Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, September 14, 2015

ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ (ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ)




ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ
(ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ)
መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም
=================================================
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ባጠቃላይና በተለይ ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣኑን በተቆጣጠረባቸው ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ ህወሓት/ኢህአዴግን እንቃወማለን በሚለው ወገን ገንነው የመጡ ሁለት አፍራሽና ኋላቀር የፖለቲካ አዝማሚያዎች (trends ) አሉ። ከነኝህ ውስጥ አንደኛው ራስን በፖለቲካ አመለካከት ዙሪያ ከማሰባሰብ ይልቅ በጎጥና በዘውግ ደረጃ የመመልከትና ሀገራዊ ፖለቲካን በደም ቆጠራ የመመንዘር አባዜ ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ያልተናነሰው ችግር የፖለቲካ ድርጅት በመሰረታዊ ያመለካከት መርሆች ዙሪያ ሰፋ ያለ የማህበረሰብ ክፍልን የማሰባሰቢያ ድንኳን መሆኑ ቀርቶ፤ በስራ ሳይሆን ድንገተኛ አጋጣሚን በመጠበቅ ትርፍ ለማጋበስ በሚቋምጡ ሰነፍ “ነጋዴዎች“ የተቋቋሙ ሩቅ የማይሄዱ የንግድ ድርጅቶች ይመስልበ ተግባር ምንም የማይፈይዱ ”የፖለቲካ ድርጅቶች“ እንደ አሸን የመፍላታቸው ፈሊጥ ነው። እነኝህ ሁለቱም አዝማሚያዎች የህወሓት/ኢህአዴግን ህይወት ከማራዘም አልፈዉ ማህበረሰቡን ወደሚመኘው እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንድ ጋት እንኳን ፈቀቅ አላደረጉትም። ይልቁንም ዴሞክራሲን የሚናፍቁ ታጋዮች ተሰባስበውና ተጠናክረው ስርዓቱን ከመግፋት ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ወይንም በትናንሽ ቡድኖች በመሰባሰብ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በስርዓቱ በቀላሉ እየተመቱ ብዙ ታጋዮች ለሞት፤ ለስቃይና ለእስር ተዳርገዋል። አሁንም እየተዳረጉ ነው።
የዚህ አይነት የትግል አካሄድ ሩቅ እንደማያስኬድ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተገነዘበው ቆይቷል። ይህ አካሄድ እንዲቀየርና የፖለቲካ ሀይሎች ተሰባስበው ይህንን በስልጣን ላይ ከሚገባው በላይ የቆየና አገሪቱን ለውርደት የዳረገ የጥቂት ዘራፊዎች ቡድን ከጫንቃው ላይ እንዲያነሱለት ሲማጠን ቆይቷል።ምንም እንኳን በመሪዎች ድክመት የሚመኘውን ዳር መድረስ ባይችልም ባጭር ጊዜ ልምዱ በትንሹም ቢሆን የተባበረ ትግል ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመጠኑም ቢሆን አይቶታል።
ይህ የህዝብ ፍላጎት መኖር ግን በራሱ ይህንን የተባበረ ሰፊ ማህበራዊ እንቅስቃሴ መፍጠርን ቀላል ያደርገዋል ማለት አይደለም። በብዙ ስራ፤ በብዙ ድካምና ያላሰለሰ ጥረት የሚፈጠር እልህ አስጨራሽ ሂደት ነው። ባንድ በኩል እንዲህ አይነት ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴ በስልጣኑ ለመቆየት የሚፈጥርበትን ችግር የሚረዳው በስልጣን ላይ ያለው የዘራፊዎች ቡድን ይህን እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለማምከን ያለ የሌለ የገንዘብ፤ የስለላና የተንኮል ሀይሉን ይጠቀማል። በተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ደካማ ሀይሎችን በገንዘብ በመግዛት ወይንም በማስፈራራት እንዲህ አይነት ትብብሮች እንዳይፈጠሩ ከውስጥ ለመቦርቦር ተግቶ ይሰራል። በሌላ በኩል ደግሞ የትም የማያደርሳቸውን “የራሳቸውን ድርጅት” የሙጢኝ ብለው ለትልቅና አገራዊ አላማ እራሳቸውን ላለማስገዛት የቆረጡ ደካማ “የድርጅት መሪዎች” እንዲህ አይነቱን የጋራ እንቅስቃሴ በራሳቸው ግብዝነትና ስግብግብነት ምክንያት ብቻ ሊያሰናክሉት መሞከራቸው አይቀርም።
