ኢሳት ዜና (ጳጉሜ 2, 2007) የኤርትራ መንግስት ከጎረቤት ኢትዮጵያ ወታደራዊ ወረራ ሊፈጸምብኝ ይችላል ሲል ዛሬ ሰኞ ገለጠ። በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ (ህወሃት) ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ ላይ እያቀረበ ያለው ፀብ-ጫሪ መግለጫና ንግግር እየጨመረ መምጣቱን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ማመልከቱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። የተለያዩ ሃይሎችን ድርጊት ከኤርትራ ጋር ለማቆራኘት ጥረት ሲያደርግ የቆየው የህወሃት ገዢ ፓርቲ ከተያዘው ክረምት ወቅት ጀምሮ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል ሲል የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስተቴር በመግለጫው አመልክቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጎረቤት ኤርትራ ለተለያዩ ተቃዋሚ ሃይሎች ወታደራዊ ድጋፍን እያደረገች ነው ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከአንድ ወር በፊትም ከኤርትራ ሰርገው ወደሰሜን ኢትዮጵያ የገቡ ታጣቂ ሃይሎች ተደምስሰዋል ሲል የኢትዮጵያ መንግስት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን ፣ ለድርጊቱም ኤርትራን ተጠያቂ አድርጓል። ከኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የቀረበን ማሳሰቢያና ዛቻ ተከትሎም ኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ የወረራ እቅድ መኖሩን የገለጸች ሲሆን ከኢትዮጵያ ወገን የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ኣዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አመልክቷል። ሁለቱ ሃገራት ከአስር አመት በፊት ካካሄዱት የድንበር ግጭት በኋላ የሁለቱ ድንበር አካባቢ ሰላምና ጦርነት የሌለበት ቀጣና ተደርጎ ይገለጻል።
No comments:
Post a Comment