የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን
‹‹የበጀት ዓመቱን ሒሳብ ዘግቼ ለመመርመር ሰባት ቀን ሲቀረኝ ተዘዋውሬአለኹ››/ሒሳብ ሹሟ
- በኹለት ዓመት ውስጥ ለደብሩ ከብር 18 ሚልዮን በላይ ተቀማጭ አስመዝግቤአለኹ
- የተነሣሁት ሕገ ወጥ ክፍያዎችን በመቃወሜ እና ምዝበራዎችን ለመሸፋፈን ሲባል ነው
- ሕገ ወጥ አሠራር ቢረጋገጥም ውሳኔ አያገኝም፤ በአጥፊዎችም ላይ ርምጃ አይወሰድም
- የሰነዶቹ ደኅንነት ታይቶ ቢሮዬ ይታሸግልኝ፤ መንግሥት ኦዲተሮችን መድቦ ያጣራልኝ
- በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚፈጸሙ አደገኛ አሠራሮች ቀርቤ በቃል እንዳስረዳ ይመቻችልኝ
* * *
- የሀገር ሀብት በባለሥልጣናት በሚያስፈራሩት ዋ/ሥ/አስኪያጁ ሲዘረፍ ማየቱ አደጋ ያስከትላል
- የየማነ ቢሮ የንግድ ማስታወቂያ አልተለጠፈበትም እንጂ የሰው ዘር መሸጫ መደብር ኾኗል
- ለፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ የኮቴ ይከፈላል፤ እስከ ግማሽ ሚልዮን እንዲሰጣቸው በቃል ያዛሉ
- ፓትርያርኩ ሙስና ይጥፋ ቢሉም ከሚዲያ አላለፈም፤ በሥራ እንጂ በሚዲያ አይጠፋም
/ሒሳብ ሹሟ ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም/
(ምንጭ፡- ኢትዮ-ምኅዳር፤ ቅጽ ፫ ቁጥር ፻፲፬፤ ቅዳሜ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን
ከብዙኃን ምእመናን የተሰበሰበ በብዙ ሚልዮን ብር የሚገመት የቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት አላግባብ ተመዝብሮበታል የተባለው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሒሳብ፣ በገለልተኛ እና ሕጋዊ አካል በይፋ እንዲመረመር ተጠየቀ፡፡
ሓላፊነትን አላግባብ በመጠቀም እና የሒሳብ አያያዝ እና የንብረት አጠባበቅ ድንጋጌዎችን በመጣስ በደብሩ አስተዳደር ተፈጽሟል በተባለው ምዝበራ እና ብክነት÷ ጥናት እና ጥራት ለጎደላቸው ሥራዎች ከፍተኛ ወጪዎች ይታዘዛሉ፤ ከተመደበው እና ከተወሰነው ውጭ በሕገ ወጥ ትእዛዝ የደብሩን ካፒታል የሚንዱ የተለያዩ ክፍያዎች ይፈጸማሉ፤ ለተከራይ በሚያደሉ እና የደብሩን ጥቅም በሚጎዱ የሕንፃ ኪራይ ውሎች ግለሰቦች መቶ ሺሕዎችንና ሚልዮን ብሮችን ያካብታሉ፤ በዐውደ ምሕረት በምንጣፍ አና በስእለት የተሰበሰበ ገንዘብ በአግባቡ ሳይቆጠር እና በሞዴል ገቢ ሳይኾን እየተወሰደ የገባበት አልታወቀም፡፡
ከኹለት ዓመታት በላይ የደብሩ ሒሳብ ሹም ኾነው ሲሠሩ የቆዩት ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም÷ የተሰበሰበው ገንዘብ የት ገባ ብለው በመጠየቃቸው ያለምንም ማጣራት እና ቅድመ ኹኔታ፣ ንብረት እና መዛግብት አስረክበው ወደ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው እንዲሠሩ ባለፈው ሰኔ 22 ቀን ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መታዘዛቸውን ይናገራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት በመኾኗ በተዛወሩበት ደብር ለመሥራት ፈቃደኛ ቢኾኑም፣ የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሊዘጋ ሰባት ቀናት ሲቀሩት ዝውውር የተደረገበትን አሠራር ግን እንደሚቃወሙት ገልጸዋል፡፡
