“የድረሱልኝ ጥሪ” ያሰሙት የስልጤ ዞን ቂልጦ ቅድስት ማርያም ምእመናን “ሃይማኖታዊ ግጭት ለማስነሣት ተንቀሳቅሳችኋል” ተብለው ፍርድ ቤት ቀረቡ
- ፳፩ የምርመራ ቀናት የጠየቀባቸው የወረዳው ፖሊስ የ፲ ቀን ጊዜ ተፈቅዶለታል
- በድረሱልኝ ጥሪው÷ ከሥራቸው የታገዱ፣ ከደረጃ ዝቅ የተደረጉ እና የታሰሩ አሉ
- የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎችና ምእመናኑ ከወረዳው አስተዳደር ጋር እየተነጋገሩበት ነው
- በተቃጠለው የቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው መቃኞ ሰኔ ፳፩ ይመረቃል
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፰፻፫፤ ቅዳሜ ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ፣ የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና የደብሩ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት “ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
የወረዳው ፖሊስ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ እና በዚኽ ሳምንት ሰኞ ስድስት የሰበካ ጉባኤውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት በቁጥጥር ሥር በማዋል በቂልጦ ወረዳ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል፡፡
ምእመናኑ፣ “የድረሱልኝ ጥሪ” በሚል “ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ጽሑፍ ጽፈው በፌስቡክ አሰራጭተዋል” ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የሰበካ ጉባኤው ሊቃነ መናብርት “የድረሱልኝ ጥሪ” በሚል ደብዳቤ መጻፋቸውን ቢያምኑም በፌስቡክ አለመልቀቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ምእመናን ላይየማጣራው ነገር አለ በሚል የኻያ አንድ ቀን የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ቢኾንም ፍርድ ቤቱ የዐሥር ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶለታል፡፡
ስለ ጉዳዩ በስልክ የተጠየቁት የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ቶፊቅ ከድር፣ “በሕግ የተያዘ ጉዳይ በመኾኑ አስተያየት ለመስጠት አልችልም፤”ሲሉ መልሰዋል፡፡
ከዐሥራ ስድስት የቂልጦ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ እና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ አሠሪ ኮሚቴ ምእመናኑ መካከል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ስድስት አባላት÷ ሊቀ መንበሩ መ/ር የማርያም ወርቅ ተሻገር፣ መ/ር ሀብታሙ ተካ፣ አቶ ሙሉጌታ አራጋው፣ ወ/ሪት ንጋት ለማ፣ አቶ ማስረሻ ሰይፈ እና አቶ ማሩ ለማ የሚባሉ ሲሆኑ በወረዳው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት፣ የፖሊስ፣ የጤና እና የግብርና ጽ/ቤቶች እንዲሁም የባንክ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ናቸው፡፡
”የድረሱልኝ ጥሪ“ በሚል ርእስ የተሰራጨው እና የደብሩን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ማኅተም የያዘው ጽሑፍ÷ በስልጤ ዞን በምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው ላይ በአክራሪነት አስተሳሰብ የተወጠሩ ባለሥልጣናት ይፈጽሙብናል ባሏቸው ግፎች መማረራቸውን፣ የአምልኮ ነጻነታቸው እና ሠርተው የመኖር ዋስትናቸውም አደጋ ላይ መውደቁን ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት መኾኗን የገለጹት ምእመናኑ፣ ስለሚፈጸምባቸው ግፍ እና ሥቃይ ለወረዳው የፖሊስ እና የሕግ አካላት በየደረጃው ቢያመለክቱም የአስተዳደሩ መዋቅሩ እና አሠራሩ ያልተገባ “ሕጋዊ ሽፋን” በመስጠቱ የጥቃቱ ስልት ዐይነት እየጠነከረ መጣ እንጂ መፍትሔ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በየቤታችን እና በሥራ ቦታዎች እየደረሰብን ነው ያሉት እስር፣ እንግልት፣ ዛቻ፣ በሥራ ቦታ ከሓላፊነት መነሣት፣ ከደረጃ ዝቅ መደረግ፣ መታገድ እና መባረር እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት ምእምኑ፣ ድርጊቱ የተባባሰው፤ የቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ተረክበው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጡበት ከጥቅምት ፳፬ ቀን ወዲኽ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ለመንግሥት እና ለቤተ ክህነት አካላት አቤቱታቸውን ያሰሙበት “የድረሱልኝ ጥሪ” የሚለው ይኸው ጽሑፍ፣ የሀገረ ስብከቱን ፈቃድ በመጠየቅ የተዘጋጀ እንደኾነ የገለጹት ምእመናኑ አክራሪነት በተጠናወታቸው አንዳንድ ባለሥልጣናት የሚደርስባቸውን ሥቃይ በመዘርዘር መፍትሔ የጠየቁበት እንደኾነ ጠቁመው፤ “ታምኑበታላችኹ ወይስ አታምኑበትም” እየተባለ ሃይማኖታዊ ግጭት እንደቀሰቀስን እና የወረዳውን ስም እንዳጠፋን ተደርገን መታየታችን አሳዝኖናል ሲሉ ርምጃውን ተቃውመዋል፡፡ ታሳሪዎቹ በየሞያቸው የተመሰገኑና በምግባራቸው የተወደዱ የመከባበር እና የፍቅር ተምሳሌት መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ቀድሞ ያስቀድሱበት እና የመካነ መቃብር አገልግሎት ያገኙበት የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከኻያ ዓመት በፊት መቃጠሉን ያስታወሱት ምእመናኑ፣ በምትኩ የሚያሠሩት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኒቱ መቃኞ በመጪው ሰኔ ፳፩ ቀን የሚመረቅ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
የሃዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች እና የሰበካው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከወረዳው አስተዳደር ጋራ በጉዳዩ ላይ እየተነጋገሩበት እንዳሉ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል፣ ””የድረሱልኝ ጥሪ” በሚል በፌስቡክ ተሰራጭቷል ለተባለው ጽሑፍ የታሰሩት የሰበካ ጉባኤ አባላት ማስተባበያ እንዲሰጡና መሳሳታቸውን አምነው ይቅርታ እንዲጠይቁ በማግባባት ከእስር ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መቃኞ ዕብነ መሠረት በአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በተቀመጠበት ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከተለያዩ አህጉረ ስብከት ከ2500 በላይ ምእመናን በ20 አውቶቡሶች እና የግል መኪኖች በመምጣት በዓሉን አክብረዋል፡፡
ጉልላቱ በተሰቀለበት ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በየጊዜው የሚወርደው ቀስተ ደመና በጉልሕ ይታይ ነበር፡፡ የወረዳውን ምእመናን የማጽናናት እና የአንድነት መንፈስን የመፍጠር ዓላማ ያለው ጉባኤ ግንቦት ፰ እና ፱ ቀን በሕንፃ አሠሪው ኮሚቴ አዘጋጅነት የተካሔደ ሲኾን ከአዲስ አበባ የተጋበዙ መምህራን ተሳትፈውበታል፡፡
አኹንም በብዙ ውጣ ውረድ ለተሠራው ለቤተ ክርስቲያኑ መቃኞ ምረቃ በዓል መነሻው ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከመስቀል ዐደባባይ የኾነ የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን በመግለጽ ምእመናን ኹሉ እንዲሳተፉ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
No comments:
Post a Comment