መልዕክት በድሆች ድህነት ለመክበር መሯሯጥ ላይ ላሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት !
የግል ኑሮን ለማደላደል ሲባል የወያኔ አባል መሆን “ወይን ለመኖር” የሚል ስያሜ ከተሰጠው ዓመታት ተቆጥሯል። “ወይን ለመኖር” ዜጎች ነፃነታቸውን ለጥቅም አሳልፈው የሚሸጡበት፤ የሰው ልጅ ክብር የሚዋረድበት ገበያ ነው። በወይን ለመኖር “የገበያ ህግ” መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ሊያገኘው መብቱ የሆነውን አገልግሎት እንዲያገኝ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴግ፣ የደህዴግ፣ የአብዴፓ፣ የቤጉህዴፓ፣ የጋህአዴን፣ የሀብሊ ወይም የኢሶዴፓ አባል መሆን፤ አልያም መደገፍ ግዴታ ነው። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የህወሓት ተቀጽላ ወያኔዎች ናቸው። የእነዚህ ድርጅቶች አባል ወይም ደጋፊ ያልሆነ እንኳስ የመንግሥት አገልግሎት ሊያገኝ ጥሮ ግሮ ያፈራውንም ይነጠቃል።
በዚህም ምክንያት፣ በገጠር ያለው አርሶ አደር ቁራጭ የእርሻ መሬት፣ የግብርና ባለሙያዎች የምክር እገዛ፣ የማዳበሪያና ዘር ግዢ፣ ብድር ወይም እርዳታ ለማግኘት በአካባቢው ባለ የወያኔ ድርጅት አባልነት መመዝገብ፤ አንድ ለአምስት መደራጀት እና የወያኔን የስልጣን እድሜ የሚያራዝሙ ነገሮችን መሥራት ይጠበቅበታል። በከተሞች ውስጥም ሥራ ለመቀጠር፣ ለደረጃ እድገት፣ የመኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ለመግዛት ሲባል መወየን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ሆኗል:: በንግዱም ዘርፍ የንግድ ፈቃድ፣ የሥራ ቦታ እና የባንክ ብድር ለማግኝት፣ የመንግሥት ጨረታዎችን ለማሸነፍ፣ ከጉምሩክ እቃ ለማስለቀቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መወየን ግዴታ ነው።
“ወይን ለመኖር” የኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋረደ፤ ለትውልድ የሚተርፍ የማኅበራዊ ስነልቦና ኪሳራ ያደረሰ እና ደካማውን ወያኔን ጠንካራ በማስመሰል በሕዝብ የትግል መንፈስ ውስጥ ፍርሃትን የረጨ መሆኑ ግንዛቤ እየዳበረ በመጣ መጠን እየቀነሰ የመጣ ክስተት ነው። በአሁኑ ሰዓት ከቀድሞው እጅግ በተሻለ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን ከህወሓት ባርነት እያላቀቅን ምሬታችንን በግልጽ መናገር የጀመርንበት ወቅት ነው፤ ከዚያም አልፎ የህቡዕ ተግባራዊ የትግል እንቅስቃዎችን ማድረግ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
አገር ውስጥ እየተዋረደ የመጣው “ወይን ለመኖር” በአገዛዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን (ዲያስፓራ) መካከል ነፃነታቸውን በጥቅም የሚለውጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ፍለጋ ተሠማርቷል። አገዛዙ ተስፋ ያደረገው ያህል ባይሆንም ጥረቱ የተወሰነ ውጤት እያስገኘለት ነው። በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ካመጣቸው ውስጥ በስርዓቱ ብልሹነት ያዘኑና የተሰማቸውን በግልጽ የተናገሩ መኖራቸው የሚያስደስትና የሚያበረታታ ቢሆንም ከመንደር ካድሬዎች ባነሰ ተለማማጮችና አጎብዳጆች በማየታችን ተሸማቀናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለነው አብዛኛው ሕዝብ አንፃር ሲታይ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ዲያስፓራዎች መካከልም ነፃነታቸውን በጥቅም ለመለወጥ የሚፈቅዱ መገኘታቸው አሳዛኝ ነው። እነዚህ ክብራቸውን በጥቅም የለወጡ ዲያስፓራዎች ዓለም ባንክንና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (IMF) ተክተው ህወሓት ስላስገኘው ፈጣን እድገት በአገዛዙ ራድዮ እና ቴሌቪዥን ሲነግሩን መስማት ያሳፍራል። የህወሓት አገዛዝ “ፍትህን፣ መልካም አስተዳርንና ዲሞክራሲን አስፍኗል፤ ይህንንም መጥተን በዓይኖቻችን ተመልክተናል” እያሉ የግፉን ገፈት እየቀመስን ላለነው ሲነግሩን መስማት ያማል።
እነዚህ ወገኖቻችን ህወሓትን በማሞካሸት የሚያገኙት መሬት ብዙ ድሆች የተፈናቀለቡት፤ ለእነሱ በብላሽ የተሰጠው ብድር በረሃብ ለሚጠቃ ወገን የተላከ እርዳታ መሆኑ ማሳሰብ ይገባል። ከህወሓትና አጫፋሪዎቹ ጋር ተስማምተው ባገኙት ገንዘብ የሚቆርሱት እያንዳንዱ እንጀራ የብዙ ወገኖቻችን ደምና እንባ የፈሰሰበት መሆኑ ማስገንዘብ ያሻል። ከህወሓት ጋር በማበር በወገኖቻችን ድህነትና ችጋር እየከበሩ ያሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት ከዚህ እኩይ ሥራቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቅ ይገባል። እኚህ ወገኖች የራሳቸው ክብር ማጉዳፋቸውን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸውም የሚያፍሩባቸው መሆኑን ማስታወስ ይገባል። ከዚህም አልፎ የዛሬ ተግባራቸው ነገ በህግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የአገዛዙን እድሜ በማራዘም ላይ የተሰማሩ፤ በድሆች ድህነት ለመክበር በመሯሯጥ ላይ ያሉ፤ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለአገዛዙ ጥብቅና የቆሙ የዲያስፓራ አባላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 “ከህወሓት ውድቀት በኋላ ያለው ጊዜ ለእናንተም ከዛሬው የተሻለ ይሆናል። ዛሬ ከህወሓት ጋር ያላችሁን ሽርክና አቋርጡ። ለነፃነት የሚደረገውን ትግል እርዱ፤ መርዳት ባትችሉ እንቅፋት አትሁኑ፤ አለበለዚያ ግን ከተጠያቂነት የማታመልጡ መሆኑን እወቁ” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!! !
No comments:
Post a Comment