የሒሳብ ሠራተኛ የተመረመረ ሰነድ ማስረከብ እንዳለበት ሒሳብ ሹሟ ጠቅሰው፣ ከመጋቢት/2005 ዓ.ም. ጀምሮ እስከተዘዋወሩበት ሰኔ 22/2007 ዓ.ም. ድረስ በደብሩ በቆዩባቸው 27 ወራት ከብር 54 ሚልዮን በላይ ገቢ እና ወጪ የሠሩባቸው፤ ከብር 18 ሚልዮን በላይ ተቀማጭ ያስመዘገቡባቸው የሒሳብ ሰነዶች እና መዛግብት በይፋ እንዲመረመሩ በአድራሻ÷ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና ለዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በጻፉትና በግልባጭ ደግሞ ለሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ለመንግሥት የደኅንነት አካላት ባደረሱት ሰፊ ጽሑፍ ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ መና እንደሚሉት፣ ሰነዶቹ እና መዛግብቱ ያልተመረመሩ ብቻ አይደሉም፡፡ የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመጣስ ተፈጽሟል የሚሉት የአስተዳደርና የፋይናንስ አሠራር ችግር እንዲጣራ ለፓትርያርኩ ባቀረቡት አቤቱታ መነሻነት ያለአግባብ የባከነውና የተመዘበረው የብዙኃን ምእመናን ገንዘብ በሀ/ስብከቱ በሚመደቡ ሠራተኞች ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ መመሪያ የተሰጠበት ከፍተኛ ክሥ ያለባቸው ሰነዶች እና መዛግብትም ናቸው፡፡ ይህንንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ከመሾማቸውም በፊት እንደሚያውቁት ያወሱት ሒሳብ ሹሟ፣ ሳይመረመሩ ከብር 54 ሚልዮን በላይ ገቢና ወጪ የሠራኹባቸውን ሰነዶች እና መዛግብት እንደ ቀላል ወረቀት አስረክበው ይውጡ ማለት ‹‹ከአንድ ተቋም ሓላፊ የሚጠበቅ አይመስለኝም፤ አጥፊዎቹ ወገኖቼ ናቸውና ተደብስብሶ እንዲቀርላቸው በማሰብ ነው፤›› ይላሉ፡፡
በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት የሒሳብ ብክነቱን ለማጣራት፣ የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር ዋና ክፍል ሓላፊ ባሉበት ልኡክ በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ምርመራ ቢካሔድም ውጤቱ የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ሒሳብ ሹሟ ይገልጻሉ፡፡ ሓላፊው እንኳንስ በደብዳቤ ለምርመራ ተልከው ገንዘብ ጠፋ፤ ንብረት ባከነ ሲባል አጣርተው ለውሳኔ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት ሒሳብ ሹሟ፣‹‹ቁጥጥር ሳይኾን ቁጥርጥር ነው የያዙት›› ሲሉ ይወቅሷቸዋል፡፡
ውሳኔን በውሳኔ በመሻር ከደብሩ የሕንፃ ገቢ ላይ ከብር ስድስት ሚልዮን በላይ ወደ ግለሰቦች ኪስ መግባቱ፤ በውል ላይ ውል በመዋዋል ከአንድ የሕንፃ ኪራይ ብቻ ብር 487,869.32 መመዝበሩ ለቋሚ ሲኖዶሱ ካቀረቧቸው አቤቱታዎች እንደሚገኙበት ሒሳብ ሹሟ ይዘረዝራሉ፡፡ ይህንንም የሕንፃ አጣሪ በሚል ተሠይሞ በደብሩ ጽ/ቤት ለተገኘ ሌላ ኮሚቴ ከመዝገብ ቤት ፋይል እያስቀረቡ በጋራ በማየት መተማመን ላይ ቢደርሱም ‹‹እስከ አኹን ውጤቱ የት እንደደረሰ አይታወቅም›› ይላሉ፡፡
ሒሳብ ሹሟ በስፋት ከዘረዘሯቸውና በየጊዜው በሚካሔዱ ማጣራቶች ቢረጋገጡም ውጤት ላይ አልተደረሰባቸውም ካሏቸው ሕገ ወጥ አሠራሮች መካከል፡- የቀድሞው አስተዳዳሪ ባልተሾሙበት ዘመን ወደ ኋላ እየተመላለሱ አግባብነት የሌለው ወጭ አድርገዋል፤ በአንድ ወር ከአበልና ከነዳጅ ውጭ እስከ ብር 8,000 በሠንጠረዥ እየፈረሙ ወስደዋል፤ ለአንድ የሰበካ ጉባኤ አባል በወር እስከ ብር 30,000 ወጪ ተደርጓል፤ የበዓል መዋያ ድጎማ ተከፍሏል፤ በሰበካ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቱ ተወካይ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ ቅጥረኛ ተደርገዋል፡፡
