Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 23, 2015

“የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ላይ በደል እየፈጸመ ነው” ተጓዦች

“የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ላይ በደል እየፈጸመ ነው” ተጓዦች
በአየር መንገዱ የተመደቡ የደኅንነት ሰዎች ግልጽ ጉቦ ይጠይቃሉ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚጓዙ መንገደኞችን በአሮጌው ተርሚናል በኩል በማስተናገድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው እየተዋከቡ መሆኑን መንገደኞቹ የደረሰባቸውን በደል ዋቢ በማድረግ ምንጮች ገልጸዋል። በተለይ ከሳውዲ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተጓዦችን በአየር መንገዱ የሚገኙ የደኅንነት ሰዎች ግልጽ ጉቦ እየጠየቁ እንደሆነ ተነገረ፡፡
በተለይ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚጓዘው ኢትዮጵያውያዊ አብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግባቸው የሚገልጹ እነዚህ ምንጮች ዜጎች በገዛ አገራቸውና አየር መንገዳቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየታችው የመንግስት እጅ እንዳለበት አመላካች መሆኑን ይጠቁማሉ።
በአሮጌው ተርሚናል የሚስተናገድ እነዚህ የአየር መንገዱ ተገልገላይ ኢትዮጵያውያን ደምበኞች ይዘውት በሚወጡትና በሚገቡት እቃዎቻቸው ላይ ያለአግባብ ጥብቅ ፍተሻ ይደረጋል፤ ለቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ስጦታ የሚውል እቃዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ይጣላል፤ የመንገደኛው ሻንጣ ቁልፍ ተሰብሮ ይዘረፋል፤ ሻንጣዎቹ እስክነ አካቴው የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ፣ ወዘተ። ከዚህም ሌላ በዚህ ተርሚናል የሚስተናገዱ ደንበኞች በአየር መንግዱ ሰራተኞች ክብር አይሰጣቸውም መብቱን ለማስከበር “ለምን?” ብሎ የጠየቀ መንገደኛ ይሰደባል፣ ይገለመጣል፣ አልፎ አልፎ በጥፊና በካልቾ የሚሰተናገድበት አሳዛኝ አጋጣሚ እንደሚከሰት የአይን እማኞች ገልፀዋል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው እና የከፋው ሳውዲ አረቢያ “መካ” ለሃጅ የፀሎት ሥርዓት በቤተሰብ አጀብ የሚሸኙ የጸሎት ተጓዥ ምእመናን ወደ አሮጌው ተርሚናል ከገቡ በኋላ እንደ ፀሎት ተጓዥ ሳይሆን አንደ አንድ መንገደኛ ማግኘት የሚገባቸውን ክብር አጥተው ስርዓት በሌላቸው አንዳንድ የአየር መንገዱ አስተናጋጆችና የፀጥታ አባላት እንደሚዋከቡ በደሉ የደረሰባቸውን ዜጎች ዋቢ በማድረግ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሮጌው ተርሚናል እያደረገ ካለው የወረደ መስተንግዶ ይልቅ “ጅዳ” ሳውዲ አረቢያ አየር ማረፊያ በባዕዳኑ የአየር መንገዱ ሰራተኞችና የፀጥታ ሃይሎች የሚደረጉላቸው አቀባበልና መስተንግዶ ምንም እንደማይገናኝ ሰሞኑን ጅዳ ከገቡ ምዕመናን የሃጅ ጸሎት ተጓዥ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ ተችሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገዱ መስተንግዶ “አገዛዙ ሃገር ውስጥ በጋራ እና በተናጠል ህዝበ ሙስሊሙ ተቋም ላይ ከሚፈጽመው በደል አይለይም” የሚሉ አንዳንድ ወገኖች፤ በአሮጌው ተርሚናል በኩል የሚያልፍ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እንደ ዜጋ ቀርቶ አንድ ቆዳው ነጣ ያለ መንገደኛ የሚሰጠውን ክብር ያህል ቦታ የለንም ይላሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገዱ መስተንግዶ በኢትዮጵያዊን ሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ብቻ ያነጣጠር ይሁን እስካሁን ማረጋገጫ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም “ከተልባ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ በኮንተራት ስራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተጠቀሱት ሃገርት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ በደሉ እየተፈፀመባቸው መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የሃገሪቱን ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ አርማው በማድረግ ከግማሽ መዕተ አመት በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ይህ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሆነው አየር መንገድ በገዥው ፓርቲ ህ.ወ.ሃ.ት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርአት ካድሬዎች እጅ ከወደቀ ወዲህ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ የዜግነት ክብራቸውን የሚያጡበት ብቻ ሳይሆን የአየር መንገዱ ሰራተኞች ጭምር በብሄር ማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው እየተለዩ ግፍና በደል የሚፈፀምባቸው ማዕከል እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።
የህወሃት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት የዜጎችን ከሃገር ወደ ሃገር የመዘዋወር ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ ከሳውዲ አረቢያ ቤተዘመድ ጥየቃ ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ዜጎች የዕረፍት ግዜያቸውን ጨርሰው ሲመለሱ የሚኖሩበትን ሃገር የመኖሪያ ፈቃድ መታወቂያ “ኢቃማ” ካላመጣችሁ አታልፉም በሚል ምክንያት በአየር መንግዱ ውስጥ በተሰገሰጉ የፀጥታ ሃይሎች እስከ 10 ሺህ ሪያል የሚደርስ ጉቦ በግልጽ እንደሚጠየቁ ለመረዳት ተችሏል።
በሳውዲ አረቢያ ህግ ማንኛውም የውጭ ሃገር ዜጋ ፓስፖርቱን ከአሰሪው እጅ ሲቀበል የመኖሪያ ፈቃዱን ለአሰሪው ማስረከብ እንደሚገባ ይደነግጋል። (Ethiopian Hagere Jed Bewadi ለጎልጉል የላኩት)
**********************
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials