Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 23, 2015

ከስህተት ወደ ጥፋት የተሸጋገረው የቋንቋ ግድፈታችን!





ከስህተት ወደ ጥፋት የተሸጋገረው የቋንቋ ግድፈታችን!
(የትነበርክ ታደለ)
ከቅርብ አመታት ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለው የቋንቋ ግድፈትና የቋንቋ አጠቃቀም ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ህጻናትን "አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ሁለቱም ወንጀል ናቸው።" ብሎ እስከ ማስተማር የደረሱ ትምህርት ቤቶችን አፈራን። ስህተት ነው ይታረም ስንል ተንጫጫን~ ችግሩ ግን ዛሬም ድረስ ተሸፋፍኖ እንዳለ ነው።


ቀጠለና በየአደባባይ የምንለጥፋቸው የህዝብ ማስታወቂያዎች ላይም ስህተት የማይመስሉና ሆን ተብለው የሚደረጉ እስኪመስሉ ድረስ ቃላት ማጣመምና ፊደላት መግደፍን ስራዬ ብለን ተያያዝነው። ለዚህም የትኛውም የሚመለከተው ክፍል መልስ ሳይሰጥ እኛም በዋዛ ፈዛዛ አለፍነው።

በተለይ ደግሞ ሰሞኑን የኤሌክትሪክ ባቡሩን ስራ መጀመር ተከትሎ ለአካባቢ መለያነት የተለጠፉት ታፔላዎች ፍጹም ወንጀል በሆነ መልኩ በሁሉም አቅጣጫዎች በህዝብ ፊት ተለጣጥፈው እያየን ነው። ለዚህም እስካሁን ሀላፊነት የወሰደ አላየንም።

እነዚህን እንደ ተራ ስህተት ብንወስዳቸውም ከጅምሩም እንዳይፈጠሩ ብቃት ባላቸው ሰዎች ማሰራት ይቻል ነበር።

ከሁሉ በላይ የሚያሳስበው ግን ለዘመናት ራሱን ችሎ ለብዙ አዳዲስ ጽንሰ ሀሳቦችም ሆነ ቁስ አካል ሁነቶች ስያሜ ሲወልድ የኖረን ቋንቋ በፍጹም ሊወከል በማይገባው በባእዳን ቋንቋ ሲተካ ማየት ከግርምትም በላይ እጅግ በጣም ይከነክናል።


አሁን "የህዝብ መጓጓዣ" የሚለውን ሀረግ "ፐብሊክ ትራንስፖርት" ብሎ ማለት ምን ማለት ነው? ያውም በቋንቋው ፊደላት። ይህ ምንድነው? ስንፍና? ንቀት? ምን አገባኝ? ምን ታመጣላችሁ? ጥላቻ? ወይስ ምን?

እጅግ በጣም ይገርማል! ይህ ስርአት ራሱን ከሚገልጽበት ዋናው ባህሪ የቋንቋን መብት ማስከበር ነው። ሀገር ወለድ ቋንቋዎች በትምህርትና በጥናት ተደግፈው እንዲያድጉና ተናጋሪዎቹም ያለምንም መሸማቀቅ እንዲገለገሉበት ማስቻል "በትግል አስገኘሁት" የሚለው አንዱ ውጤት ነው።

አማርኛ ቋንቋ ደግሞ የፌደራል የስራ ቋንቋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይበልጥ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት የሚገባና ሁላችንም ጥብቅና ልንቆምለት የሚገባ እንጂ እንዲህ መዘባበቻ ሊሆን የሚገባው ቋንቋ አይደለም። በፍጹም!!

እና ምንድነው የምንሰማውና የምናየው ነገር? ለምንድነው ለምንፈጥራቸው ችግሮች ሀላፊነት የማንወስደው? ለምንድነው ያለንን ነገር ለመጣልና ለማስጣል የምንራወጠው? ለምን?

ይህ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም! እንደ ቋንቋ መምህርነቴ ፊደል አስጠንቼ፣ ቃላት አስመስርቼ አረፍተ ነገር ብሎም አንቀጽ ጻፉ ብዬ ያስተማርኳቸው ተማሪዎች እንዲህ ያለ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የማይሰራውን አይነት ስህተት በየጎዳናውና በየአገልግሎት መስጫው ሲገጥማቸው ሳይ እኔ ስለነሱ አዝናለሁ።

ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ሊያመጣ የሚችለውን ሀገራዊ የቋንቋ ግድ የለሽነት መዘንጋት ነው!። ይህ እያወቅን የሰደድነው እሳት ነውና በጊዜ ልናጠፋው ይገባል! በጊዜ! አሁን ነገሩ ከስህተት ወደ ጥፋት አድጓልና! [From Error to Mistake then a crime!]

No comments:

Post a Comment

wanted officials