በናይሮቢ ኬንያ በምግብ ደህንነት ዙሪያ ወርክ ሾፕ ለመካፈል የተገኙ ስድስት አለም አቀፍ የልማት ተቋማትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ያሰራቸውንና በሽብርተኝነት የከሰሳቸውን የአለም ባንክ አስተርጓሚና ሁለት ጓደኞቻቸውን በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡ ፓስተር ኦሞት አግዋ ከስድስት ወራት በፊት ተይዘው በቅርቡ በሽብርተኝነት መከሰሳቸው አይዘነጋም፡፡ ኦሞት አገዋ፣አሽኒ አስቲንና ጀማል ኦመር ሆጀሌ የታሰሩት በማርች 2015 በምግብ ደህንነት ዙሪያ የአለም አቀፍ ተቋማትና አንድ አገር በቀል ድርጅት ባዘጋጁት ሰሚናር ለመካፈል ወደ ናይሮቢ ለማምራት በተዘጋጁበት ወቅት ነበር፡፡አቃቤ ህግ በክሱ ሰሚናሩን ‹‹የሽብር ተግባር ለመፈጸም የታሰበ››ማለቱም ታውቋል፡፡
ከኦሞት ጋር ታስረው የነበሩት ጓዶቻቸው በኤፕሪልና ጁን ወሮች ያለምንም ዋስ በነጻ መለቀቃቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በምግብ ደህንነቷና በምግብ ራስን መቻል ችግሮቿ ዙሪያ ውይይቶች እንዲደረጉ መፍቀድ አለባት የሚሉት የብሪድ ፎር ኦል የበጎ አድራጎት ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ሚገስ ባውማን ‹‹በአለም አቀፍ ደረጃ ክብር የተቸራቸው ድርጅቶች ባዘጋጁት ሰሚናር ሊካፈሉ የነበሩ ሰዎችን በሽብርተኝነት መወንጀል ተቀባይነት የለውም››ብለዋል፡፡ ኦሞት በጋምቤላ የወንጌላዊት መካነ ኢየሱሰ ቤተክርስቲያንን በመጋቢነት(ፓስተርነት)ሲያገለግሉ ከመቆየታቸውም በላይ በ2014 ከአለም ባንክ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በአኙዋክ ማህበረሰብ ስለደረሰ መፈናቀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥናት ለማድረግ በአካባቢው ለተገኙ የአለም ባንክ የምርመራ ቡድን አስተርጓሚ በመሆን አገልግለዋል፡፡ኦሞት ለእስር ከመዳረጋቸው ቀደም ብሎም ከትርጉም ስራቸው ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መንግስት ደህንነቶች ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
dawit solomon
dawit solomon
No comments:
Post a Comment