ጥራት ለሌለው የሕንፃ ጠርዝ መሠረት ሥራ፣ ጄኔሬተር ለማዘዋወር፣ ለመኪና እድሳት፣ ለካህናት ጊዜያዊ ቤት ሥራ ጥናት የጎደላቸው ወጭዎች ተደርገዋል፤ በሰኔ 2006 ለኹለት የሰበካ ጉባኤ አባላት ብር 250,000 በአስቸኳይ ወጭ ኾኖ ያለደረሰኝ በሞዴል 6 እንዲከፈል ሕገ ወጥ ትእዛዝ በማዘዝ፤ በነሐሴ 2006 ለደመወዝ ከተወሰነው በላይ በልዩነት ከብር 236,000 በላይ ወጭ በማድረግ የደብሩ ካፒታል ተንዷል፤ የደብሩ ጠበቃ በፍርድ ቤት የተከሰሱ ተከራዮች ውዝፍ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ለማድረግ ሲዳረስ ክሡን በይቅርታ በማንሣት በምትኩ የደብሩ ገቢ ለግል ጥቅም ውሏል፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ወ/ሮ መና እንደሚገልጹት፣ የተጣሩት ሕገ ወጥ አሠራሮች ውሳኔ ሳያገኙ በመቅረታቸው እና ርምጃ ባለመወሰዱ ‹‹ያለፉት አጥፊዎች ምን ተደረጉ?›› በማለት በወቅቱ የደብሩ እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ የተለቀቀ ሱቅ በጨረታ ማከራየት ሲገባቸው ሽያጭ አካሒደዋል፤ ቤተሰቦቻቸውን አስቀጥረዋል፡፡ በሚያዝያ 22 እና ግንቦት 22 የቅዱስ ዑራኤል ክብረ በዓል በዐውደ ምሕረት አስተዳዳሪው በተቀመጡበት ምንጣፍ እና በስእለት ከምእመናን የተሰበሰበ ገንዘብ ሳይቆጠርናበደረሰኝ(በሞዴል 30) ገቢ ሳይደረግ በሻንጣዎች ተሞልቶ ተወስዷል፤ የት እንደገባም አይታወቅም፡፡
የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራው በባንክ የመቁጠሪያ ማሽን እንዲከናወን የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በየስብስባው መመሪያ እንደሚሰጡ የጠቀሱት ሒሳብ ሹሟ፣ በዐውደ ምሕረት በምንጣፍ እና በጥላ ስለተሰበሰበው ገንዘብ ቢጠየቅም ሀገረ ስብከቱ እንኳ እንዲያጣራ አለመፈለጉን ይገልጻሉ፡፡ ሒሳብ ሹሟ ለምን በማለት ይጠይቁና ምላሹን ራሳቸው ሲሰጡ ‹‹ፈቃጁ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በመኾናቸውና አያገባችኹም ስላሉ›› ብለዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ መና፣ በማጣራት የተረጋገጡ ጥፋቶች ተገቢው ርምጃ የማይወሰድባቸው፣ የደብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች ለበላይ አካል ያለትእዛዝ በሚያቀርቧቸው ማባበያዎች ስለሚሸፋፈኑ ነው፡፡ የደብሩ ሒሳብ ክፍል ሳያውቀው፣ ገንዘብ ከባንክ ሳይወጣ በዋና ተቆጣጣሪው አማካይነት ከዕለት ገንዘብ ተቀባዮች በብድር በተወሰደ ብር 430,000 ለፓትርያርኩ ቢሮ በስጦታ የተበረከተው ሶፋ፣ ሒሳብ ሹሟ በጽሑፉ ካሰፈሯቸው ኹለት ማባበያዎች የመጀመሪያው ሲኾን የቅዱስ ዑራኤል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በማይመለከተው እና ባልታዘዘበት በቀድሞው አለቃ የሥራ ዘመን የተፈጸመ ነው፡፡
‹‹ለአባቶች ራት ግብዣ›› በሚል በሰበካ ጉባኤው የተወሰነውን ብር ስድሳ ሺሕ ወጪ ከማወራረድ ጋር በተያያዘ ከወቅቱ የደብሩ አለቃ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ወ/ሮ መና በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ እንደ እርሳቸው፣ መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓትርያርኩ ቢሮ ለተደረገው የመስተንግዶ ወጭ የሚያስፈልገው ብር 38,611.66 ሲኾን አስተዳዳሪው፣ ‹‹ለምግብ ማስገቢያ የኮቴ የከፈልኩትን አብረሽ አወራርጂ፤ ገንዘቡ ተወስኖና ተፈቅዶ ከባንክ ወጪ ኾኗል›› በማለት እንዳዘዟቸው ጠቅሰዋል፡፡
