በዝናብ እጥረት ምክንያት የምግብ ዋስትና ችግር ለገጠማቸው ወገኖች በውስን ጨረታ የስንዴ ግዥ እንዲፈጸም ተፈቀደ፡፡ በውስን ጨረታ ግዥ መፈጸም በመንግሥት የሚደገፍ ባይሆንም፣ የስንዴው አስፈላጊነት አጣዳፊ በመሆኑ ምክንያት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በውስን ጨረታ ግዥ እንዲፈጸም ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
በዚህ መሠረት የመንግሥትን ግዥዎች በማዕከላዊ ደረጃ እንዲፈጸም የተቋቋመው የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ግልጽ ጨረታ የማውጣት ሐሳቡን በመሰረዝ በውስን ጨረታ የስንዴ ግዥ ለመፈጸም የመጨረሻ ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደሳሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል ስንዴ በማቅረብ ከሚታወቁ 40 ኩባንያዎች መካከል ሰባት ኩባንያዎች በደብዳቤ ይጠየቃሉ፡፡ ነገር ግን እነማን እንደሆኑ በውል አልተለዩም፡፡
“ኩባንያዎች ማቅረብ እንደሚችሉ ካሳወቁና በዋጋ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ሥራው ይሰጣቸዋል፤” በማለት አቶ መልካሙ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች መንግሥት በ2007 ዓ.ም. ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ግዥ የፈጸመው 300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ያቀረቡ ናቸው ተብሏል፡፡
አብዛኛዎቹ የውጭ አገር ኩባንያዎች ሲሆኑ በአገር ውስጥ ካላቸው ወኪል ጋር የሚሠሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ስንዴ ግዥ ጨረታ ውስጥ ከ40 በላይ ኩባንያዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የምሥራቅ አውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእንግሊዝና የሱዳን ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አብረውት ከሚሠሩት ውስጥ ለመረጣቸው ሰባት ኩባንያዎች ብቻ ነው ደብዳቤ በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው፡፡
አቶ መልካሙ እንዳሉት፣ ከሰኞ ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ኩባንያዎቹ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል፡፡ በኤልኒኖ ምክንያት ክስተት በኢትዮጵያ የክረምት ወራት የዝናብ መዛባት ማጋጠሙ ይታወቃል፡፡ በዚህ ምክንያትም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የምርት መስተጓጎል እንዳጋጠማቸው መንግሥት በይፋ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ 222 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲገዛ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህ ስንዴ ከመጠባበቂያ እህል ክምችት ውጭ ተደርጎ እየተከፋፈለ ያለውን ስንዴ የሚተካ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከስንዴ ግዥ በተጨማሪ መንግሥት 700 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ፣ የተለያዩ አስቸኳይ ዕርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ባለፈው ሳምንት ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment