ፔጊዳ (አዲሱ ናዚ)፣ ስደተኞች እና ጀርመን!
ፔጌዳ በስደተኞች መጠለያ ላይ ያደረገው ጥቃት ከዚህ በፊት በስደተኛ ላይ የከረረ አቋም የነበራቸው እንደ ቢልድ ዓይነትጋዜጦችን ሳይቀር በማበሳጨቱ ትናንት ባወጣው ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣የእግር ኳስ ተጨዋጮች እና ጸሃፊዎች ስደተኞችን ከጎናችሁ ነን እና ወደ ጀርመን እንኳን ደህና መጣችሁ!” የሚሉ ጽሁፎችን አትሟል።
ፓሳው የተባለችው የባቫሪያን ከተማ 'የጀርመኗ ላምፓዱሳ' የሚል ስያሜ ያገኘች ሲሆን ድንገቴውን የስድተኞች ጎርፍ ለማስተናገድ አቅሟ ውስን ሆኖባታል።ላምፓዱሳ የአፍሪካ ስደተኞች በሜዲትራሚያን ባህር ላይ ተጉዘው የሚያገኟት የመጀመሪያ የአውሮፓ መግቢያ በር የሆነች የጣሊያን ደሴት ናት። በጀርመን ምስራቃዊ ግዛት የጎስላር ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኦሊቨር ጀንክ በከተማዋ ውስጥ ነዋሪ የሌለባቸውን 99ቤቶች ለስደተኛ ማከፋፈላቸውን አስታውቀዋል።
ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ ፔጌዳ በስደተኞች ላይ ያደረሰውን ጥቃት “በጣም አሳፋሪ ነው” ያሉት የሃገሪቱ መሪ አንጌላ መርክል “ስደተኞችን የሚሳደብ እና ጥቃት ለመፈፀም የሚሞክር ሁሉ ቅጣት እንደማይቀርለት ይወቅ።” ብለዋል። “የሌላ ሰውን ክብር ፈጽሞ መንካት አይቻልም። ለዚህ ደግሞ ምንም ዓይነት ትግስት አይኖረንም።” ያሉት ቻንስለር መርክል “ ጀርመን ታላቅ እና ህዝቧም ርህሩህ ነው። ስደተኞቹ ጀርመን ትቀበለናለች ብለው መዳረሻቸውን ጀርመን ማድረጋቸው በራሱ ለእኛ መልካም ነገር ነው። ስለዚህ የስደተኞቹን ጉዳይ በቢሮክራሲ ሳናንዛዛ ለቀቅ ማድረግ ይኖርብናል።” በማለት ስደተኞቹን እንደ ግሪክ ወጥረው እንደማይዙ በገደምዳሜ አሳውቀዋል።
በግሪክ ጉዳይ ከራሳቸው ፓርቲ ውስጥ ሳይቀር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተው የሰነበቱት የሃገሪቱ ቻንስለር አንጌላ መርክል አሁን እጅግ ወደ ከፋ፣ ውስብስብ እና ፖለቲካሊ አደገኛ ወደ ሆነ ሌላ ቀውስ ውስጥ እየገቡ ሲሆን ለስደተኞቹ ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ ካልፈለጉ በቀር በቀጣዩ ዓመት ለመመረጥ ያላቸውን እድል እና የእስከዛሬውን ስኬታቸውንም ጭምር ሊያደበዝዝባቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው።
No comments:
Post a Comment