Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 2, 2015

ለ3ኛ ጊዜ በመንግስት ቤቱ የፈረሰበት ወጣት ራሱን አጠፋ


ለ3ኛ ጊዜ በመንግስት ቤቱ የፈረሰበት ወጣት ራሱን አጠፋ

‹‹የሳምንት አራስ ጎዳና ላይ ወድቃለች››




‹‹የሳምንት አራስ ጎዳና ላይ ወድቃለች››

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎላ መንደር ‹‹ህገ ወጥ የቤት ግንባታ›› በሚል በመንግስት ለሶስተኛ ጊዜ ቤቱ የፈረሰበት ወጣት ታምራት ታንቱ ባሳ ራሱን ማጥፋቱን ምንጮች ከሶዶ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ወጣት ታምራት ታንቱ ባሳ በዚህ መንደር ረዘም ላለ ጊዜ እንደኖረ የገለፁት ምንጮች ለሶስተኛ ጊዜ ‹‹ህገ ወጥ ግንባታ ነው›› ብለው እንዳፈረሱበት አቶ ታደመ ፈቃዱ የተባሉ የሶዶ ነዋሪ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

በተደጋጋሚ ቤቱ በመንግስት የፈረሰበት ታምራት ታንቱ ‹‹በዚህ ሁኔታ እንዴት ብዬ እኖራለሁ?›› ብሎ ራሱን ያጠፋው ነሃሴ 24/2007 ዓ.ም ሲሆን በትናንትናው ዕለት የቀብር ስነ ስርዓቱ እንደተፈፀመም አቶ አበራ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ገልጸውልናል፡፡

በሶዶ ከተማ ህገ ወጥ ናቸው ተብለው ከ500 በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን የገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎቹ አብዛኛዎቹ ከአምስት አመት እስከ ዘጠኝ አመት በአካባቢው ኖረውበታል ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ የተነገረ ሲሆን ሚሚ ባቴ የተባለች የሳምንት አራስም ቤቷ ስለፈረሰባት ጎዳና ላይ ወድቃለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ትናንት ነሃሴ 25/2007 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት በሶዶ ከተማ ቅዳሜ ገበያ በሚባለው የገበያ ማዕከል ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ በርካታ የንግድ ቤቶች መውደማቸውን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials