Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 23, 2015

ዲያስፖራው ተቃውሞውን ይበልጥ ወደ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ያሳድግ ዘንድ የቀረበ ታላቅ ሕዝባዊ ጥሪ --ድምፃችን ይሰማ

ዲያስፖራው ተቃውሞውን ይበልጥ ወደ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ያሳድግ ዘንድ የቀረበ ታላቅ ሕዝባዊ ጥሪ! ከተባበርን ብዙ መስራት እንችላለን! ማክሰኞ መስከረም 11/2008
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንገልጽ እንደቆየነው የዲያስፖራው ማህበረሰባችን ለትግሉ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከትግሉ ጅማሮ አንስቶም ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ታላቅ ድጋፍ የበለጠ ይጠናከር እና ውጤታማ ይሆን ዘንድ ደግሞ የትግሉን አድማስ በማስፋት የተለያዩ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በመስራት ጫናቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በአጠቃላይ የትግላችንን ምንነትና ሂደቱን በምንኖርባቸው አካባቢ ለሚገኙ የተለያዩ የውጭ መንግስታት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ማስገንዘብን ያካትታል፡፡ ከማስገንዘብ ባሻገርም እነዚህ አካላት የበኩላቸውን ጫና እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዲያስፖራው ማህበረሰብ አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች እስከፈቀዱለት ድረስ የሚከተሉትን ተግባራት በመፈጸም ትግሉን ይበልጥ ይደግፍ ዘንድ አደራ ለማለት እንወዳለን፡-
1/ ግልፅ ደብዳቤዎችን በሚኖሩባቸው አገራት ለሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፓርላማ ወይም የምክር ቤት አባላት መፃፍ፤ ቀጠሮዎችን በማስያዝ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ከእነዚህ ኣካላት ጋር ማድረግ፤
2/ በየአገራቱ ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር፤ በተለይም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ስልክ በመደወል፣ ኢሜልና ትዊት በማድረግ፣ ቀጠሮ በመያዝና ኢንተርቪው በመስጠት፣ እንዲሁም በመሳሰሉ መንገዶች የትግሉን ምንነትና የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን የመብት ረገጣ በሚገባ ማሳየት፤
3/ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚታተሙ ኘ ጋዜጦች ላይ መጣጥፎችን በአገሪቱ ቋንቋ በመፃፍ መላክና ማሳተም፤
4/ በሚሰግዱበት መስጊድ ለሚገኙ ኢማሞችና ዑለሞች የኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊሞች ላይ እየፈፀመ ስላለው ብሄራዊ ጭቆና በሰፊው ማስረዳት ፤ ስለሁኔታው በአጭሩ በማብራራት በራሪ ወረቀቶችን ማሳተምና መስጊድ ለሚገባው ሁሉ በማደል መረጃውን የበለጠ ማሰራጨት፤
እነዚህ እንደአብነት የተጠቀሱ ተግባራት እንጂ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በየጀመዓውና በየኮሚኒቲው ይህንን የዲፕሎማሲ ስራ እንዴት የበለጠ መስራት እንዳለበት በመወያየት ይበልጥ ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡ እኒህ ተግባራት በአላህ ፈቃድ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎች በመሆናቸው የዳያስፖራው ማህበረሰባችን በሙሉ ልብ እና በቁርጠኝነት በስፋት እንዲተገብራቸው በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም የትብብር ጥሪያችንን እናቀርባለን!
ብሄራዊ ጭቆናን አንቀበልም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል! ድምጻችን ይሰማል! አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment

wanted officials