በተከታታይ በደቡብ አፍሪካና በአረብ ምድር ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉን እልቂት ከተመለከትኩ በሗላ የሀገራችንን ፖለቲካ መከታተል የበለጠ አሳዛኝ ዜና ያመጣብኝ ይሆናል በሚል ስጋት ኮምፒተሬን በእጅጉ ፈርቸዉ ከረምኩ አንዱ ሳይቋጭ ሌላ መከራ፡ በመከራ ላይ መከራ፡ መሪዎቻችን የመከራ አምካሪዎች፡ ምን ይበጀን ይሆን?። ባለፈዉ ስፈራ ስቸር በተለመደዉ በድር ጥንጥን ስተላለፍ ሼህ አላሙዲ በዉጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች የእሳቸዉን ስራ ዋጋ ሰጥተዉት ለዉይይት ባለማቅረባቸዉ የተሰማቸዉን ሐዘን ፍንጭ የሰጡበት አጋጣሚ ቀልቤን ስቦት ሀሳቤን ልናኘዉ በማለት ወረቀትን ከብእር አገናኘሁ የዜናዉ ምንጭ ኢሳት ለኳሺ ኤልያስ ክፍሌ።
ሼህ አላሙዲ ከኢትዮጵያ አፈር ተበጥብጠዉ እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያነሰ ወይም የጎደለ ኢትዮጵያዊነት ሳይኖራቸዉ እንደኔዉ በትንሿ መንደራቸዉ ተወልደዉ አድገዉ ከጓደኞቻቸዉ ጋር ዘር ሀይማኖት ሳይለዩ ከሰፈራቸዉ ልጆች ጋር ቡድን ተቧድነዉ ኳስ አቃብለኝ ብለዉ ሲጮሁ፤ ላዘገየባቸዉ ወይም ላላቃበላቸዉ ደግሞ ቆይ ጠብቅ ባንተ ምክንያት ነዉ የተሸነፍነዉ ብለዉ ሲዝቱ፤ ጎል ጠባቂ ተረኛ ሁነዉ ደግሞ ብዙ ጎል ሲገባባቸዉ ሁለተኛ አንመርጥህም እንደዉም ከኛ ጋር አትጫወትም ሲባሉ ሆድ ሲብሳቸዉ። ከዛ ደግሞ አለፍ ብሎ ተማሪ ቤት አጠገባቸዉ የተቀመጠዉን ተማሪ ዞር ሲል ሲቆነጥጡ እሱም ባንኖ አንተነህ ሲላቸዉ እሳቸዉም እኔ አይደለሁም ብለዉ ሲክዱ፤ እሱም ጊዜ ጠብቆ ብድሩን ሲወጣ። እርሳሳቸዉ ሲጠፋባቸዉ አጠገባቸዉ ካለዉ ጓደኛቸዉ ነድፈዉ አይኔን ግምባር ያድረገዉ ብለዉ ሲክዱ።እንዲህ አንዳንዴ ደግሞ ሾለክ ብለዉ ብይ ሲጫወቱ ፤ ወደ ሁዋላ ደግሞ አንድ ቀላ ድምቡሺቡሺ ያለች ልጅ ወድደዉ እንዳይጠይቁ ፍርሀት በሰራ አከላታቸዉ ገብቶ መላ አጥተዉ በልጅቱ አጠገብ ሲያለፉ እጃቸዉን ኪሳቸዉ ከትተዉ ድንጋይ በጫማቸዉ እየመቱ ልጅቱ እንደበደለቻቸዉ ሁሉ ቆይ ነገ ባላገኝሺ ብለዉ ፎክረዉ በቄንጥ ባጠገቧ ሲያልፉ። ለልጅቱ የላኩት የፍቅር ደብዳቤ ተጠልፎ ዲሊክተሩ ቢሮ ደርሰዉ የተግሳጽና የኩርኩም ናዳ ሲወርድባቸዉ እንዲያ እንዲያ እያሉ ከዛሬዉ ከዲታነታቸዉ ዘመን በላይ የልጅነት ጊዜያቸዉን በምድረ ኢትዮጵያ እስከ መጨረሻዉ የማይረሳ ህልም ሁኖ የሚቀር የደስታ ኑሮ ኑረዉ እንደእኔዉ ኑሮን ለማቅናት በረሃዉን ተከትለዉ ልባቸዉ ወደመራቸዉ ቦታ ተጓዙ። ምድር በሰጠችህ በረከት ትኖራለህ ተብለዉ ነበርና የዛሬዉን አላሙዲን ሲሆኑ እኔም በላብህ ጥረህ ግረህ ትኖራለህ የሚለዉ የግድ ተግባራዊ እንዲሆን ከሳቸዉ በተቃራኒ ሂጄ በአንድ የምእራብ ሀገር እኔን ሁኜ እኖራለሁ።
ከተረሳ ሁሉም ይረሳል የፖሊስ ጥፊ የባለስልጣን ግልምጫ ሳያየኝ አምላክን እያመሰገንሁ እኖራለሁ። ምርጫ ሲመጣ አንዴ አንዱን በሌላ ጊዛ ደግሞ የወደፊት እቅዴ ደሀን ሀብት በሀብት ማድረግ ነዉ ሲለኝ ብዙ ጊዜ ብታለልም እዉነት እየመሰለኝ መልሼ ያንኑ እመርጣለሁ። ደግነቱ ወረቀቴ በገባችበት ሳጥን ቆይታ ለመረጥኩት ተፎካካሪ ማንም ሳይነካት ትደርሳለች ክፉም አይነካትም። አደራ እፍረት ባጠገባችሁ ያላለፈ የስርአቱ ደጋፊዎች ኢትዮጵያም እንዲሁ ነዉ ብላችሁ እንዳታስቁኝ። ይሄኛዉ ነገሩ ሌላ ነዉ እናንተም ታዉቁታላችሁ ብቻ ለማደናቆር ስትፈልጉ ዶሮዋን ቆቅ ታደርጓታላችሁ።
ስለልጂነት ዘመናቸዉ ይህን ካልኩ በሗላ በቀጣዩ ደግሞ እኝህ ግለሰብ በኢትዮጵያዉያኑ መሀል የተለያየ ስምና ስብእና እየተሰጣቸዉ እኛም ከወሬዉ ብዛት ትክክለኛዉ እሳቸዉ የትኛዉ እንደሆኑ ማመን ተቸገርን እዚህ ደርሰናል። ኑሮ እንጨት እንጨት ሲለዉ ገመድ አዘጋጅቶ የመጨረሻ ትንፋሹን ሊዉጥ ሲል ገመዱን በብር ሺራፊ ቆረጡት ይላል በአይኔ በብረቱ አየሁ የሚል አዳናቂ፤ አይ ያንተ ነገር ይሄማ ምን አለዉ ይለዋል ሌላዉ አላሙዲን በአይኑ አይቶ የማያዉቅ ተራኪ። አየር ለመቀበል ወጣ ሲሉ አንዷ ደሀ በትካዜ ተዉጣ እድሌ ነዉ እንግዲህ ምን ይደረጋል እሱ ያዉቃል ብላ እምባዋን ጠራርጋ ስትነሳ አንች ሴት ከቅድም ጀምሮ ስመለከተሺ ነበር ምን ችግር ቢገጥምሺ ነዉ ቢሏት ማንነታቻዉን ያላወቀች አንዲት ያገሬ ሰዉ ልብ በሚሰብር አነጋገር ኑሮዋን ብታወጋቸዉ ልባቸዉ ተነክቶ 3 ልጆቿን ወደ ባህር ማዶ ልከዉ አስተማሩላት ይላል ሌላዉ። ሌላዉ ደግሞ ባለፈዉ አንድ የሰፈራችን ሰዉ የተሰጠዉ እድሜ አልቆ አትድንም አትልፋ ብሎ ሀኪም ቢነግረዉ ጆሮ ጠባቂያቸዉ ጉዳዩን ቢያደርስላቸዉ ባህር ማዶ ልከዉ አሳክመዉት ይባስ ብሎ ሩጫ ጀምሯል ይላል ለሰዉ የተደረገለተ ወደሱ የሚጋባ የሚመስለዉ ምናበኛ። ሌላዉ ደግሞ ተሰባስበን የሙዚቃ ክፍል ልናቋቋም ነዉ ብለዉ ወጣቶቹ አቤቱታ ቢያቀርቡ አይናቸዉ ሳያይ እጃቸዉ ብቻ ዘግኖ ያወጣዉን 30000 ዶላር ቢሰጧቸዉ ነገሩ ለዉሻ እንደ ተወረወረ ስጋ አይነት ነገር ሁኖ ተካክደዉ አንዱ ሌላዉ በደረሰበት አይደርስም ይላል። ቡና ቤት ከፈቱላት፤ መኪና ገዙላት፤ የወር ደሞዝተኛ አደረጉት፤ ወደ ትምህርት ተቋም ልከዉ አስተማሩት፤ አቋቋሙት፤ዳሩት የሚለዉ ነገር ችሮታዉ ከተደረገበት ቦታ እያለፈ ሲሄድ በከፍተኛ ፍጥነት እየተባዛና እየገዘፈ የሼህ አላሙዲን ነገር አንዴም እንደ ሮቢን ሁድ(Robin Hood) ለድሀ ተቆርቋሪ አይነት ሲያደርጋቸዉ ሌለዉ ደግሞ ከሰማዩና ከመንፈሳዉያን መሀል ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ ነገር ከምድራዊ ሰዉ ሊሆን አይችልም ብሎ ነገሩን ይዘጋዋል።
እኚህ ሼህ በኢትዮጵያ አፈር በቅለዉ ለፍሬ መብቃታቸዉ ሀብታቸዉ ብቻ ሳይሆን መልካቸዉ እና ሌሎች አረቦች ላይ የማናየዉን እሴቶች በሳቸዉ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል። አንድ ቀን ስለ ሀብታም የማላዉቀዉ የለም የሚለዉ ፎርበስ (Forbus) መጽሄትም በኢትዮጵያ ባንድራ ጥለት በተንቆጠቆጠ እጀ ጠባብ እና ኩታ ያሳየን ይሆናል የሚል ተስፋም አለን። እንደዉ አሁን ማን ይሙት ኢትዮጵያዊ መሆን ምኑ ያሳፍራል? ስለ ሰዉ ልጂ አፈጣጠር ንትርክ ሲነሳ ችግር መፍቻ እና ማነጻጸሪያ የሚሆነዉ ያዉ ኢትዮጵያ ነዉ ። ነጻነት የጠማዉ የየሀገሩ ዜጋ በምናብ የሚያየዉ ይህችኑ የነጻነት ተምሳሌት ኢትዮጵያን ነዉ አረ ስንቱ መለስ ዘራዊ አዋርዶን ሄደ እንጂ ምን እሱ ቢሞት ሌሎች የማይሞቱትን ተክቷል እንደዉም እሱ ጥሩ ሰዉ ነዉ ቀድሞ መሞቱ። ያነጋገር፤ የባህል፤ ሰዉ የማክበር ምሳሌ ኢትዮጵያዊ ሁኖ እያለ በየምክንያቱ በኢትዮጵያዊነት እንዲታፈር የሚደረግበት ምክንያቱ ምን ይሆን? ክቡር አቶ መለስ አንዱ ፓርላመንተኛ ደጋግሞ ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ ፓርላማዉ ዉስጥ ቢያነሳባቸዉ ደማቸዉ ፈልቶ ምነዉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት አበዛህ ብለዉ ለህዝብ በሚተላለፍ ቴሌቨዢን ዉቃቢዉን ገፈዉት የለ? ዛሬ ሙት ወቃሺ አያድረገኝ እንጂ በዉነቱ በዛን ቀን እዚያ ምስኪን ላይ አቶ መለስ በብስጭት የጮሁት ጩኸት አበበ ከላዉም ከዛ በላይ እሳቸዉ ላይ አልጮኸም ነበር ሰበብ ሁነዉበት አረፉት እንጂ። ነገር ነገርን አስነስቶ ወዳልፈለግሁት አቅጣጫ ገፋኝ እንጂ ነገሬን ለማሳጠር ዲታ አላሙዲ ገንዘቡን ከላያቸዉ ስናነሳ ኢትዮጵያዊ አንጂ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም ለማለት ፈልጌ ነዉ እንጂ አቶ መለስማ ወደ ማይመለሱበት ሂደዋል።
እንግዲህ ከዚሁ ተንደርድረን ጌታ አላሙዲ ለስራዬ እዉቅና ተነፈግሁ ከህዘቡ ጋር አላገናኙኝ አሉ የዜና ተቋሞችን መዉቀሳቸዉ የወዳጂነት እንጂ የክፋት ስላልሆነ እሳቸዉም በድፍረት ኢትዮጵያዉያን ሰፈር ቀርበዉ ኢትዮጵያዉያን ጋር የሆድ የሆዳቸዉን ቢወያዩ መልካም ነዉ እላለሁ። ከእነ አቦይ ስብሀት፤ በረከት ሰምኦን፤ ከመለስ ዘራዊ ጋር አንዴ ሲያጨበጭቡ አንዴ ሲፍነከነኩ ደስታ በደስታ ሁነዉ ሲዝናኑ ብዙ መረጃዎች ደርሰዉናል። ኢትዮጵያዉያን መሀል ግን በእንዲህ ሁኔታ ደፍረዉ የታዩበት አጋጣሚ ብዙም አናስታዉስም።
በነገራችን ላይ ሼህ አላሙዲ በዉጭ የሚኖሩ ኢንቨስተር እንጂ የህዝብ አደራ የተቀበሉ ባለስልጣንም አይደሉም አንዳንዶቻችንም ከአንድ መንግስትና ጥሩ ዜጋ የማይጠበቅ ሰብአዊ፤ልማታዊ፤በጎአድራጎታዊ ስራ ከሼህ አላሙዲ ስንጠብቅ እንታያለን። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ነገሩን ስናየዉ ሼህ አላሙዲ ግለሰብ ብቻ አይደሉም እሳቸዉ የሚወስዱት የኢንቨስትመንት ዉሳኔ ጉዳቱና ጥቅሙ የሀገራችን ጥቅም እና ጉዳት በመሆኑ ዜጋ አይኑን ከፍቶ ሊመለከተዉ ይገባል። ስለዚህ ሼክ አላሙዲ የግል ሳይሆኑ የህዝብ በመሆናቸዉ የህዝብ የሆነ ደግሞ በሀገሩ የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ በግልጽ መገምገም ስላለበት ሼህ አላሙዲም የዚህ ክስተት አንዱ መሆናቸዉን እሳቸዉም ሊገነዘቡልን ይገባል። ጥሩ ሲያደርጉ ጀግና፤ ከኢትዮጵያዊነት መስፈርት ሲወርዱ ደግሞ በህግ አምላክ ማለታችን ግድ ይላል ምንም እንኳን አሁን ህግ ባይኖርም የኢትዮጵያ ሊቃዉንት በየሀገሩ ስለተበተኑ መደበቂያ ጠፍቷል። ባለፈዉ ሼክስፒር ፈይሳ የወያኔን መሪዎች ከሀገር ወጥተዉ ሺቶ እንኳን እንዳይገዙ አስጨንቆ ይዟቸዉ መላ ጠፍቷቸዉ ነበር። ሼክ ሰፒር ፈይሳና ፕሮፌሰር አልማርያም እግር ላይ ወድቀዉ ምህረት ጠየቁ መሰል ዛሬ ፍርሀቱ ለቋቸዉ እየመጡ ሺቶ ነገር እየገዙ፤የቤት ክራይ እየተቀበሉ፤ ቱቦ እያስቀየሩ መመለስ ጀምረዋል።
እንግዲህ ሼህ አላሙዲ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍ ያለ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉ ግለሰብ በመሆናቸዉ የሳቸዉ ኢንቨስትመንት ጥቅም እና ጉዳቱን ለመለካት ብቃት ያላቸዉ ባለሙያዎች ጉዳዩን አስመልከተዉ ማብራሪያ እንዲሰጡን ስለጉዳዩ እናዉቃለን የሚሉ ዜጎች ደግሞ የግል ሀሳባቸዉን፤መረጃቸዉን፤ጽሁፋቸዉን ወደ ጋዜጣዉ ቢሮ አከታትለዉ ቢልኩ ስለሳቸዉ ተጨባጭ ግንዛቤ እንይዘለን የሚል ግምት አለኝ።
እሳቸዉም ረቂቅ የሆነዉን የአማርኛ እዉቀታቸዉን ተጠቅመዉ ማብራሪያ እንዲሰጡ ፍቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አለበለዚያ ከክፉ መሪዎች ጋር ተመሳጥረዉ የሀገርን ንብረት አባከኑ የሚለዉ ክስ ተከላካይ እስካልቀረበበት ድረስ እዉነት ሁኖ ሊቀር ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮየጵያ ላይ የሚያደርጉት የመዋእለ ንዋይ ፍሰት እሳቸዉም ተጠቅመዉ ህዝቡንና አገሪቱን ለመጠቀም ከሆነ እሳቸዉም ለዚህ ሀሳብ ትክክለኛነት ድፍረቱ ካላቸዉ የፖለቲካ ድርጅቱን እምነት ብቻ እንደ ፖለቲካ ሳይሆን እንደ ሀይማኖት አክርሮ በሚሰብክ የሚዲያ ተቋማት ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ክብር የሚሰጧቸዉና ተአማኒነት ባላቸዉ የዜና ተቋሞች ማብራሪያ እንዲሰጡ ይጠበቃሉ (አይጋ ፎረምን ማለቴ እንዳልሆነ ማስታወሻ ይያዝልኝ አስመሮም ለገሰንም የኢትዮጵያ ችግር ፈላጊ አድርጎ የሚያቀርብ ከክቡር ኢሳይያስ አፈወርቂ ቀጥተኛ ትእዛዝ የሚሰጠዉ በመሆኑ እሱም አይመቸኝም)።
ሼህ አላሙዲ ላገራችን/ቸዉ ጥሩ ሰርተዉ በመረጃ እጥረት ስራቸዉን ካቃለልንባቸዉ በጣም ያሳዝናል በሌላ በኩል ደግሞ ሼህ አላሙዲ በዉጭ ሀገር እንደተመለከቱት ሁሉ በገለልተኝነት በኢንቨስትመንት ስራቸዉ ላይ ብቻ አተኩረዉ እጃቸዉን ሰብስበዉ ከመቀመጥ ይልቅ ከዚህ አፋኝ ስርአት ጋር እጅና ጓንት ሁነዉ ከሰሩም ኢትዮጵያዉያን የወያኔ መሪዎችን ባየንበት አይን የምንመለከታቸዉ መሆኑን በግልጽ ማስገንዘብም ያስፈልጋል።
ለማንኛዉም ይህንን ነገር ለማጥራት ሼክ አላሙዲ ከዶ/ር አክሎግ ቢራራ/ዶ/ር ጌታቸዉ በጋሻዉ ጋር በመሆን ፓናል ዉይይት ቢያደርጉልን ይህንን የጥርጣሬ ደመና ያጠራዋል የሚል እምነት አለኝ። እዚህ ላይ የወያኔ መሪዎች ሰዉን ለማሳሳት እንደ ሀዉዜዉ ድራማ ሁኔታ ጠብቀዉ በተቀረጸ ምስል ሰዉን ማሳሳት ልማዳቸዉ ስለሆነ አንባቢ የነዚህን ሰዎች ተንኮል ከነሱ ቀድሞ ሊገነዘብ ግድ ይላል ባለፈዉ ንብ ይሁን ዝንብ ያለበት ሸሚዝ እኝህን ሼህ አልበሰዋቸዉ በማየቴ ነዉ። ሐይለ ማርያም ደሳለኝ ክርስቶስን በአካል አግኝቸዋለሁ ማለት የሚዳዳቸዉ፤ መጠጥ ወደዚህ አለም ከመጡ ጀምሮ ሸቷቸዉ የማያዉቅ አፍሪካ መሪዎች ስብሰባ አቶ በረከት በጆሯቸዉ ምን እንዳላቸዉ አይታወቅም በእለቱ በሳቸዉ ሻምፓኝ ፍጆታ ምክንያት መሪዎቹ ሳይቃመሱ እንዳለቀ በትዝብት ተስተዉሏል። እንግዲህ እንዲህ ለነብሳቸዉ ያደሩትን መጠጥ የጋቱ ሼክ አላሙዲን ተናዳፊ ንብ ቢያለብሱም ብዙም ሊገርም አይገባም።
በእርግጥ ካፒታል ኢንቨስትመንት ከምእራብ አገሮች በላይ ወደ ታዳጊ አገሮች ቢፈስ በብዙ እጥፍ ትርፍ ሊያመጣ ቢችልም እኚህ ሼህ ግን ወደ ትዉልድ ሀገራቸዉ መዋእለ ንዋያቸዉን መሳባቸዉ ሊያስመሰግናቸዉ ሊያስከብራቸዉም ይገባል ለማንኛዉም ከሊቃዉንቱ ጋር የሚያድርጉት ዉይይት ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ስለሚመለስልን በዚህ ነገር ትርፍ ለማምጣት የሚክለፈለፉ ወገኖች በጋዜጠኝነት ስም ወደዚህ አካባቢ ዝር ሳይሉ ጉዳዩ ክብርና እዉቅና ባላቸዉ ወገኖች እና ምሁራን ዉይይት ቢደረግበት ዜጋ ብዙ ጥቅም ሊያገኝበት ይችላል የሚል ጽኑ እምነት ሲኖረኝ ሼህ አላሙዲም በሄዱበት ሁሉ አጃቢያቸዉ ኢትዮጵያዉ ሁኖ ያለሃሳብ የኢትዮጵያዊነት ነጻነት የሚያስገኘዉን ጥቅም ተቋዳሺ ይሆናሉ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ።እንግዲህ እንደተለመደዉ ለእርምትና፤ለትንኮሳ በዚህ ድርሱኝ gebeyhubalcha@yahoo.com
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ገበየሁ ባልቻ
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/7950#sthash.Xx56su9G.dpuf
No comments:
Post a Comment