Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, September 9, 2015

ሻዕቢያ ህወሃትን አስጠነቀቀ የጦርነት አታሞ እየተመታ ነው፤ “ሳንጃም ተስሎብኛል”


ቀደም ሲል የአባትና ልጅ “አፈጣጠርና ግንኙነት” የነበራቸው ወዳጆች ሻዕቢያና ወያኔ ያልተጠናቀቀውን የባድመን ጦርነት ካካሄዱ በኋላ ለዳግም ግጥሚያ ዝግጅት እያደረጉ ነው። “የጦርነቱ ሁኔታ” ያሳሰበው ሻዕቢያ በማስታወቂያ መ/ቤቱ በኩል ለህወሃት ማጠንቀቂያ ሰጥቷል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዘገበው መሠረት መግለጫው ህወሃት ኤርትራን እንዲወጋ የአሜሪካንን ይሁንታ አግኝቷል ብሏል።
የፈረንጅ የቀን አቆጣጠር የሚከተለው ሻዕቢያ በማስታወቂያ መ/ቤቱ በኩል 4 September 2015 ያወጣው መረጃ እንደጠቆመው ህወሃት የተለመደውን የጦርነት አታሞ እየመታና ሳንጃ እየሳለ እንደሆነ ጠቁሟል። የህወሃት አገዛዝ “ሌሎች ክፍሎች ከኤርትራ ጋር እንዳይወግኑ ትንኮሳ እያደረገ” መሆኑን የጠቆመው መግለጫ ወያኔ በኤርትራ ጦርነት ማካሄድ እንዲችል ከአሜሪካ ይሁንታ ማግኘቱን በገሃድ እየተናገረ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከአራት ሳምንታት በፊት “ኢህአዴግ በኤርትራ አራት አቅጣጫዎች ጥቃት ሊሰነዝር አስቧል፤ አሜሪካ ሃሳቡ ቀርቦላታል ተብሏል” በሚል ርዕስ ባስነበበው ዜና ላይ እንዲህ ብሎ ነበር። “አሜሪካ ኢህአዴግ “አሸባሪ” ብሎ የሚፈርጃቸውን በሙሉ በሽብርተኛነት በመፈረጅ የመን የተጫወተችውን አይነት ሚና እንድትደግም ተጠይቃለች። … አሜሪካ የቀረበላትን ጥያቄዎች ስለመቀበሏ ያልጠቀሱት የመረጃው ባለቤቶች፣ ኤርትራ ውስጥ መተራመስ ሳይፈጠርና ክልሉና ቀጣናው ሳይናጋ ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ቢወሰድ አሜሪካ ተቃውሞ እንደማይኖራት ማረጋገጫ መስጠቷን አመልክተዋል። ይህ አቋም ኦባማ አዲስ አበባ ከመሄዳቸው በፊት በተለያዩ ደረጃዎች ተመክሮበት ከስምምነት የተደረሰበት ስለመሆኑም ገልጸዋል።”
ሻዕቢያ በመግለጫው ይህንን ቢልም በኢትዮጵያ በኩል ጦሩን ከአንድ ስፍራ የማንቀሳቀስ ሂደት እየተደረገ እንደሆነ ይታያል። ለዚህም የሚሰጠው ምላሽ ቀለል ያለ ብወዛ እንደሆነ ቢነገርም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለየት ባለ መልኩ በአማራው ክልል የሠራዊቱ ቁጥር እየጨረ መምጣቱን ከሥፍራው የሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአንድ ዓመት በፊት የአሰብ ወደብ እንዲታደስና በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መደረጉ ከተለያዩ ምንጮች ሲነገር የቆየ መሆኑ ይታወሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰሞኑ የህወሃት “ጨዋታ” የአዲስ አበባውን አንጃ ይመራሉ የተባለላቸው አርከበ ዕቁባይ ከጥቂት ወራት በፊት የኤርትራንና አሰብን ጉዳይ በተመለከተ ሲናገሩ “በኤርትራም ሁኔታው መቀየሩ አይቀርም፤ አሁን ያለው ሁኔታ ለዘለዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም። በእኔ ግምት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ። የኤርትራን ወደብ (አሰብን) እንጠቀማለን” ማለታቸውን የሚጠቅሱ አስተያየት ሰጪዎች በወያኔና በሻዕቢያ መካከል የሚወራው የጦርነት ዝግጅትና አታሞ “ድለቃ” ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ይናገራሉ።
*******************************
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
የዛሬ ወር አካባቢ (ኢህአዴግ በኤርትራ አራት አቅጣጫዎች ጥቃት ሊሰነዝር አስቧል - አሜሪካ ሃሳቡ ቀርቦላታል ተብሏል) በሚል ርዕስ ጎልጉል ያሰራጨውን ዜና ከዚህ በታች በድጋሚ አትመነዋል፡-

No comments:

Post a Comment

wanted officials