ምርጫ ሲባል የነጻነት ዓየር አለ፤ ምርጫ ሲባል ተፎካካሪዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል ተፎካካሪዎች በእኩልነትና በነጻነት የቆሙበት መድረክ አለ፤ ምርጫ ሲባል የራሱን ፍላጎት በትክክል የሚያውቅና ከፍርሃት ነጻ የሆነ መራጭ አለ፤ ምርጫ ሲባል የተፎካካሪዎቹን እኩልነትና ነጻነት፣ የመራጮቹን እኩልነትና ነጻነት የሚያከብሩና የሚያስከብሩ ዳኞች አሉ፤ ምርጫ ሲባል የመራጮቹን ፍላጎት በትክክልና ያለአድልዎ የሚያሳይ ሰነድ የሚያዘጋጁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሕግን የሚያከብሩ፣ ለሕዝብና ለአገር የሚቆረቆሩ ሰዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል ይኸኛው ከዚህኛው ይሻለኛል ብለው የመወሰን ችሎታ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል መራጮቹ ተመራጮቹን ማገላበጥ አለ።
ታዲያ እኛ ምርጫ የምንለው ይህንን ሁሉ የያዘ ነው? ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱም እንኳን ቢጎድል፣ ምርጫ አንለውም፤ ምርጫ-መሳይ ልንለው እንችል ይሆናል፤ አንድ የሁለት ጓደኞች የቆየ ቀልድ ትዝ አለኝ፤ አንዱ ስሙ መሳይ ነው፤ ፊታውራሪ ነው፤ ሌላው ስሙ በፈቃዱ ነው፤ ሀኪም ነው፤ አንድ ቀን በፈቃዱ መሳይን ሲያገኘው በፊታውራሪነቱ ለማሾፍ ፊታውራሪ መሳይ አለ፤ መሳይን ጫን ብሎ፤ መሳይም ሲመልስ በዶክተርነቱ እያሾፈ ዶክተር በፈቃዱ ብሎ ዶክተርን ጫን ብሎ መለሰለት! የኛን ምርጫ-መሳይ ምን ብለን፣ አንዴት ብለን እናሹፍበት? ያውም ማሾፍ ከተፈቀደ! በባህላችን በጣም የተወደደ ምግብ አለ፤ ያንን ምግብ አቅርበው መሣሪያው ሲነፍጉ ሥጋውን ሰጥቶ ቢላዋውን መንሣት ይባላል፤ ንፉግነት ብቻ አይመስለኝም፤ ክፋትም አለበት፤ የደርግና የወያኔ ምርጫ-መሳዮች በአለማወቅና በንፉግነታቸው ይመሳሰላሉ፤ በክፋት ግን አይመሳሰሉም።
ደርግም ሆነ ወያኔ ከሌኒን ለመማር አልቻሉም እንጂ አስመስለዋል፤ ምርጫ-መሳዩንም ያገኙት ከዚያው ነው፤ ሌኒን ጉሮሮን ግጥም አድርጎ በብረት ሰንሰለት አስሮ ነጻ ነህ ይላል! መገንጠል ትችላለህ! ይላል፤ ወያኔም ሲሉ ሰምቶ መገንጠል-መሳይ ሕግ-መሳይ አወጣ! ችግር ነው ጌትነት! ዱሮ ተረት ነበር፤ ዛሬ ግን በእውነት ሲቸግር እያየን ይመስለኛል፤ አንድ ሰው ራሱ ባፈራው ሀብትና በደረሰበት የጌትነት ደረጃ ችግር አይሰማውም፤ ሀብቱ ከየት እንደመጣ፣ እንዴት እንደመጣ፣ ምን ያህል ልፋት እንዳስከተለ መገመት ይቻላል፤ በተዘረፈ ሀብት ጌትነት ሲመጣ ግን ችግርን አዝሎ ነው፤ አንድ ሰው አራት ሚልዮን ብር ወድቆ ቢያገኝ አራት መቶ ካሬ ሜትር መሬት ቢገዛበት አያስደንቅም፤ የገንዘብ አያያዝን ስለማያውቅና በስጋት ስለሚከሳ መሬቱ ላይ መቀመጥ አስተማማኝ መስሎ ይታየዋል፤ ከካስትሮ በፊት የነበረውን የኪዩባ ሁኔታ በትንሹም ቢሆን የሚያውቅ በዛሬው ጊዜ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነቱን ለመረዳት አያዳግትም፤ በኪዩባም ሆነ በኢትዮጵያ በተዘረፈ ሀብት ጌትነትን ያስፋፋው አሜሪካ ነው፤ ሕዝብ የሚደኸየውና የሚከብረው በጉልበትና በዝርፊያ ብቻ በሆነበት አገር ጊዜውን ጠብቆ ከሁለት አንዱን አርግዞ ይወልዳል፤ ወይ ዘራፊዎችን ሁሉ ዘርፎ ሙልጭ የሚያወጣቸው ጉልበተኛ ይመጣል፤ ወይ በሕጋዊ መንገድ ከዘራፊዎች እየገፈፈ ሀብትን ለሕዝብ የሚያደላድል ሕጋዊ ሥርዓት ይመሠረታል፤ ሁለቱንም በማስረገዝ ላይ ያሉት በግፍ ሀብታም የሚሆኑት ናቸው።
ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንደሆነ ለማስመሰል ምርጫ መሳይ አለ፤ ሕዝብ የሀብት ባለቤት እንደሆነ ለማስመሰል ግን ትንሽ ያስቸግራል፤ በኮንዶሚንየም ለማስመሰል ቢሞከርም አልሆነም፤ ለሎሌዎች ሹሞችም አልተዳረሰም! በምርጫ መሳዩ ማሸነፍ ቀላል ነው፤ እንዲያውም መቶ በመቶ ማሸነፍ ይቻላል፤ ችግሩ የሚመጣው ከዚያ በኋላ ነው፤ ደካሞች የፖሊቲካ ቡድኖችንና ደካማውን ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚቻል ጉልበተኛው አስመስክሯል፤ ሌላው ቀርቶ ‹‹የኔ›› የሚላቸውን ቡድኖችም አፈር ላይ ሊያስተኛቸው ይችላል፤ እንዲያውም አፈሩ ምቹ ፍራሽ ነው ብለው በደስታ እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ አሁን የጉልበተኛው መድረክ እየጠበበ መጣ፤ ችግሩ የሚፈጠረው እዚህ የጠበበው መድረክ ውስጥ ባሉት ጉልበተኞችና ጉልበተኛ መሳዮች ነው፤ በአንድ በኩል በጉልበተኞች መሀከል፣ በሌላ በኩል በጉልበተኛ መሳዮች መሀከል፤ በሌላ በኩል በጉልበተኞችና በጉልበተኛ መሳዮች መሀከል፣ ይህ ትግል ዳካማዎች የፖሊቲካ ቡድኖችን እንደማሸነፍ ቀላል አይደለም፤ በአጥር ላይ እየተንጠለጠሉ የጣሉትን ለመልቀም እየተሻሙ ነው፤ በጉልበተኞቹ መሀከል ክፉ የሥልጣን ችጋር ገብቷል ማለት ነው፤ ጦር መማዘዝ ኪስን እንደሚያራቁት ያውቃሉ፤ ያለሥልጣን ኪስ ሙሉ እንደማይሆንም ያውቃሉ፤ ታዲያ ምን ይሻላል?
No comments:
Post a Comment