Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, June 2, 2015

በ2007 ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የነበረው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ የምርጫ በጀት መድረሻው አልታወቀም

የጠፋው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ የምርጫ በጀት መድረሻው አልታወቀም


በ2007 ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ ለመሆን ወደ ፉክክር መድረኩ ገብቶ የነበረው የአዲስ

ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የምርጫ በጀት የት እንደገባ አለመታወቁን የፓርቲው ዕጩዎች
ተናገሩ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኢተያ ምርጫ ክልል የፓርቲው ዕጩ የነበሩትን አቶ ተሾመ ደረሰን ጨምሮ
በሌሎች አካባቢዎችም የፓርቲው ተወካዮች የነበሩት ግለሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣
አስፈላጊውን የምርጫ ፎርማሊቲ አሟልተው ወደ ምርጫ ፉክክሩ ከገቡ በኋላ በቅድመ
ምርጫው ወቅት ምንም ዓይነት የምረጡኝ ቅስቀሳም ሆነ ማስታወቂያ ሳያከናውኑ የቀሩት፣
ፓርቲው የተመደበለት በጀት ሥራ ላይ ባለመዋሉ ምክንያት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አስፋው ጌታቸው ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ፣ በተወካዩ
ግለሰብ እጅ የነበረው ገንዘብ ለምርጫ ተግባራት መዋል ሲገባው የውኃ ሽታ ሆኖ
መቅረቱን አባላቱ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ባከፋፈለው በጀት መሠረት
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) 487,999.03 ብር የደረሰው ሲሆን፣ ፓርቲው ግን በበርካታ
ቦታዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በምርጫው ቀን ማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ አቶ ደምሰው በንቲ፣ ቦርዱ ይህንን በተመለከተ ምንም ዓይነት
ሪፖርት እስካሁን እንዳልቀረበለት ጠቁመው፣ ፓርቲው ግን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ
አሟልቶ ለምርጫው የተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲው መሥራችና ሊቀመንበር እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ አስፋው ጌታቸው በ1968
ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው በግብርና ኢኮኖሚ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በቢኤ ዲግሪ
የተመረቁ መሆናቸው በፌስቡክ አካውንታቸው ላይ የሠፈረውና ፓርቲውን አስመልክቶ
የተቀመጠው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታና አሁን ያለውን
ገዥ ሥርዓት በማጣጣም፣ አዲሱ ትውልድ የሚኖረውን ሚና ከግምት በማስገባት
እንደተቋቋመ የሚነገርለት አዲስ ትውልድ ፓርቲ ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡
ለጊዜው በጉዳዩ ላይ ምንም ነገር ማለት እንደማይቻል ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ደምሰው፣
ምርጫ ቦርድ የሚከታተለው ነገር ካለ ወደፊት የሚታወቅ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር በሊቀመንበሩ ተወክለዋል የተባሉትን ግለሰብ በተደጋጋሚ በስልክ ለማነጋገር
ያደረገው ሙከራ ግለሰቡ የስልክ ጥሪ ባለመመለሳቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡
አቶ አስፋው አሜሪካ ከሄዱ ሁለት ወራት እንዳለፏቸው የሚገልጹት የፓርቲው አባላት፣
የመመለሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials