Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, September 28, 2015

ግብጽ የአባይን ግድብ ለመቆጣጠር በ43 ሚልዩን ዶላር ሳታላይት አምጥቃለች

ግብጽ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የምትገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የሚቆጣጠር ሳታላይት ካመነጨች ረዘም ያለ ግዜ ተቆጥሯል፡፡ የኦን ላይን ጋዜጣ የሆነው ናይል አሃራም የግብጽን የስፔስ ሳይንስና የብሄራዊ ደህንነት ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑትን አላኤል ዲን አልናሃሪን በመጥቀስ ባወጣው ዘገባው የሳታላይቱ ዋነኛ ስራ ግንባታውን የተመለከቱ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን በምስል የተደገፉ ማስረጃዎችን ማቅረብ ነው፡፡ ግብጽ ከሩሲያ እንደሸመተችው ለተነገረለት EGYSAT 43 ሚልዩን ዶላር ወጪ አድርጋለች፡፡ሳታላይቱ የኢትዮጵያን ግድብ ከመቆጣጠር በተጨማሪ ተመሳሳይ ፕሮጀክት የተቀረጸለትን የኮንጎውን የናይል ወንዝም እንደሚቆጣጠር ተነግሮለታል፡፡ በሳታላይቱ አማካኝነት ግብጽ ማናቸውንም አይነት ጥቅሟን የተመለከተ ነገር ሲፈጸም ካገኘችም መረጃዋን በማጠናቀር ወደ ክስ ልታመራበት ትችላለች ተብሏል፡፡ ግብጽ አባይ ላይ እየተሰራ የሚገኘውን ግድብ ለመቆጣጠር በማሰብ ሳታላይት ማምጠቋን የዘገቡት የአገሪቱ ጋዜጦች ብቻ አይደሉም፡፡ሳታላይቱን የሸጠችው ሩሲያም በሚዲያዎቿ አማካኝነት ነገሩን ይፋ አድርጋለች፡፡ታስ የተሰኘ የሩሲያ ድረ ገጽ ባወጣው ዘገባ ሩሲያ ያመረተችውና ሶዩዝ ሮኬት ሳታላይቷን ጭኖ መጥቋል ብሏል፡፡ 1.050 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሳታላይቱ ዋነኛ ተልእኮው ምድር ላይ አሰሳ ማድረግ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ሪዞሊሽን የተገጠመለት በመሆኑ ከሳታላይቱ የሚገኙት የምስልና ተንቀሳቃሽ መረጃዎች ያለ ችግር ሁኔታዎችን ለመለየት የሚያስችሉ ይሆናሉ፡፡ለእርሻ፣ለአካባቢ ሳይንስና ለከርሰ ምድር ጥናት ታስቦ ሳታላይቱ መገንባቱንም ታስ ጨምሮ ዘግቧል፡፡ እንደ ታስ ዘገባ ከሆነም ሳታላይቱ የተገነባው ለ11 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ነው፡፡በኢትዮጵያ በኩል በዋናነት የግድቡን ሂደት እንዲቆጣጠር ግብጽ ባመጠቀችው ሳታላይት ዙሪያ የተሰጠ በጎም ይሁን ተቃራኒ አስተያየት አልተመዘገበም፡፡የስፔስ ሳይንስ አስገራሚ በሆኑ ግኝቶችና ታሪኮች የተሞላ ስለመሆኑ የሚናገሩ የዘርፉ ባለሞያዎች ግብጽ ሳታላይቱን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ስለላዎችን ልታደርግም ትችላለች ይህም በግድቡ ዙሪያ የበላይነት እንዲኖራት ሊያደርግ ይችላል ይላሉ፡፡ የግብጽ መንግስት ለዚሁ አገልግሎት ባመጠቀው ሳታላይት አማካኝነት የግድቡን ግንባታ በቅርበት እየተከታተለ ለመሆኑ በቅርቡ የወጣ መረጃ በእማኝነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የግብጽ ጋዜጦች በካይሮና ጊዛ በተባሉ አካባቢዎች የተፈጠረን የውሃ እጥረት ከግድቡ በውሃ መሞላት መጀመር ጋር በማያያዝ ዘግበው የነበረ ቢሆንም የግብጽ የአፈር ጥበቃ ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ በመስከረም ወር አጋማሽ የተወሰደን የሳታላይት የምስል ማስረጃን በመጥቀስ የጋዜጦቹ ዘገባ ስህተት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ የግድቡ ግንባታ ለግብጽ መንግስት ከፍተኛና ቅድሚያ የሚቸረው ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡የፕሮጀክቱ እቅድ ይፋ ከተደረገበት ወቅት አንስቶም ወደ አስዋን ግድብና ወደ አገሯ የሚገባው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ ስትከራከር መቆየቷም ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ በመስማማት አለም አቀፍ አማካሪ ቡድኖችን በመቅጠር በግድቡ ዙሪያ ጥናት እንዲያቀርቡ ቢያዙም ዴልታርስ የተሰኘው የሆላንድ ድርጅት በቂ የሆነ የስራ ዋስትና አልተሰጠኝም በማለት ራሱን ማግለሉ አይዘነጋም፡፡


No comments:

Post a Comment

wanted officials