ኢሳት ዜና (ነሐሴ 22 ፣ 2007) ከአራት አመት በፊት የተቋቋመውና አስር የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለማካሄድ ሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው የ 2007 አም በጀት አመት የሰባት ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። የሃገሪቱ ነባር የስኳር ፋብሪካዎች እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው ይኸው ኮሮፖሬሽን ለስራው ማስኬጃ ከተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ለእቃ አቅርቦት መከፈል የነበረበትን ሶስት ቢሊዮን ብር በወቅቱ ሳይከፍል መቅረቱን ታውቋል። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ካጋጠመው ከፍተኛ ኪሳራ በተጨማሪ አቶ አባይ ጸሃዬ ኮሮፖሬሽኑን ለሁለት አመታት ያህል በዳይሬክተርነት ባስተዳደሩበት ጊዜ ከ 800 ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰበት እንዳልታወቀ የድርጅቱ ምንጮች ለኢሳት በሰጡት መረጃ አመልክተዋል። የተከሰተውን የገንዘብ ጉድለት ተከትሎም የድርጀቱ የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ጉዳዩን ለጠቅላላ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ቢሮ በማቅረብ የኦዲት ምርመራ እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል። ይሁንና ጥያቄ የቀረበለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ለጉዳዩ ምላሽ አለመስጠቱን የተናገሩት ምንጮች ለስኳር ኮርፖሬሽኑ ያጋጠመውን የፋይናንስ ቀውስ ተከትሎም በርካታ ሰራተኞች ከድርጅቱ በመልቀቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በአቶ አባይ ጸሃዬ ምትክ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ሽፈራው ጃርሶ በተለያዩ መድረኮች “ የተረከብኩት በቁሙ የሞተ ድርጅት ነው” ሲሉ መግለጻቸውም ተነግሯል። ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙት አቶ ሽፈራው ጃርሶ በቅርቡ የስራ መልቀቂያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንዲያቀርቡ የኮርፖሬሽኑ ምንጮች ለኢሳት አስረድተዋል። የግንባታ ስራዎች በተጋነነ ዋጋ ያለጨረታ መሰጠታቸውና ከተሰጡም በኋላ የዋጋ ልዩነት መጥቷል እየተባለ በድጋሚ የተጋነነ ክፍያ ሲፈጸም በመቆየቱ ኮሮፖሬሽኑ በኪሳራ ውስጥ ከተካተቱ ድርጅቶች ዋነኛው መሆኑን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል። የቀድሞው የኮሮፕሬሽኑ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አባይ ጸሃዬ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው የሚባለውና በቀድሞ GYB ቡቲክ ባለቤት አቶ የማነ ግርማይ የተሰጠው እና ኦሞ በሚገኘው የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በተጋነነ ዋጋና ያለጨረታ ከተሰጡ ግንባታዎች መካከል ምሳሌ መሆናቸውን ምንጮች ማስረጃዎችን በማስደገፍ ለኢሳት አመልክተዋል። ኮርፖሬሽኑ ለሌሎች ኩባንያዎች ክፍያን መፈጸም እንዳማይችል ቢገለጽም ይኸኛው ግንባታ ግን ክፍያ ተቋርጦ እንደማያውቅበት ለመረዳት ተችሏል። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን የተበደረው ብድር መጠን 44 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ምንጮች፣ ድርጅቱ ተጨማሪ ካፒታል ካልተመደበለት የመፍረስ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል አስታውቀዋል። ኮርፖሬሽኑ ለሚዋዋላቸው የተጋነኑ ውሎችና ስምምነቶች ብድሩን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያገኝ መቆየቱም ታውቋል።
No comments:
Post a Comment