Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, August 28, 2015

ፍርድ ቤቱ አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲቀለቀቅ ወሰነ

ፍርድ ቤቱ አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲቀለቀቅ ወሰነ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የአራዳ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ነሃሴ 22/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት የተደረገውን ሰልፍ አደራጅቶ መርቷል እንዲሁም ለዋናው (ለሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲለቀቅ ወስኗል፡፡
አቃቤ ህግ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም አቶ ማሙሸት ገንዘብ ከፍሎ ወጣቶችን ሰልፍ እንዳስወጣቸው፣ ወጣቶችን እንዳደራጀ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅትም መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን በመሪነት ሲያሰማ እንደነበርና ለሚያዝያ 14 ሰልፍም ሲያደራጅ እንደነበር ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት የሰው ምስክሮችን ማሰማቱ ይታወሳል፡፡
ይሁንና ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የግል ሰራተኛ እንደሆነ በምስክርነት ቃላቸው ቢሰጡም በመስቀለኛ ጥያቄ አንደኛው የመንግስት ሰራተኛ፣ ሁለተኛው የወጣቶች ሊግ ከዚህም አለፍ ሲል የኢህአዴግ አባል፣ ሶስተኛው ደግሞ የጥቃቅንና አነስተኛ ባልደረባ መሆናቸውን በማመናቸው የሰጡት ምስክርነት ትክክል አለመሆኑን ያስረዳል ብሏል፡፡ በተጨማሪም ምስክሮቹ ገዥው ፓርቲን የሚደግፉና የወጣት ሊግ አባል ሆነው ገዥው ፓርቲን የሚቃወም ግለሰብ ላይ የሰጡት ምስክርነት ገለልተኛ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል ብሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር ምስክሮቹ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ሆነው እያለ አቶ ማሙሸት አማረ በተደጋጋሚ ይደውልላቸው እና ይገናኙም እንደነበር የመሰከሩ ሲሆን አቶ ማሙሸት ቀንደኛ የገዥው ፓርቲ ተቃዋሚ ሆኖ እያለ ከመንግስት (ከገዥው ፓርቲ) ቀንደኛ ደጋፊዎች እንዲህ አይነት ግንኙነት ይኖረዋል ብሎ ለማመን እንደማይቻል አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ከ4 አመት ጀምሮ እስከ 7 አመት አዲስ አበባ ውስጥ የኖሩት ምስክሮች ስለ ሰልፉ ባስረዱበት ወቅት ቤተ መንግስትን ጨምሮ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው ራሳቸውን ከመስቀለኛ ጥያቄ ለማዳን ያደረጉት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ገልጾአል፡፡ በመሆኑም የምስክሮቹ ቃል ታማኒነት ስለሌለው አቶ ማሙሸት አማረ መከላከል ሳያስፈልገው በዛሬው ዕለት በነፃ እንዲለቀቅ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማምጣቱ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስከዛሬ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials