ሙጋቤ ጥቁሮች በነጮች ተይዘው የነበሩ የእርሻ መሬቶችን እንዲወስዱ ማድረጋቸውና ለነጮች አለማጎብደዳቸው አፍቃሪ አፍርቶላቸዋል፡፡ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የጤንነት መቃወስ በአደባባይ መሬት ለመሬት ሲጎትታቸው ቢታይም ሙጋቤ የአረጀ አንበሳ ግሳታቸውን በግል ጠባቂዎቻቸው ላይ በማንቋረር ሲያባርሩና ሲያስሯቸው ቆይተዋል፡፡
አስቂኙ ነገር ደግሞ ሙጋቤ አንዷን ዚምቧቡዌን ለመምራት አቅም ከድቷቸው እየተመለከትን በአፍሪካ ህብረት የተሰገሰጉ ጓዶቻቸው ህብረቱን እንዲመሩ መርጠዋቸዋል፡፡የአህጉሪቱ ድርጅት የባለስልጣናቱ ከገላ ማከኪያነት ያለፈ ሚና ቢኖረው ሙጋቤ የአፍሪካዊያን ፕሬዘዳንት ይሆኑ ነበር ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም ዛሬ ከወደ ሐራሬ የሙጋቤን እርጅና የሚያሳብቅ ተጨማሪ ዜና ተገኝቷል፡፡ከወር በፊት ለፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ አቅርበውት የነበረን ወረቀት በዛሬው የፓርላማ ውሎም በድጋሚ አንብበውታል፡፡ሙጋቤ ወረቀቱን ሲያነቡት ለማስታወስ እንኳን አለመቻላቸውም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡የፕሬዘዳንቱ ጽ/ቤት በኋላ ላይ ባወጣው ማስተባበያ ‹‹ስህተቱ የተፈጸመው ሙጋቤ ለዛሬው ፓርላማ ለማንበብ ያዘጋጁት ወረቀት ከባለፈው ወር ጋር በመደበላለቁ ነው፡፡ስህተቱ በዋናነትም የሚመለከተው ጸሐፊያቸውን ነው››ብሏል፡፡
አንድ አስቂኝ ነገር እንጨምር በፓርላማው የዛኑ ፓርቲ ተመራጭ የሆኑ አባላትም በፕሬዘዳንቱ ንግግር ዙሪያ ሞሽን ለማድረግም ተዘጋጅተው ነበር፡፡ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ‹‹ሰውዬው ወንበሩ ላይ እስኪሞት መጠበቅ አይገባንም እናም በቃኝ ይበሉ››ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
No comments:
Post a Comment