የሽቦ አጥርም እየተነቀለ ሣሩ በከብት እንዲበላ እየተደረገ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡
‹‹መታሰር በክርስትና ያለ ነው፤ መገፋታችን ጥሩ ነው፤›› ያሉት የሐዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አባ ቢንያም ከበደ በበኩላቸው፣ የፍርድ ቤቱ የውሳኔ ግልባጭ ባይደርሳቸውም ጉዳዩን ለክልሉ አስተዳደር እና ለፍትሕ ቢሮ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠበቃ በማቆም ይግባኝ ለመጠየቅ ማሰባቸውንና ክልሉም ‹‹ነገሩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሩ አቅጣጫ ተይዟል›› ብለዋል፡፡
የወረዳው አስተዳደር በሰጠው ቦታ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መሠረቷ የተጣለውና ሥራዋ የተጠናቀቀው የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት(ምረቃ) ሰኔ 21 ቀን ለማከናወን ታስቦ የነበረ ቢኾንም ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉንና ገና እንዳልተሰወነም ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በስልጤ ዞን ምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ቂልጦ ከተማ በየዕለቱ ከሚደርስባቸው ማሸማቀቅ የተነሣ በጭንቀት ውስጥ የሚገኙትን ኦርቶዶክሳውያን ለማጽናናት፣ ከሐዋሳ እና ከአዳማ የምእመናን ጉዞዎች እየተደረጉ ሲኾን ሰላማቸው እስኪጠበቅ ድረስም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጧል፡፡
Source:: haratewahido
No comments:
Post a Comment