ይህ ግን ጊዜው ያለፈበት አዝማሚያ ነውና የሚሳካ ሙከራ አይሆንም። የተናጠል ትግል ሂደት ማብቂያው ጊዜ ተቃርቧል። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚታገሉ ኃይሎች እንዲህ አይነቱን ፋይዳ ቢስ ሂደት የመቀበል ትዕግስታቸው ተሟጧል። በቅርብ ጊዜ የሞላ አስገዶምን መክዳት በማስመልከት የትህዴን አመራር ባወጣው መግለጫ“ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አብሮ መስራት የድርጅታችን መሰረታዊ መርሆ ነው” እንዳለው ይህ መሰረታዊ መርሆ በሀገራችን የጸረ ህወሓት/ኢህአዴግ ትግል የበላይነት ይዞ እየመጣ ያለ እጅግ አስፈላጊና ለድሉም ወሳኝ የሆነ የጊዜው የፖለቲካ አዝማሚያ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ይህን መሰረታዊ መርሆ ከምር ወስዶ የሚንቀሳቀስ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው።
ይህአዲስ የፖለቲካ አዝማሚያ ምቾት የማይሰጣቸው የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ የስለላ ድርጅት ከሰሞኑ ሞላ አስገዶምን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በግልጽ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ኃይሎች ተሰባስበው እንዳይታገሉና ስርዓቱን እንዳይፈታተኑ የማያደርገው ጥረት የለም። በዚህ በህወሓት/ኢህአዴግ መሰሪ እንቅስቃሴ ደግሞ በቀላሉ መጠቀሚያ የሚሆኑት በጋራ የሚደረግ ትግል በግለሰብ ደረጃ ያሳጣናል ብለው የሚፈሩት “የግል ጎጆና” ጥቅም የሚያስጨነቃቸው ደካማ የፖለቲካ መሪዎች ነን ባዮችን ነው። ባንጻሩ በየድርጅቶቹ ውስጥ በሚገኙት ብዙሀኑ ሩቅ አሳቢ መሪዎች ጥረትና በተለይም ደግሞ ይህን ትግል ለአላማ እንጂ ለሌላ ምንም አይነት የግል ጥቅም ያልተቀላቀሉና በትግሉ ሂደትም ትልቁን ሚና በሚጫወቱት ብዙሀን ታጋዮች አልበገር ባይነት እንዲህ አይነት ደካማ መሪዎች ተከታይ በማጣት ሲዳከሙና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በድርጅታቸው ውስጥ የሚነሳባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ባለመቻላቸው በቀላሉ እየተፍሸለሸሉ ከመራገፍ በስተቀር በድርጅቶቹ ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ ይከስማሉ።
በህወሓት/ኢህአዴግ “የስለላ ድርጅት አቀናባሪነት” በሞላ አስገዶም መሪነት ከሰሞኑ የተሞከረው የማፍረስ ንቅናቄ ከሽፎ ወደ ተስፋ መቁረጥ የክህደት እንቅስቃሴ የተቀየረው የሰሞኑ ሙከራም የዚህ አጠቃላይ ሂደት አካል ነው። በዚህ የከሸፈ ሙከራ ውስጥ እጅግ የሚገርመውና የትህዴንን ብዙሀን አመራሮች ብስለት፤ የድርጅቱን መዋቅራዊና ድርጅታዊ ጥንካሬ፤ እንዲሁም ብዙሀኑ ታጋይ ለጋራ ትግል ያለውን ቆራጥ አቋም ያስመሰከረው፤ ይህንን የማፍረስ ሙከራ የመራውና ሳያሳካለት በመጨረሻም በጣም ጥቂት ተከታዮቹን ብቻ ይዞ የከዳው ለረጅም ጊዜ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረው ሞላ አስገዶም መሆኑ ነው። እንዲህ አይነት የመክዳት ሂደት ባጭር ጊዜ በማህበረሰባችን ላይ የሚፈጥረውን አስጨናቂ ስሜት የምንረዳው ቢሆንም ከዚያ በላይ ልንረዳው የሚገባው ግን በእንዲህ አይነት ከፍተኛ ያመራር ቦታ የነበረ ሰው ሙከራ አለመሳካት በእርግጥም የሀገራችን ፖለቲካ እየበሰለ፤ ከግለሰብ አመራሮች ተጽእኖ እየተላቀቀ፤ አዲስ የተባብሮ መታገል አቅጣጫን እያበሰረ እየሄደ መሆኑንና በትናንሽ ሰዎች መግተርተር ይህ ሂደት የማይቀለበስ መሆኑን የሚያመለክት የረጅም ጊዜ ግኝት መሆኑን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በዚህ አጋጣሚ ለትህዴን ብዙሀን አመራርና ለሰፊው ታጋይ በመርህ ላይ ለተመሰረተው አቋማቸውና መርሃቸውን ለማስጠበቅ ለሚያደርጉት ቆራጥ ትግል ያለውን ጓዳዊ አክብሮት ይገልጻል። በመግለጫቸው ላይ በግልጽ ያስቀመጡት መርሆአቸው የኛም መርሆ መሆኑን ስንገልጽላቸው በታላቅ ኩራት ነው። ድርጅታቸውን እያጸዱ የተመሰረቱበትን መርሆ ጠብቀው ለመጓዝ ባሳዩት ቁርጠኝነትና ወደፊትም በሚያደርጉት ትግል ምንጊዜም ከጎናቸው መሆናችንንና ጓዳዊ ድጋፋችን ምንጊዜም እንደማይለያቸው በዚህ አጋጣሚ ደግመን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። በመግለጫቸው ላይ እንዳሉትም ይህ ትግል ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሳያደርግ የማይቆምና እንዲያውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለኢትዮጵያ ህዝብም በየጊዜው በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ላይ ሳያተኩር ትግሉን በሙሉ ልብ እንዲደግፍ ያደረጉት ጥሪ የኛም ጥሪ ነው።
አንድነት ኃይል ነው!!!
አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

No comments:

Post a Comment

wanted officials