ሒሳብ ሹሟ አክለውም ‹‹ደረሰኝ የሌለው የኮቴ ወጪ አላወራርድም ብዬ ስላልተግባባን ሕጋዊው ሰነድ ሳይወራረድ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ለዘጠኝ ወራት ከቆየ በኋላ ተወራርዷል፤›› ካሉ በኋላ ‹‹የኮቴ ክፍያውም በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ተፈጻሚ ይኾናል›› ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቷ በዚኽ መልክ ያለደረሰኝ ወይም ያለሞዴል 6 እየተመዘበረች እንደምትገኝ ያስታወቁት ወ/ሮ መና፣ ‹‹ሕገ ወጥ ኾኖ አላወራርድም ያልኩት የፓትርያርኩን መመሪያ ወደ ተግባር የለወጥኩ መስሎኝ የነበረ ቢኾንም በእንደራሴ ነን ባዮች የሚፈጸምብኝን ደባ አላሰብኩትም ነበር፤›› በማለት በደብሩ የፋይናንስ አሠራር ላይ ያቀረቧቸው አቤቱታዎች በዝውውር ሽፋን ተድበስብሰው እንዳይቀሩ ተማፅነዋል – ‹‹ምርመራው በቤተ ክህነቱ ሳይኾን መንግሥት በሚመድባቸው ኦዲተሮች ከመሠረቱ ከመጋቢት 2005 እስከ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ እንዲደረግልኝ እፈልጋለኹ፤ ቢሮዬም ተሰብሮ ሰነድ እንዳይወጣ ሕጋዊ የመንግሥት አካል ባለበት እስከ አኹን ያለው ደኅንነት ታይቶ እስኪመረመር ድረስ እንዲታሸግልኝ፤ ለማሳያነት ካቀረብኋቸው ጉዳዮች ባሻገርም በቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሚፈጸሙ አደገኛ አሠራሮች በአካል ቀርቤ በቃል ለማስረዳት እንድችል ይደረግልኝ ዘንድ እጠይቃለኹ፡፡››
በወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ‹‹እንደራሴ ነን ባዮች›› የተባሉት፣ በቤተ ክህነቱንም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር ፓትርያርኩን በወሳኝነት ያማክራሉ የተባሉ ሦስት የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን (መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ፣ መልአከ ብርሃናት ዘካርያስ ሓዲስ እና መልአከ ገነት ተስፋ ፍሥሓ) እንደኾነ በጽሑፋቸው ተመልክቷል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ሹመታቸው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ቢኾንም ‹‹በምስጢር ለመላው ኢትዮጵያ ነው›› እንዳሏቸው ወ/ሮ መና ጠቁመው፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና እንደራሴ ነን ባዮቹ በሚሏቸው ብቻ እንዲሠሩ ለፓትርያርኩ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጣቸው በሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ‹‹በዘመናዊ የሙስና አደረጃጀት›› እየተመራ እንዳለ ገልጸው፣ ከዝውውር አሠራር ጋር በተያያዘ በአንድ አካባቢ ተወላጅ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ባለው የአስተዳደር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ‹‹የሰው ዘር መሸጫ መደብር ኾኗል›› ይላሉ፡፡ የፓትርያርኩ የፀረ – ሙስና ዐዋጅ ከሚዲያ ፍጆታነት እንዳላለፈ ተችተው፣ ሙስና በሥራ እንጂ በሚዲያ እንደማይጠፋ የሚገልጹት ሒሳብ ሹሟ፣ ችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው ወደፊት ቤተ ክርስቲያኒቷን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላት አሳስበዋል፡፡
ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ተዛውረው በተመደቡበት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሒሳብ ሹም የነበሩት ሠራተኛ፣ በሰነድ ማጭበርበር በተፈጸመ ከፍተኛ የእምነት ማጉደል ወንጀል ተከሠው በሰኔ ወር መጨረሻ የተላለፈባቸውን የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት የእስር ቅጣት በመፈጸም ላይ እንዳሉ ተገልጧል፡፡
Source:: haratewahido
No comments:
Post a Comment